አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳደር እንዲሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሾማቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳደር እንዲሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሾማቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታወቀ።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከዚህ በፊት ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት፣ እንዲሁም በመንግሥት እና በህወሓት መካከል ፕሪቶሪያ ላይ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ነው ጊዜያዊ መንግሥቱ የሚቋቋመው።
አክሎም የሚኒስትሮች ምክር ቤት መጋቢት 09/2015 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባው የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደርን የሚመለከት ደንብ ማጽደቁን አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህወሓት ከፍተኛ አመራር አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን እንዲመሩ የሾሙት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከህወሓት ላይ የሽብርተኛ ቡድንነት ስያሜን ካነሳ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቡዕ መጋቢት 13/2015 ዓ.ም. ልዩ ስብሰባ በመጥራት ነበር በትግራይ ጦርነቱ መቀሰቀሱን ተከትሎ በህወሓት ላይ የተጣለውን የሽብርተኝነት ፍረጃን ያነሳው።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ህወሓት ሥራ አስፈጻሚ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር የሆኑትን አቶ ጌታቸው ረዳን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ መሰየሙ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን እንዲመሩ የሾሙ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ርዕሰ መስተዳደሩ በክልሉ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች የሚሳተፉበት አካታች አስተዳደር እንደሚያዋቅሩ ተገልጿል።
በተጨማሪም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ርዕሰ መስተዳደር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የክልሉን አስፈጻሚ አካል የመምራት እና የማስተባበር ኃላፊነት እንደተጣለባቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የፌደራል መንግሥቱ ውድቅ ያደረገው ምርጫ በትግራይ ክልል ተካሂዶ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በክልሉ ውስጥ ጊዜያዊ አስተዳደር ሲቋቋም የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ለሁለት ዓመት የቆየው ጦርነት ትግራይ ውስጥ ተጀምሮ በሳምንታት ውስጥ የፌደራሉ ሠራዊት ዋና ከተማዋን እና በአብዛኛውን የክልሉን አካባቢ በተቆጠጠረበት ወቅት ጊዜያዊ አስተዳደር አቋቁሞ እንደነበር ይታወሳል።
በዚህም መሠረት ዶክተር ሙሉ ነጋ ቀዳሚው ጊዜያዊ አስተዳዳሪ የነበሩ ሲሆን፣ ቀጥሎም የአሁኑ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም በላይ ለአጭር ጊዜ ቦታውን ይዘው ቆይተው ነበር።
ነገር ግን ጦርነቱ ተባብሶ የትግራይ ኃይሎች መቀለን መልሰው ሲቆጣጠሩ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ህልውና በዚያው አክትሟል።
በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ከወራት በፊት በፕሪቶሪያ በተደረሰው ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም በተደረሰው ስምምነት መሠረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሰረት ተወስኗል።
ህወሓት የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ካዋቀረ በኋላ በሰላም ስምምነት መሠረት በፌዴራል መንግሥት መጽደቅ አለበት።
በሚዋቀረው ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የሚኖርን ውክልናን በተመለከተ 30 በመቶ ለህወሓት፣ 25 በመቶ ለትግራይ ሠራዊት፣ 15 በመቶ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ቀሪው ለምሁራንና ለሲቪክ ማህበራት እንደሚሰጥም ከዚህ ቀደም መገለጹ ይታወሳል።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግሥት ምሥረታ ጋር ተያይዞ ምሥረታውን ለማካሄድ የተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴ ከትግራይ ተቃዋሚዎች በኩል ተቃውሞ እንደተነሳበት መገለጹ ይታወሳል።
ሳልሳይ ወያነ፣ ባይቶና እና የትግራይ ነጻነት ፓርቲዎች በኮሚቴው ላይ የገለልተኝነት እና የአሳታፊነት ጥያቄ በማንሳት ከሂደቱ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል።
ኮሚቴው የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ሌ/ጄኔራል ታደረሰ ወረደ እና አቶ ሙሉ ወርቅ ኪዳነማርያምን ጨምሮ ዘጠኝ አባላት ያሉት ሲሆን፣ ሦስት ከትግራይ ኃይሎች፣ ሦስት ከህወሓት እና ሦስት ከሲቪክ ማኅበራት የተውጣጡ መሆናቸው በወቅቱ ተገልጿል።
ጥቂት ስለ አቶ ጌታቸው ረዳ
ትግራይ ውስጥ ለሁለት ዓመታት ከተካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ ስማቸው በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ከነበሩ ሰዎች መካከል ጌታቸው ረዳ አንዱ ናቸው። አቶ ጌታቸው የትግራይ ኃይሎችን በመወከል በጦርነቱ ሂደት ውስጥ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ላይ በተደጋጋሚ ሲቀርቡ ቆይተዋል።
ጌታቸው ረዳ በፓርቲ፣ በክልል እንዲሁም ፌደራል መንግሥቱ ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ሰርተዋል። የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ ሆኖ በቆየው ህወሓት ውስጥ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፣ የፕሬዝዳንቱ ረዳት እና የፓርቲው ቃል አቀባይ ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ከፍተኛ አማካሪ ሆነው ከመሥራታቸው በተጨማሪ፣ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትርም እና በሌሎች የኃላፊነት ቦታዎችም ሠርተዋል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው አቶ ጌታቸው ከአሜሪካው የአላባማ ዩኒቨርስቲ ደግሞ በሕግ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በዚሁ ዘርፍ በመቀለ ዩኒቨርስቲ መምህር ሆነው ሠርተዋል።
አቶ ጌታቸው በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ሄዶ ወደ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ተሰማርተው ከነበሩት የቡድኑ ፖለቲካዊ አመራሮች መካከል አንዱ ሆነው ቆይተዋል።
በጦርነቱ ወቅት የትግራይ ኃይሎችን የተመለከቱ መረጃዎችን ለዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙኃን እና በማኅበራዊ ሚዲያ በትግርኛ፣ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ሲያርቡ፣ ሲወያዩ እና ሲከራከሩ በስፋት ይታወቃሉ።
ከዚህ ባሻገርም ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም ያስቻለው በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል በተደረገው ድርድር ወቅት የትግራይን ወገን በመወከል የተሳተፉ እንዲሁም የፈረሙ አቶ ጌታቸው ረዳ ናቸው።












