በህወሓት ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮች ላይ የቀረቡ ክሶች መነሳታቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, tplf
በትግራይ ውስጥ የተካሄደው ጦርነትን ተከትሎ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው ተከሰው የነበሩ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች ክሳቸው እንዲነሳ መወሰኑን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከሁለት ዓመት በፊት በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጦርነት በተቀሰቀሰበት ጊዜ በበርካታ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ላይ ከባድ የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር ይታወሳል።
በዚህም በመንግሥት ቁጥጥር ስር የነበሩትን ከፍተኛ የህወሓት ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮች እና ባልተያዙት ላይ ጭምር ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶ የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸው ቆይቷል።
የፍትሕ ሚኒስቴር ሐሙስ መጋቢት 21/2015 ዓ.ም. እንዳሳወቀው በፌዴራል መንግሥት እና ህወሓት መካከል በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሠረት ከግጭቱ ጋር ተያያዥ የሆኑ ወንጀሎች ተጠያቂነት በተመለከተ በሽግግር ፍትሕ ማዕቀፍ ሊታዩ እንደሚገባ መወሰኑን በመግለጽ ክሱ እንዲነሳ መደረጉን አመልክቷል።
ስለሆነም በወንጀል ተጠርጥረው ክስ ቀርቦባቸው የነበሩ የህወሓት አመራሮችን ክስ በክርክር ሂደት ላይ ይገኙ የነበሩ የወንጀል ክሶች በአዋጅ 943/2008 አንቀጽ 6 (3) (ሠ) መሠረት የተነሱ መሆናቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር አሳውቋል።
ይህ ውሳኔ ይፋ የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህወሓት ላይ ጥሎት የነበረውን የሽብርተኛ ቡድንነት ፍረጃን ከተነሳ እና ክስ ተመስርቶባቸው ከነበሩት ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ከተሾሙ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።
ጦርነቱ ከተጀመረ ከወራት በኋላ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት እና የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤልን እንዲሁም የአሁኑ የክልሉ ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በበርካታ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ላይ ከባድ የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው ነበር።
ህወሓት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ ከተሰየመ በኋላ ከቡድኑ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮች በተጨማሪ፣ ከህወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ተቋማት ጭምር ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር ይታወሳል።
በህወሓት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ የፌደራል ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ የአገር ክህደት ወንጀልን ጨምሮ በርካታ የከባድ ወንጀሎች ክስ አቅርበው የተጠርጣሪዎቹ ንብረት ታግዶ የመያዣ ትዕዛዝ አውጥተውባቸው ነበር።
አዲስ አበባ እና ትግራይን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥም በርካታ የህወሓት አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለው ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቷል።
ከእነዚህም መካከል ከህወሓት መስራቾች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ስብሐት ነጋ እና ሌሎችም ትግራይ ውስጥ ተይዘው ወደ አዲስ አበባ መጥተው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ተይዞ ባለበት ጊዜ፣ በጤና እና ከዕድሜ ጋር በተያያዘ በምህረት መለቀቃቸው ይታወቃል።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. በተቀሰቀሰው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት እንደጠፋ እና በቢሊዮኖች ዶላር የሚገምት የንብረት ውድመት መድረሱ ይነገራል።
ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ጦርነት ለማስቆም ሲደረግ የነበረው ጥረት ባለፈው ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. የፌደራል መንግሥቱ እና የህወሓት መሪዎች ደቡብ አፍሪካ ላይ በደረሱት ስምምነት ውጤታማ ሆኖ ጦርነቱ እንዲቆም አስችሏል።
ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ በተደረሰው በዚህ ስምምነትም በጦርነቱ ተሳታፊዎች የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች እና በደሎች በሽግግር ፍትሕ ሂደት መቋጫ እንዲያገኙ መወሰኑ ይታወሳል።
በዚህም መሠረት የፌደራሉ የፍትሕ ሚኒስቴር የህወሓት አመራሮች ላይ አስከ ሞት ሊያስቀጡ በሚችሉ ከባድ ወንጀሎች የቀረበባቸው ክስ ክስ እንዲነሳ መወሰኑን አሳውቋል።












