ወደ ሕዳሴ ግድብ ሲጓዙ በፋኖ የታገቱ የደቡብ ኢትዮጵያ ወጣቶች ቤተሰቦች ከፍተኛ ጭንቀት ላይ ነን አሉ

በፋኖ የታገቱ የደቡብ ኢትዮጵያ ወጣቶች

የፎቶው ባለመብት, YT

ከደቡብ ኢትዮጵያ ለጉልበት ሥራ ወደ ሕዳሴ ግድብ ሲያመሩ በአማራ ክልል ውስጥ በታጣቂዎች የታገቱ ወጣቶች ቤተሰቦች ስለ ልጆቻቸው ጉዳይ መፍትሄ የሚሰጣቸው አጥተው ጭንቀት ላይ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለደን ምንጣሮ ወደ ሕዳሴ ግድብ ሲያመሩ በአማራ ክልል ደብረ ማርቆስ አካባቢ በፋኖ ታጣቂዎች ስለመታገታቸው መገለጹ ይታወሳል።

የአካባቢው ፋኖ በበኩሉ እነዚህ ወጣቶችን መያዙን አረጋግጦ፤ እንደሚባለው ለደን ምንጣሮ የሚሄዱ ሳይሆኑ ምልምል ወታደሮች መሆናቸው ብሏል።

ምልምል ወታደሮች ያሏቸው እነዚህ ወጣቶች በጠርናፊ (ወታደራዊ አመራሮች) ታጅበው እንደነበር እና መሪዎቹም ወታደሮች መሆናቸውን ማረጋገጣቸውን አቶ ማርሸት ፀሐይ የአማራ ፋኖ በጎጃም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ወጣቶቹ ከመጡባቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች መካከል አንዷ የሆነችው የአሌ ዞን የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ገኒሴ ገሳቶ፣ ወጣቶቹ ለሥራ እንጂ ለውትድርና የተመለመሉ አይደሉም ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የወጣቶቹ ቤተሰቦች በበኩላቸው ወጣቶቹ ከአካባቢያቸው ጉዞ የጀመሩት ለጉልበት ሥራ መሆኑን ቸምልከተው፣ የመታገታቸው ጉዳይ እጅግ እንዳስጨነቃቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለታጋቹ ደኅንነት ሲባል ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈቀደ አንድ የታጋች ታላቅ ወንድም፤ ዳቦ በመጋገር ይተዳደር የነበረው ወንድሙ ሕይወት “ከብዶኛል በማለት” ስለጉልበት ሥራው መረጃ ከደረሰው በኋላ ጉዞ መጀመሩን ገልጿል።

ይህ ታላቅ ወንድም እንደሚለው ልጁ በታጣቂዎች መያዙ ከታወቀ በኋላ በተለይ በዕድሜ የገፉት ወላጅ አባቱ ከፍተኛ ጭንቀት ላይ ናቸው ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ከተያዘ በኋላ በአጋቾቹ ስልክ ይደውል ነበር። በቀን አንድ ጊዜ ዳቦ እንደሚሰጧቸው ነግሮናል” ይላል ወንድሙ ስላለበት ሁኔታ ሲናገር።

ሌላ የታጋች ቤተሰብ ደግሞ የልጆቹን ዕጣ ፈንታ ለማወቅ እና ድጋፍ ለመጠየቅ ወደ መንግሥት ቢሮዎች ቢሄዱም ምላሽ የሚሰጣቸው አለማግኘታቸውን አመልክቷል።

ይህ የቤተሰብ አባል እንደሚለው በጉዳዩ ላይ ከተፈጠረው ውጥረት የተነሳ ቅጥር እንዲፈጸም አስተባብሯል የሚሉት የአሌ ዞን የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሠራተኞች ከአካባቢው እስከ መሸሽ መድረሳቸውን ይገልጻሉ።

አቶ ማርሸት እነዚህ ወጣቶ በተጨባጭ ወታደራዊ ተመልማዮች መሆናቸውን አረጋግጠናል የሚሉ ሲሆን፣ ለዚህም እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት ከተያዙት ጠርናፊዎች (ወታደራዊ አመራሮች) ጋር የተደረገውን ቃለ መጠይቅ ነው።

“ወታደራዊ አመራሮች መሆናቸውን አምነዋል። ዕዛቸውን፣ ኮራቸውን እና ሌሎች መረጃዎችን ይዘናል። ከእነሱ ነው ምልምል ወታደሮች መሆናቸውን ያረጋገጥነው” ይላሉ።

ሌላኛው የሚጠቅሱት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “ለክልሎች በይፋ የኃይል መዋጮ እንዲያደርጉ ኮታ በማውጣት ደብዳቤ መጻፋቸውን” ነው። እናም እነዚህ ወጣቶች ከደቡብ ክልል የመጡ ወታደራዊ ምልምሎች እንደሆነ አጽንኦት በመስጠት ይናገራሉ።

አቶ ማርሸት ሌላኛው የሚያነሱት ጉዳይ የጉዞ መስመራቸውን ነው። ከዚህ ቀደም ከደቡብ ኢትዮጵያ፣ ከምስራቅ እና ከምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ወደ ህዳሴ ግድብ የሚሄዱ ሰራተኞች ከአዲስ አበባ፣ በአምቦ፣ በነቀምት እና በአሶሳ ተደርጎ ነው ግድቡ ወዳለበት ጉባ የሚደርሱት ይላሉ።

ሆኖም እነዚህ ሰራተኞች “በአማራ ክልል የጦርነት ቀጣና መሆኑ እየታወቀ በጎጃም ማለፋቸውን” በመጥቀስ “ወታደራዊ ምልምል ለመሆናቸው ተጨባጭ ማስረጃ ነው ይላሉ።

የአሌ ዞን የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ገኒሴ ወጣቶቹ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ለሚያርፍበት ቦታ የደን ምንጣሮ ቅጥር ከተፈጸመባቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ሦስት ዞኖች መካከል የአሌ ዞን አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጸ ከሆነ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን እያካሄደ ካለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደን ምንጣሮውን ለማካሄድ ኒኮቲካ ኮንስትራክሽን የተባለ ድርጅት ውል ከያዘ በኋላ በክልሉ ካሉ ሦስት ዞኖች የጉልበት ሠራተኛ ቅጥር እንዲፈጽም ለክልሉ ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

ድርጅቱ የጉልበት ሠራተኞቹን ቀጥሮ ወደ ሕዳሴ ግድብ ሲያጓጉዝ ከታገቱ መካከል 38 የሚሆኑት ወጣቶች ከአሌ ዞን መሆናቸውን አቶ ገኒሴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“እነዚህ ልጆች ከውትድርና ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም። ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 30 ያሉ ናቸው” የሚሉት ኃላፊው ታጋቾቹ በእገታ ላይ ሆነው ወደ ቤተሰብ ስልክ እየደወሉ እንደሆነ ይናገራሉ።

“ስልክ እንዲደውሉ ይፋቅዱላቸዋል። ‘ለመከላከያ የተመለመላችሁ ናችሁ’ እንደሚሏቸው ይናገራሉ። ‘እኛን ለመውጋት ነው የመጣችሁት’ እንደሚሏቸው ይናገራሉ። ለሥራ እየሄዱ እንደሆነ ቢነግሯቸውም አይቀበሏቸውም።”

“ዝርዝር ነገር እንዲናገሩ የሚፈቀድላቸው አይመስለኝም። ሲደውሉ በቂ ምግብ እንደማያገኙ ነገር ግን ደህና መሆናቸውን ብቻ ነው የሚናገሩት” ብለዋል።

ወጣቶቹ ወደ ቤኒሻንጉል የሚጉዙት ለጉልበት ሥራ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ ቢይዙም የያዙት ሠነድ ከእገታ እንዳላስጣላቸው ኃላፊው ይገልጻሉ።

“የይለፍ ደብዳቤ ይዘዋል። ለሥራ እንደሚሄዱ ወረቀት አላቸው። ከቀጣሪው ጋር የገቡት ስንት እንደሚከፈላቸው፣ ቀለብ እና ሥራ ሁኔታቸውን ሁሉ የሚገልጽ የሥራ ውል ይዘዋል። ስማቸው እና የስልክ ቁጥራቸው፣ ችግር ቢደርስ ተጠሪ ያለበት ዝርዝር መረጃ ይዘዋል” ይላሉ።

“እነዚህ ልጆች ሰላማዊ፤ ለሥራ የሚሄዱ ናቸው። ከውትድርና ጋር ፈጽሞ የሚያገናኛቸው ነገር የለም” ካሉ በኋላ፣ ከወጣቶቹ በተጨማሪ ከቀጣሪ ድርጅቱ አስተባባሪ የሆኑ አራት ግለሰቦች አብረው ስለመታገታቸው ከድርጅቱ መስማታቸውን አቶ ገኒሴ ጨምረው አስረድተዋል።

የወጣቶቹ እገታ ከተሰማ በኋላ ከቤተሰብ ተደጋጋሚ ጥያቄ እየቀረባለቸውን መሆኑንም ይናገራሉ።

“ቤተሰብ በጣም እያጨናነቀን ነው። ይሄ ከእኛ አቅም በላይ ሆኗል። በክልል ደረጃ ኮሚቴ ተደራጅቶ ወደ አማራ ክልል ሄዷል። ወደ ቀጣሪ ድርጅቱም ሄዷል። ከፌደራል መንግሥት ጋርም ንግግር እየተደረገ ነው።”

አቶ ማርሸት በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ለህዳሴው ግድብ የጉልበት ሰራተኛም ሆነ ሰራተኛ የሚጓጓዘው ባህርዳርና አሶሳን ጨምሮ በየተለያዩ ከተሞች ጽህፈት ቤት ባለው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ጽህፈት ቤት አማካኝነት እንደሆነ በመጥቀስም እነዚህ ሰራተኞች በዚያ በኩል የመጡ አይደለም ይላሉ።

ቢቢሲ ቤተሰቦቻቸውን ማናገሩን፣ ወጣቶቹ የይለፍ ወረቀት ይዘው እንደሆነም በመጥቀስ የሆነ ስህተት ተፈጽሞ ይሆን ብሎ ለፋኖ አመራር ላቀረበላቸው ጥያቄ ምልመላ በማሳሳት እየተፈጸመ ነው ብለዋል።

“ሥርዓቱ ወጣቶችን በውጭ አገራት የጉዞ ወኪሎች፣ በካድሬ እና የካድሬ ቤተሰቦች፣ በግንባታ ድርጅቶች፣ በአስጎብኚ ድርጅቶች፣ በትራንስፖርት ማኅበራት ኤጀንሲዎች፣ በእርሻ ሥራ በተሰማሩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች አማካኝነት ነው ወታደራዊ ምልመላ የሚያካሂደው” ብለዋል።

አክለውም "ወጣቶች ከአስር ሺህ ብር ጀምሮ በከፍተኛ ገንዘብ እስከ 30 ሺህ ብር በወር እንደሚከፈላቸው ተደርጎ ተታለው ይወሰዱና መዳረሻቸው. . . ወታደራዊ ማሠልጠኛዎች ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ስለዚህ ልጆቹ በዚህ መንገድ ተታልለው ለሥራ ተወስደዋል? ወይስ ልጆቹ ለውትድር መመልመላቸውን ያውቃሉ? በሚል ቢቢሰሲ አቶ ማርሸትን የጠየቃቸው ሲሆን፣ እሳቸውም “ጠርናፊዎቹ ዓላማውን ያውቃሉ፤ የተታለሉ እንዳሉ ሁሉ ለወታደራዊ ምልመላ የመጡ አሉ” ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል።

ከዚህ ቀደምም ከአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ ኃይሎች ለሥልጠና ወደ ብር ሸለቆ እና ጊታ የተሰኙ ማሠልጠኛዎች ሲሄዱ ይዘዋቸው እንደነበረም ገልጸዋል። ከእነዚህም ውስጥ ግማሾቹ “በደፈጣ ጥቃት ሲደመሰሱ፣ አብዛኛዎቹ ግን የተሃድሶ ሥልጠና ሰጥተን ወደ ቤታቸው መልሰናቸዋል” ብለዋል።

የወጣቶቹን ዕጣ ፈንታ በተመለከተም “የላካቸው ክልል ሃቁን አምኖ የላኳቸው ለወታደራዊ ምልመላ ነው ካለ ገንዘባቸውን ሰጥተን እንልካቸዋለን። በዚህ ማጭበርበር የሚቀጥል ከሆነ ግን ረዥም ጊዜ የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ምናልባትም ፋኖን ይቀላቀላሉ ወይም እንደ ምርጫቸው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የወጣቶቹን እገታ በተመለከተ ከቀጣሪው ኒኮቲካ ኮንስትራክሽን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ቢቢሲ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።