የህወሓት ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?

የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) እና ምክትላቸው ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር

የፎቶው ባለመብት, tplf

የምስሉ መግለጫ, የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) እና ምክትላቸው ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር

ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ወታደራዊውን መንግሥት በመቃወም የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ. ም. ነበር ወደ ትጥቅ ትግል የገባው።

በኋላም ግንቦት 1981 ዓ. ም. በትግራይ ውስጥ በተምቤን ዓዲ ገዛእቲ በሚባል አካባቢ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የሚባል ጥምር ግንባር መሠረተ።

ግንባሩን ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እና በኋላ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደሕዴን) ተቀላቅለውታል።

በ1983 ዓ.ም. በወታደራዊ ኃይል ደርግ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ በህወሓት መሪነት የተመሠረተው ግንባር አገሪቱን ማስተዳደር ያዘ።

ህወሓትም የግንባሩ አውራ ፓርቲ ሆነ።

የህወሓት እና የኢህአዴግ የረዥም ጊዜ ሊቀ መንበር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት እና በጠቅላይ ሚኒስትርነት መርተዋል።

በዋነኛነት በኦሮሚያ ተነስቶ በመላው አገሪቱ የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፍቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለቀው ዐቢይ አሕመድ የግንባሩን ሊቀመንበርንት መረከባቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ኢሕአዴግን ከአራት ፓርቲዎች ግንባርነት ወደ ውህድ ፓርቲ በማሸጋገር ብልጽግና ፓርቲ ሲመሠረት፣ የግንባሩ አስኳል የነበረው ህወሓት ራሱን አግልሎ በትግራይ ከተመ።

ከብልጽግና መመሥረት በኋላ ፓርቲው ማዕከላዊውን መንግሥት የተቆጣጠረ ሲሆን እራሱን ካገለለው ህወሓት ጋር የነበረው ግንኙነት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ክፉኛ እየተበላሸ የሁለቱ ፓርቲዎች አለመግባባት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ወደ ደም አፋሳሹ ጦርነት አመራ።

በዚህ ወቅት ነበር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህወሓትን ህጋዊ ሰውነት ሰርዞ ህልውናው ማብቃቱን ያሳወቀው።

ለሁለት ዓመት የዘለቀው ጦርነት በፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት ቢጠናቀቅም ቦርዱ ዕውቅናውን መልሶ ለፓርቲው አልሰጥም።

ህወሓት ለምን ተሰረዘ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፣ ቦርዱ በወቅቱ ህወሓት ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጻ ተግባር ላይ ተሰማርቷል በሚል ጉዳዩን መመርመሩን እና ማስረጃዎችንም መመልከቱን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚከታተል እና የሚቆጣጠር ክንፍ አለው። ይህ አካል በወቅቱ የህወሓት አመራሮች የሚሰጧቸውን መግለጫዎች መሠረት አድርጎ የፓርቲውን ሕጋዊነት የመሰረዝ ጉዳይ ማንሳቱን ጠቁመዋል።

ጉዳዩ በቦርዱ መታየት በጀመረበት ወቅት በህወሓት በኩል “ያለውን የመሰማት መብት በሕጉ ስለነበረው” ፓርቲውን ወክለው ከቦርዱ ጋር ግንኙነት ለነበራቸው ግለሰብ ማሳወቃቸውንም ያስታውሳሉ።

“በወቅቱ እኛ ጉዳዩን በምናይበት ጊዜ ክስ ቀርቧል እና በዚህ ጉዳይ ምላሽ ስጡ ብለን ጠየቅን። ተወካዩም “ፓርቲውን እንደበፊቱ ወክዬ የምቀርብበት ሁኔታ ስለለሌለ መጥቼ ላስረዳ አልችልም አሉ’” ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላም በቀረበው ማስረጃ መሠረት ኃይልን መሠረት ባደረገ በአመጻ ተግባር ላይ ፓርቲው ተሳትፏል በሚል “በአዋጁ በግልጽ እንደተቀመጠው የመሰረዝ ውሳኔ መሰጠት እንዳለበት ቦርዱን ያስገድደዋል። ይህንን መሠረት አድርገን ፓርቲው ተሰርዟል” ብለዋል አቶ ውብሸት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን ታኅሣሥ 28/2013 ዓ.ም. ያስተላላፈ ሲሆን፣ ውሳኔው ይፋ የተደረገው ጥር 10/2013 ዓ.ም. ነበር።

በሕጉ መሠረትም ፓርቲውን መሰረዝ ብቻ ሳይሆን የፓርቲው ኃላፊዎች ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ውሳኔ የተላለፈ ሲሆን፣ “እንዲሁም ዕዳ ካለበት ንብረቱ ለዕዳ መሸፈኛ እንዲሆን ዕዳ ከሌለበት ደግሞ የሚቀር ገንዘብ ወይም የሚተርፍ ንብረት ካለ ለሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት እንዲውል” መወሰኑን አስረድተዋል።

የህወሓት ጥያቄ ለምን ውድቅ ሆነ?

የሁለት ዓመቱ ደም አፋሳሽ ጦርነት በመንግሥት እና በህወሓት መካከል በተደረገ ስምምነት ከተቋጨ በኋላ፣ ፓርቲው በበላይነት የሚመራው ጊዜያዊ የክልል መስተዳደር ተቋቁሟል።

በተጨማሪም በጦርነቱ ወቅት በሽብር ቡድንነት የተጣለበት ፍረጃ እና በእስር ላይ የነበሩ የቡድኑ አመራሮች እና አባላት ተለቀው ፓርቲው ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በቅርበት እየሰራ ነው።

ይህንንም ተከትሎ ህወሓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰረዘበት ሕጋዊ ሰውነት እውቅና እና ንብረቶቹ እንዲመለሱለት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘቱን ቦርዱ አሳውቋል።

ለዚህም የተሰጠው ምክንያት አንድ ፓርቲ የመሰረዝ ዕጣ ሲገጥመው ህልውናውን መልሶ የሚያገኝበት ሁኔታ በቦርዱ አዋጅ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አለመቀመጡን ለውሳኔው መነሻ መሆኑን አቶ ውብሸት ይናገራሉ።

የአንድ የተሰረዘ ፓርቲን “ህልውናን መልሶ መስጠትን የሚደግፈው ሕግ በሌለበት ቦርዱ ሊሰጥ አይችልም፤ ከሰጠም ቦርዱ ከተጠያቂነት አያመልጥም። ስለዚህ ጉዳዩን ከዚህ ውጭ ማየት የሚቻልበት ሁኔታ የለም” ብለዋል።

ስለዚህም ጥያቄውን ከሕግ፣ ከደንብ እና ከመመሪያ ውጭ ላለመወሰን በገለልተኛነት ኃላፊነቱን ለመወጣት ባለበት ኃላፊነት “ከተቋሙ አንጻር ሌላ አማራጭ የለም። ከአዋጅ፣ ከደንብ እና ከሕግ ውጪጭ አንሠራም” ብለዋል።

በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ላይ ጥያቄ ኣላቸው በመቀለ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር እና የሕገ መንግሥት ተማራመሪ የሆኑት አቶ ገብረመስቀል ኃይሉ “ቦርዱ ህወሓት በሕገ ወጥ ድርጊት ውስጥ ስለተሳተፈ ሕጋዊነቱ ይነጠቃል የሚለውን ብቻ ነው የተረጎመው” ይላሉ።

ነገር ግን “ሕግን የሆነ ዓላማን እንዲያሳካ በሚያስችል መልኩ እንጂ ቃል በቃል መተርጎም አይገባም” በማለት፣ ቦርዱ ውሳኔ የሚሰጠው “የቀረበው ጥያቄ ታይቶ፣ ክርክር ተደርጎበት ነው መልስ ሊሰጥ የሚገባው” ይላሉ አቶ ገብረመስቀል።

በተጨማሪም የፕሪቶሪያው ስምምነት በህወሓት እና በፌዴራል መንግሥቱ መካለል የተደረገ መሆኑን በመጥቀስ “ይህ ማለት ህወሓት የሚባል ህልውና ያለው አካል መኖሩን የሚያመላክት ነው” ብለዋል።

ስለዚህም “ድርድር እና ስምምነት ከተደረገ በኋላ ህወሓት የሚባል አካል እውቅና የለውም የሚል ውሳኔ ልክ አይደለም” ሲሉ አቶ ገብረ መስቀል ይሞግታሉ።

የህወሓት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?

ምርጫ ቦርድ ህወሓት ሕጋዊ እውቅናው እንዲመለስለት ያቀረበውን ጥያቄ በአውንታዊ ለመመለስ የሚያስችለው የሕግ መሠረት ባለመኖሩ፣ እንደ አዲስ ለመመዝገብ እንዲጠይቅ መክሯል።

ነገር ግን ህወሓትም ሆነ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የቦርዱ ምላሽ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ መሆኑን በመጥቀስ ተቃውሞውታል።

በዚህም ሳቢያ የፓርቲው ሕጋዊነት ጉዳይ በእንጠልጥል ላይ ይገኛል። ትልቁ ጥያቄም ቀጣይ የህወሓት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? የሚለው ሆኗል።

በተደረሰው ስምምነት መሠረት ጊዜያዊውን የክልሉን መስተዳደር የሚተካ ቋሚ አስተዳደር ለማቋቋም እና በፌደራል የክልሉን ተወካዮች ለመሰየም በሚቀጥለው ዓመት ምርጫ እንደሚደረግ ተገልጿል።

በአዋጁ እና በድንጋጌዎች መሠረት ህወሓት ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ ለመንቀሳቀስ የሚችለው ድጋሚ የምዝገባ ጥያቄ ሲያቀርብ እና ቦርዱ ሕጉን መሠረት አድርጎ ሲፈቅድ መሆኑን ምርጫ ቦርድ ወስኗል።

ህወሓት እንደ አዲስ በሕጉ ላይ የተመለከቱትን የምዝገባ መስፈርቶች አሟልቶ መቀረብ እንዳለበት ውሳኔ ማሳለፋቸውን እና በደብዳቤው መግለጻቸውን አቶ ውብሸት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“መልሰው ሊመዘግቡት ይችላሉ። ነገር ግን ገንዘብ እና ውርስ የሌለው፤ እንደ ሌሎች አዲስ ድርጅቶች ሆኖ ተጽዕኖ የማይፈጥር አናሳ ድርጅት እንዲሆን የተፈለገ ነው የሚመስለኝ” የሚሉት አቶ ገብረ መስቀል ናቸው።

ጉዳዩ በትግራይ በኩል ምን ዓይነት ምላሽ ይኖረዋል የሚለው ወደፊት እንደሚታይም ነው ያሉት አቶ ተብረ መስቀል “ከፓርቲው አጠቃላይ ሂደት በተጨማሪ ሙስና እና የፍትሕ ዕጦት ያነግሸገሸው ሕዝብ በዚህ ውሳኔ ምን እንደሚሰማው አላቅም” ብለዋል።

እንደተባለው ህወሓት እንደ አዲስ ለመመዝገብ የሚፈልግ ከሆነ በተመሳሳይ ስም መምጣት ይችላል እንደሆነ ከቢቢሲ የተጠየቁት አቶ ውብሸት “እሱ ጥያቄው ሲመጣ የምናየው ይሆናል” ሲሉ አጭር መልስ ሰጥተዋል።

ህወሓት እና የፕሪቶሪያ ስምምነት?

በህወሓት እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ የተደረሰውን ግጭት ያስቆመና ዘላቂ ሠላም እንዲፈጠር መንገድ የከፈተ ሆኗል።

ይህን ተከትሎም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብር ቡድንነት ተሰይሞ የነበረው ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ፍረጃው እንዲነሳለት መደረጉ ይታወሳል።

“ይሄን ሁሉ [የሠላም ስምመነቱ እና ከአሸባሪነት መሰረዙ] ከሆነ በኃላ ‘አላቅህም፤ ሕጋዊ አይደለህም’ ማለት በእነዚህ ሃቆች ዐይን ሲታይ ተቀባይነት የለውም” ይላሉ አቶ ገብረመስቀል።

አገራዊ ዕርቅ ለመፍጠር እየተደረገ ባለበት ወቅት እንደዚህ ዓይነት ውሳኔ አሉታዊ፣ የሠላም ስምምነቱን የሚያበላሽ እና አደገኛ ሁኔታ ሊያስከትል እንደሚችልም ነው ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀመጡት።

“ምናልባትም የተደረገው የሠላም ስምምነት ላይ የራሱ አሉታዊ ጥላ ሊያሳርፍ ይችላል። ጊዜያዊ መንግስትም እንዳልተመሰረተ ነው የሚቆጠረው። ከማን ጋር ነው ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት የተቋቋመው የሚል ጥያቄም ያስነሳል” ብለዋል።

የፕሪቶሪያው ስምምነት በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ላይ ያለውን ተጽዕኖ በተመለከተ ቢቢሲ ለአቶ ውብሸት ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

ቦርዱ ከተቋቋመበት በተጨማሪ ፓርቲዎች የሚተዳደሩበት አዋጅ መኖሩን ጠቅሰዋል።

እነዚህን መሠረት አድርገው የወጡ መመሪያዎች ብቻ ቦርዱን የሚገዙ መሆናቸውን ገልጸው፣ አንድ ፓርቲ ህልውናው እንዲቀጥል ወይም እንዳይቀጥል የማድረግ ነገር የሚወሰነው በሕጉ መሆኑን ተናግረዋል።

“ከዚህ ውጭ እኛን የሚመለከተን ነገር አይደለም” ሲሉ አቶ ውብሸት ምላሽ ሰጥተዋል።

ህወሓት ምን አለ?

የምርጫ ቦርዱን ውሳኔ በተመለከተ ህወሓት እና በህወሓት የሚመራው ጊዜያዊ የክልሉ መስተዳደር መግለጫ አውጥቷል። የቦርዱን ውሳኔንም ተቀባይነት የሌለው ብለውታል።

ሁለቱም መግለጫዎች ውሳኔው ጦርነቱን ባስቆመው የሰላም ስምምነት ላይ ጥላውን የሚያሳርፍ እና ክልሉን ምልሶ ከጦርነት እንዲያገግም ለማድረግ የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደርም ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

“በፕሪቶሪያ የተደረሰው ስምምነት እና ሕግን መሠረት ያላደረገ፤ እየተጠናከረ በመሄድ ላይ ያለውን የሰላም ስምምነት ትግበራን ባለቤት አልባ የሚያደርግ” በማለት ነው ውሳኔውን አጥብቆ የተቃወመው።

የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሕጋዊም ሆነ ፖለቲካዊ ተቀባይነት እንደሌለውም “በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የሰላም ተስፋ ከመደገፍ ይልቅ የሰላም ስምምነቱ ዋናው ባለቤት የሆነው ህወሓት ህልውና እንዳይኖረው ለማድረግ ያስተላለፈው” ነው ብሏል።

ፓርቲው ጨምሮም ስምምነቱ በተለያዩ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በፍትሕ ሚኒስቴር እና በሌሎችም አካላት ስምምነቱ እውቅና እና ድጋፍ የሰጡት መሆኑን በመጥቀስ “የቦርዱ ውሳኔ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የማይቀበል ነው” ሲል አጥብቆ ተችቶታል።

የቦርዱ ውሳኔ “የሰላም ሂደቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ያለው ህወሓት፣ ውሳኔውን እንደማይቀበለው እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚወያይበት ገልጿል።

“የምርጫ ቦርድ ውሳኔውን እንደገና በማጤን የፕሪቶሪያን ስምምነት እና ሌሎች የፌደራል ተቋማት ያሳለፉትን ውሳኔዎች መነሻ በማድረግ” ጥያቄውን እንዲቀበል ጠይቋል።

የፌደራል መንግሥቱም “ሕጋዊ እና ፖለቲካዊ አማራጮችን” ተጠቅሞ ፓርቲው ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት እንዲመለስ እንዲያደረግም ጥሪ አቅርቧል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተደደርም የቦርዱ ውሳኔ “የሰላም ስምምነቱን ባለቤት አልባ የሚያደርግ” እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ እየተሳተፉ ያሉት ከፍተኛ የህወሓት አመራሮችን “እውቅና በመንፈግ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ህልውና አደጋ ላይ ይሚጥል” ነው በማለት የሰላም ስምምነቱን የሚፈታተን በመሆኑ ቦርዱ ውሳኔውን መርምሮ እንዲያስተካክል ነው ጠይቋል።