በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች የጦር ወንጀሎች መፈጸማቸውን አሜሪካ አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተዛመተው ጦርነት ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች የጦር ወንጀሎች ፈጽመዋል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሷን አሜሪካ አስታወቀች።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ጦር፣ የህወሓት ኃይሎች እና የአማራ ኃይሎች ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት የጦር ወንጀሎች ፈጽመዋል ሲሉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ተናግረዋል።
ብሊንከን ይህንን ያሉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአገራትን የሰብዓዊ መብቶች ይዞታን በተመለከተ የሚያደርገውን ግምገማ ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ በተደረገበት ሰኞ መጋቢት 11/2015 ዓ.ም. ነው።
ከጦር ወንጀሎች በተጨማሪ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ጦር እና የአማራ ኃይሎች ግድያዎችን፣ መድፈር እና አስገዳጅ ስደትን ጨምሮ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ፈጽመዋል ሲሉ ብሊንከን ተናግረዋል።
እንዲሁም የአማራ ኃይሎች አባላት በምዕራብ ትግራይ አስገዳጅ ማፈናቀል እና የዘር ማጽዳት ወንጀል መፈጸማቸውንም ነው ብሊንከን ያሳወቁት።
በቅርቡ ኢትዮጵያን የጎበኙት ብሊንከን “እነዚህ ወንጀሎች ብዙዎቹ በዘፈቀደ ወይም በጦርነት ውስጥ የተከሰቱ ሳይሆን ሆን ተብለው ታስበው የተፈጸሙ ናቸው” ብለዋል።
በደም አፋሳሽ ጦርነቱ የተፈጸሙ ጥሰቶችን በተደጋጋሚ ሲናገሩ የነበሩት ብሊንከን ከዚህ ቀደምም በምዕራብ ትግራይ የዘር ማጽዳት ወንጀል (ኤትኒክ ክሊንሲንግ) መፈጸሙን መናገራቸው ይታወሳል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ያሉትን መረጃዎች መርምሮ ድምዳሜውን እንዳስተላለፈ ያስታወቁት ብሊንከን፣ ይህ ድምዳሜ በአሜሪካ ፖሊሲ ላይ ወዲያውኑ የሚያስከትለው ለውጥ እንደማይኖር ቢገልጹም፣ ወንጀሎቹን የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባም ነው ከፍተኛ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት
“ሁሉም ወገኖች ለፈጸሙት ግፍ እውቅና መስጠት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ወሳኝ እርምጃ ነው። በኃላፊነት ቦታ ላይ የተቀመጡትን ጨምሮ ጥሰቶቹን የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል” በማለት አስረድተዋል።
ባለፈው ዓመትም በጦርነቱ የተፈጸሙ ጥሰቶች የጦር ወንጀሎች እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በጦርነቱ የተፈጸሙ ጥሰቶችን የሚያጣራው የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያ ቡድን ማስታወቁ ይታወሳል።
በዚህ ግኝት ላይ በሰላማዊ ዜጎች ላይ መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ አምርተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንዲሁም በቅርቡ በህወሓት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳሪ እንዲሆኑ ከተመረጡት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር መገናኘታቸውን በዚሁ ዕለት ጠቅሰዋል።
ሁለቱም ወገኖች ግጭትን በዘላቂነት ለመፍታት በደረሱት ስምምነት ላይ እና በአተገባበሩ ላይ ስለደረሱበት ጉልህ መሻሻልም ማመስገናቸውን ጠቅሰዋል።
ብሊንከን እንዳሉት ስምምነቱን ተከትሎ ጦርነቱ እንደቆመ፣ ሰብዓዊ እርዳታ እየገባ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች እየተመለሱ እንደሆነ እንዲሁም የኤርትራ ኃይሎች እየወጡ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።
“ሆኖም ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ሁሉም ወገኖች ለፈጸሟቸው ግፎች እውቅና መስጠት አለባቸው ከዕርቅ ጋር ተጠያቂነት ሊመጣ እንደሚገባም” ከባለሥልጣናቶቹ ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምን ያህል አውዳሚ እንደሆነ የገለጹት ብሊንከን፤ ወንዶች፣ ሴቶችና ህጻናት ተገድለዋል፤ ሴቶች እና ታዳጊዎች አሰቃቂ ወሲባቂ ጥቃቶች ተፈጽሞባቸዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ከቤታቸው ተፈናቅለዋል እንዲሁም በብሔራቸው ተለይተው ኢላማ ተደርገዋል ብለዋል።
ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነቱን ተከትሎ ተፋላሚ ወገኖች ለተፈጸሙ ጥሰቶች ተጠያቂነት ለማስፈን የገቡትን ቁርጠኝነትም በበጎ እንደሚያዩትም ገልጸዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ መንግሥት መጠነ ሰፊ ጥሰት ከተፈጸመባቸው አገራት ተሞክሮን በማጎልበት የሸግግር ፍትህ አማራጭን በማምጣት የመጀመሪያ እርምጃ ወስዷል ብለዋል።
የሽግግር ፍትህ ሁሉን አካታች፣ ተዓማኒ እና በተለይም የተጎጂዎች ደምጽ የሚሰማበት መሆን ያስፈልጋል ያሉት ብሊንከን “ተጠያቂነት፣ እርቅ እና መግባባት ማምጣት በኢትዮጵያ ለዓመታት የቆየውን የጥቃት አዙሪት ለመስበር ቁልፍ ነው” ብለዋል። አሜሪካም በዚህ ሂደት አጋር ትሆናለች ብለዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት ተቀስቅሶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ለቀጠፈው እና በሚሊዮኖች ሕይወት ላይ ከባድ ሰቆቃን ያደረሰው ደም አፋሳሽ ጦርነት ከአራት ወራት በፊት መቆሙ ይታወሳል።
ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ተፈርሟል።
በተያያዘ ዜና የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በጦርነቱ የተፈጸሙ ጥሰቶችን በሚያጣራው የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያ ቡድን ዛሬ መጋቢት 12፣ 2015 ዓ.ም ገለጻ እንደሚቀርብለትም ተጠቅሷል።












