ሩሲያ የዩክሬንን መዲና ለዘጠነኛ ጊዜ በሚሳኤል አጠቃች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሩሲያ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ዘጠነኛ የተባለውን የሚሳኤል ጥቃት በዩክሬን መዲና ኪዬቭ ላይ ፈጸመች።
የኪዬቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊችኮ የሚሳኤል ጥቃቱ መቀጠሉን ገልጸው በአንድ አካባቢም የወዳደቁ ሚሳኤሎች የእሳት ቃጠሎ ማስነሳታቸውን ነው።
ከመዲናዋ በተጨማሪ በማዕከላዊ ዩክሬን በሚገኙት ቪኒትሳ፣ ክሜልኒትስኪ እና ዚሂቶሚር ግዛቶች ውስጥ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል።
የኪዬቭ ወታደራዊ አስተዳደር መረጃ እንደሚያመለክተው በከተሞቹ ላይ የተቃጡ ሚሳኤሎች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ነው።
ሩሲያ በኪዬቭ ላይ የአየር ጥቃት በአንድ ወር ብቻ ለዘጠኝ ጊዜ ያህል ፈጽማለች።
በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ዩክሬን ስድስት የኪንዝል ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን መትታ መጣሏን አስታውቃለች።
ሩሲያ ማክሰኞ የፈጸመችው ጥቃት መጠነ ሰፊም ነው ተብሏል።
ከንቲባው በቴሌግራም ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት እሳቱ በኪዬቭ በሚገኝ ዳርኒሺያ አካባቢ በሚገኝ ጋራዥ ውስጥ መከሰቱን ገልጸው ነገር ግን ጉዳት የደረሰበት አካል የለም ብለዋል።
የኪዬቭ ወታደራዊ አስተዳደር ኃላፊ በበኩላቸው ሩሲያ ከካስፒያን ባህር ባስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች ከባድ ጥቃት ተፈጽሟል ብለዋል።
ኃላፊው ሰርሂይ ፖፕኮ ጥቃቱ ክሩዝ ሚሳኤሎችን ያካተተ ሊሆን እንደሚችልም ጠቆም አድርገዋል።
ሩሲያ የአየር ጥቃቷን ከከፈተችም በኋላ የክትትል ድሮኖችን በኪዬቭ ላይ ማሰማራቷን አክለው ተናግረዋል።
ከኪዬቭ በስተምስራቅ በሚገኘው ዴስያንስኪ ግዛትም መኖሪያ ባልሆኑ ሕንጻዎች ላይም ሁለተኛ የእሳት ቃጠሎ ተነስቷል ብለዋል። ነገር ግን ኃላፊው የተጎዱ ሰዎችን በተመለከተ ምንም አይነት መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ረቡዕ ዕለት በኼርሶን ግዛት አቅራቢያ በከባድ መሳሪያ በደረሰ ጥቃት አንድ የአምስት ዓመት ህጻንን ጨምሮ ቢያንስ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ 17 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። ሁለቱም አካላት የሰላማዊ ሰዎች መኖሪያን በከባድ መሳሪያ በማጥቃት እየተወነጃጀሉ ይገኛሉ።
ዩክሬን ቀስ በቀስ በሩሲያ ወራሪ ኃይሎች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀች መሆኑም ተገልጿል።
ምዕራባውያን ባለስልጣናት የዩክሬን ጦር በሩሲያ ላይ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን የመልሶ ማጥቃት እርምጃም ከመጀመሩ በፊትም “በከፍተኛ የዝግጁነት ደረጃ ላይ” መሆኑን ተናግረዋል።












