ትግራይ ውስጥ በረሃብ ምክንያት 25 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

የሚያለቅሱ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ትግራይ ክልል ሳምረ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ ሁለት ጎጦች በረሃብ ሳቢያ 25 ሰዎች እንደሞቱ ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት ገለጹ።

ከሞቱት መካከል ሕጻናት፣ ሴቶችና ሽማግሌዎች እንደሚገኙበት የአካባቢው አመራሮች ለቢቢሲ ትግርኛ ጨምረው ተናግረዋል።

የ51 ዓመቱ የዓምዲ ወያነ ኗሪ የሆኑት አቶ ታደሰ ገብሩ የቤተሰብ አባሎቻቸው ከሞተባቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ ናቸው።

አቶ ታደሰ የአራት ልጆች እናት የሆኑት ባለቤታቸው መጋቢት 24/2015 ዓ.ም መሞታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። የሞቱበት ምክንያትን ሲጠየቁም “ረሃብ” እንደሆነ አስረድተዋል።

ሌላዋ የአካባቢው ነዋሪ ወ/ሮ ለተሥላሰ ሐጎስም ባለቤታቸውን ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም በረሃብ እንዳጡ ይናገራሉ።

“ጥዑም ወልደገብርኤል ይባላል። በፊት አካባቢውን ጠላት ተቆጣጥሮት በነበረበት ወቅት ምግብ የሚባል ነገር ስላላገኘን ቤታችንን ጥለን ሄደን ነበር። ጠላት ሄዷል ስንባል ወደ ቤታችን ገባን። ከዛ በኋላም ቢሆን ግን ከበባ ስለነበር የሚበላ የሚጠጣ አልነበረም” ይላሉ።

ለተሥላሰ ባለቤታቸው በብርድና በረሃብ መሞታቸውን ይገልጻሉ።

የአካባቢው ነዋሪዎች በፌደራል መንግሥትና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ከመፈረሙ በፊት፣ አልፎ አልፎ በሰው 15 ኪሎ ስንዴ ያገኙ የነበረ ቢሆንም ከሰላሙ በኋላ ግን ከመነግሥት እርዳታ ያለገኙ ሰዎች እንዳሉ ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ።

“ሰላም ሲሆን ይሰጠናል ብለን ነበር። ሰላም ሲሆን ግን ያገኘነው ነገር የለም። ፈጽሞ ፈጽሞ አልመጣልንም” ይላሉ አቶ ታደሰ።

ባለቤታቸው ሲሞቱ ከ5 ልጆች ጋር ብቻቸውን የቀሩት ወይዘሮ ለተስላሰ “ልጆቹን ልመና ሂዱ ብንልም ልመና የለም፤ ሁሉም አንድ ሆኗል” በማለት ሁኔታውን ይገልጻሉ።

“ሕዝብ ሊረግፍ” ነው ሲሉም ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የመጀመርያ ልጃቸው በረሃብ እንደሞተች የሚናገሩት ወይዘሮ ፈጸጉ አበራ ደግሞ፣ ቤተ ክርስትያንን የአካባቢው አስተዳደር ከኅብረተሰብ እያዋጣ ድጋፍ እንደሚያደርግ ይጠቁማሉ።

እርሳቸው ከሦስት ልጆቻቸው ጋር “አንድ እንጀራ ጧት፣ አንድ እንጀራ ማታ” እንደሚሰጣቸውና ቀን ጾማቸውን እንደሚውሉ ተናግረዋል።

የዓምዲ ወያነ ጎጥ አስተዳዳሪ አቶ አሸብር ተካ፣ የአካባቢው ሕዝብ ለረዥም ግዜ ችግርን ሲጋፈጥ መቆየቱ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ከሁለት ዓመት በላይ በቆየው ጦርነት የአካባቢው ማኅበረሰብ የነበረውን ጥሪት በማጣቱ ችግሩን አንዳባባሰው ጨምረው ገልጸዋል

ወ/ሮ ለተሥላሰ አንዳንድ ሰዎች የዘሩት ሰብል በማዳበርያ እጦት እንደተጎዳና የቀረውንም በረዶ እንዳበላሸው ጨምረው ይገልጻሉ።

በዓምዲ ወያነ ጎጥ ውስጥ 16 ሴቶችና 6 ወንዶች እንደሞቱ የሚገልጸው አቶ አሸብር ተካ፣ የእርዳታ አሰጣጡ “አጥጋቢ” እንዳልነበር ይናገራል።

“በ3 ዓመት ውስጥ 8 ጊዜ” ብቻ እርዳታ እንደተሰጠ በመግለጽ፣ እርዳታ በቀጣይና በፍጥነት ባለመምጣቱ የኅብረተሰቡን ችግር ሊፈታ እንዳልቻለም ያስረዳል።

ኅብረተሰቡ “ለስድት፣ ለረሃብና ሞት” እንደተጋለጠም ጨምረው አስረድተዋል።

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ መሐሪ በበኩላቸው ከመስከረም ወር ጀምሮ እስከ አሁን 25 ሰዎች መሞታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“ኅብረተሰቡ ያለውን ስለሚከፋፈል ከመደበኛው እርዳታ ውጭ በተለይ ለእናቶችና ሕጻናት ምግብ የሚሰጡ በጎ አድራጊዎች ባያግዙ ከ25 ሰዎች በላይ ሊሞቱ” ይችሉ እንደነበር ገልጿል።

ቢቢሲ ከክልሉ የአደጋ ስጋትና ቅድመ ዝግጅት ኮሚሽን አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ሊሳካ አልቻለም።

የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፕሮግራም አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የተላካ እርዳታ ሲሰረቅና ገበያ ላይ ሲውል በማየታቸው ለግዜው እርዳት መስጠት እንዳቆሙ በዚህ ወር ውስጥ መግለጻቸው ይታወሳል።

በትግራይ የተቀሰቀሰውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውና ሚልዮኖች ከቀያቸው ተፈናቅለው እርዳታ ጠባቂ መሆናቸው ይታወቃል።