የቀድሞው ወንጀለኛ፤ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ መንሰራፋት እና የኬንያ ፖሊስ ጭንቀት

ሽጉጥ ጉልበቱ ላይ ያስቀመጠ ግለሰብ

እየጨመረ በመጣ አመፅና ወንጀል እየተናጠች በምትገኘው ኬንያ አንድ የቀድሞ ወንጀለኛ ወንበዴዎች ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያቸውን እንዲያስረክቡ በመማፀን ላይ ይገኛል።

ቢቢሲ አፍሪካ አይ የተሰኘው የምርመራ ዘገባ ቡድን ግለሰቡን ተከትሎ ይህንን አቀናብሯል።

"በጣም አስከፊ ያደረግሁት ነገር ቢኖር የሰው ነብስ ማጥፋት ነው። አንድ ሰው ገድያለሁ" ይላል ማንነቱ እንዳይገለጥ የጠየቀው ወጣት።

"በወቅቱ ምንም አልተሰማኝም። ምክንያቱም በዕፅ ደንዝዤ ነበር። አንድ ዝንብ የገደልኩ ያክል ነበር የተሰማኝ።"

ሳሙኤል [ትክክለኛ ስሙ አይደለም] ቪክቶሪያ ሐይቅ አጠገብ በምትገኘው ምዕራብ ኬንያዊቷ ኪሱሙ የተገኘው ኪንግ ካፉ የተባለውን ሰዎች ከወንጀል እንዲርቁ እየመከረ የሚገኘውን የቀድሞ ወንጀለኛ ለማግኘት ነው።

ትንሽ የተሸበረ ይመስላል። ኤኬ47 መሣሪያ ከደበቀበት ቦታ አውጥቶ ለፖሊስ ለማስረከብ ቆርጦ ተነስቷል።

ለምን ይህን ማድረግ መረጥክ ተብሎ ሲጠየቅ "አንድ ቀን ቤተሰቦቼ የሚበላ የሚያጡበት ቀን ይመጣል። መቀጣታቸው የሚቀር አይደለም" ይላል።

"አሁን ቀብጬ ሄጄ የማይሆን ነገር የማደርግ ከሆነ በጥይት ብለው ይጥሉኛል፤ የዛኔ ደፋ ቀና ብሎ ቤተሰቤን የሚቀልብ ሰው አላገኘም። ለዚህ ነው ይህን ነገር መመለስ አለብኝ ብዬ የወሰንኩት።"

የኬንያ ብሔራዊ የስታትስቲክስ ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው ባለፈው ዓመት ብቻ በሀገሪቱ አመፅ እና ስርቆት 20 በመቶ ጨምሯል።

ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎች በድንበር በኩል እንደልብ የሚገቡ ሲሆን የጦር መሣሪያ የታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ኢንስቲትዩት ኦፍ ሴኪዩሪቲ ስተዲስ የተባለው ተቋም ይናገራል።

ስሞል አርምስ ሰርቬይ የተባለው ዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር ተቋም እንደሚለው 750 ሺህ የጦር መሣሪያዎች በሰላማዊ ኬንያዊያን ዜጎች ዘንድ ይገኛሉ። ይህ ቁጥር ከጦር ሠራዊቱ እና ፖሊስ ቁጥር በላይ ነው።

ካፉ የጦር መሣሪያ መመለስ በሚፈልጉ ሰዎች እና በፖሊስ መካከል ሆኖ ያገለግላል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ወንጀል ሲሰራ 15 ዓመቱ ነበር። ከሰዎች እጅ ቦርሳ ነጥቆ በመሮጥ ነው ወደ ስርቆት የገባው። ቀጥሎ የጦር መሣሪያ ታጥቆ መዝረፍ ጀመረ።

በአውሮፓውያኑ 2003 ለፈፀመው የዘረፋ ወንጀል የ4 ዓመታት ፍርድ ተከናነበ።

ሳሙኤል፤ ካፉን በኢንስታግራም ገፁ አግኝቶት አግዘኝ ሲል ተማፅኖታል። ካፉ፤ ኪሱሙ ለሚገኙ የፖሊስ መኮንኖች ጥቆማ አድርጎ ሳሙኤል የጦር መሣሪያውን ለመቀበል ተስማሙ። በተደረገለት ይቅርታ መሠረት ምንም ዓይነት ምርመራ አይከፈትበትም።

ነገር ግን ኤኬ47 የጦር መሣሪያውን ይዞ መገኘት ባለበት ቀን ሳሙኤል ደብዛው ጠፋ።

የ40 ዓመቱ ካፉ ጌቶ ሬዲዮ በተሰኘው ጣቢያ የሬድዮ ፕሮግራም አቅራቢ ነው። ይህ ጣቢያ በተለይ ደካማ የሕብረተሰቡ ክፍል በሚኖርባቸው የመዲናዋ ሥፍራዎች ዘንድ ተወዳጅ ነው። ካፉ የሬዲዮ ፕሮግራሙን ተጠቅሞ የጦር መሣሪያን አስከፊነት ይሰብካል።

"ልክ ስለቀቅ ነው አብዛኛዎቹ በዚህ ሕይወት ያገኘኋቸው ሰዎች መጨረሻቸው አስከፊ እንደሆነ የገባኝ። አብዛኛዎቹ መጨረሻዎቹ የትም ሞቶ መገኘት ነው" ይላል።

"ማንም ሰው ሌባ ሆኖ አልተወለደም። ወጣቱ ሥራ ባይኖረው እንኳ ወንጀል አማራጭ ሊሆን አይገባም እያልን ነው። ሰዎች የያዙትን ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ለፖሊስ እንዲያስረክቡ እየመከርን ነው" ይላል።

የኬንያ መንግሥት ባለፉት 20 ዓመታት ታጣቂዎች የሚፈፅሙትን ወንጀል ለመቆጣጠር በሚል የጦር መሣሪያዎችን ለሚመልሱ ሰዎች ይቅርታ ሲያደርግ ቆይቷል።

በዚህ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ የጦር መሣሪያዎች የተመለሱ ቢሆንም ይህ ከጠቅላላው ቁጥር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ካፉ የጦር መሣሪያ መመለስ በሚፈልጉ ሰዎች እና በፖሊስ መካከል ሆኖ ያገለግላል
የምስሉ መግለጫ, ካፉ የጦር መሣሪያ መመለስ በሚፈልጉ ሰዎች እና በፖሊስ መካከል ሆኖ ያገለግላል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኬንያ ውስጥ የጦር መሣሪያ ማግኘት እጅግ ቀላል ነው ይላል አንድ ወንጀለኛ። በ40 ሺህ ሺልንግ [300 ዶላር ገደማ] መግዛት እንደሚቻል ለቢቢሲ አፍሪካ አይ ይናገራል።

ካፉ እንደሚለው የጦር መሣሪያቸውን ለፖሊስ መልሰው የሚያስረክቡ ሰዎች ዒላማ እንሆናለን የሚል ስጋት አላቸው።

የኬንያ ፖሊስ ከሕግ ውጭ ግድያ በመፈፀም በተደጋጋሚ ይወቀሳል። ሚሲንግ ቮይስስ የተሰኘው የኬንያ የተራድዖ ድርጅት ባለፉት አምስት ዓመት 800 ሰዎች ከሕግ-ውጭ በፖሊስ ተገድለዋል ይላል። አብዛኛዎቹ ደሀ ወጣቶች ናቸው።

ቢቢሲ አፍሪካ አይ ከካፉ ጋር ናይሮቢ ውስጥ አንድ የጦር መሣሪያውን ለመመለስ የወሰነ ሰው ለማግኘት አቀና። ጆን ስንል እንጠራዋለን።

"ለመመለስ ዝግጁ ነኝ። ሄደህ አንድ ሰው ትገድላለህ። ለዚህ ድርጊትህ በሶስት ወራት ውስጥ ገንዘብ ታገኛለህ። ነገር ግን የገደልከው ሰው ደም እጅህ ላይ አለ። ከዚያ የወንጀለኝነት ስሜት እየተሰማህ ትኖራለህ። ይህ ሕይወት በጣም ከባድ ነው።"

ጆን በጣም የሚፈራው ነገር የጦር መሣሪያ ለመመለስ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲሄድ የሆነ ነገር ያጋጥመኛል የሚለው ስሜት ነው።

አንድ ጓደኛው ሁለት የጦር መሣሪያ ለማስረከብ ሐሳብ እንዳለው ለሆነ ሰው ተናግሮ በነጋታው የፖሊስ መኪና መጥቶ ጭኖ እንደወሰደው እና በሳምንቱ የሬሳ ማስቀመጫ ክፍል እንደተገኘ ይናገራል።

"ችግሩ ማንን አምናለሁ፤ እንዴት ነው የማስረክበው" የሚለው ነው ይላል።

የኬንያ ፖሊስ የጦር መሣሪያ እና ቀለሀ ለወንጀለኛ ቡድኖች ያከራያሉ እንዲሁም ይሸጣሉ የሚለው ወሬ ከተስፋፋ ቆይቷል። ቢቢሲ አፍሪካ አይ ይህን ጥያቄ ለፖሊስ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።

ካፉ የአካባቢው የፖሊስ ኃላፊ አግኝቶ ግለሰቡ የጦር መሣሪያ መመለስ እንደሚፈልግ ካስረዳ ከጥቂት ቀናት በኋላ አብረው ሄደው አስረክበው ተመልሰዋል።

የፖሊስ መኮንኑ የጦር መሣሪያውን መለያ ቁጥር ሲያጣራ ኬፒ የሚል ፅሑፍ ይመለከታል። ኬፒ በምሕፃሩ ኬንያን ፖሊስ ማለት ነው።

ፖሊስ የጦር መሣሪያዎች መመለሳቸውን በማስመልከት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኘው ካፉ ሰዎች መሣሪያቸውን መመለስ ከፈለጉ ሊተባበራቸው ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

"መንግሥት ወጣቱን በግልፅ ሊያናግረው ይገባል። መሣሪያቸውን ሲመልሱ እንዲጠፉ ይደረጋል ወይስ ድጋፍ ይሰጣቸዋል? እኔ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ነው የምጠይቀው። እኒህ ወጣቶች ፍቅር ያሻቸዋል።"

እርግጥ ነው ይህ ብቻ ኬንያ ውስጥ የተንሰራፋውን ወንጀል ይገታል ማለት ከባድ ነው። ነገር ካፉ ይህ አንድ እርምጃ ነው ይላል። ወንጀለኞች ያምኑታል። ተጨማሪ ሰዎች የጦር መሣሪያቸውን እንዲያስረክቡ ለማሳመን እየሞከረም ይገኛል።