የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ‘ቫግነር’ መሪው ከሞተ በኋላ ታጣቂዎቹ የት ደረሱ?

የቫግነር ተዋጊዎች በየቭገኒ ፕሪጎዢን መቃብር አቅራቢያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቫግነር ተዋጊዎች በየቭገኒ ፕሪጎዢን መቃብር አቅራቢያ

ከአንድ ዓመት በፊት በአይነኬው የሩሲያው ፕሬዚዳንት ላይ አመጽ በማስነሳት ለሰዓታት የቆየ ፈተና ደቅኖ የነበረው ቅጥረኛው ተዋጊ ቡድን ቫግነር መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ከሞተ አንድ ዓመት ሆነው።

በዩክሬን፣ በሶሪያ እና በምዕራብ አፍሪካ ቅጥረኛ ተዋጊዎችን በማሰማራት የእንቅስቃሴ አድማሱን አስፋፍቶ የነበረው ቫግነር ከመሪው ፕሪጎዢን ህልፈተ ሕይወት በኋላ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ግልጽ አይደለም።

ቢቢሲ የቡድኑን የቀድሞ ተዋጊዎች እና ከቫግነር ጋር ቅርበት ያላቸውን ሰዎች በማናገር ለጥቂት ሰዓታት ከቆየው አመጹ በኋላ በአውሮፕላን አደጋ በድንገተኛ ሁኔታ ሕይወቱ ያለፈው መሪው ከሞተ በኋላ ቡድኑ ስላለበት ሁኔታ ቃኝቷል።

ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ አንድ ሰውነቱ ፈርጠም ያለ እና ሰማያዊ ዐይን ያለው ወጣት በኢስታንቡል ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ መጠበቂያ ስፍራ ላይ ነበር።

ፈርጣማው ወጣት ጭንቅላቱን አረቦች በተለይም ፍልስጤማውያን ጭንቅላታቸውን በሚሸፍኑበት ባህላዊው ካፊያ ሸብ አድርጎታል። ለሥራ ወደ ሊቢያዋ ሆዲ ከተማ እያቀና ነበር።

ወጣቱ የቫግነር ተዋጊ ነው።

በፕሪጎዢን የተመሠረተው እና ይመራ የነበረው ቫግነር እጁ ረዥም ነው ይባላል።

በቢሊዮኖች ዶላር የሚያወጡ ኩባንያዎች እና ፕሮጀክቶችን በሶሪያ፣ በማሊ፣ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በሱዳን እና በሊቢያ ያንቀሳቅስ ነበር።

ተዋጊዎቹም ሩሲያ ዩክሬንን በወረረችበት ወቅት ቁልፍ ሚናን ተጫውተዋል።

የዩክሬን ወረራ በተፈጸመባቸው ወራት የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የመከላከያ ሚኒስቴር በዩክሬን ውስጥ 50 ሺህ የሚገመቱ የቫግነር ቅጥረኞች እንዳሉ አስታውቆ ነበር።

ነገር ግን ወደ 20 ሺህ የሚጠጉት አብዛኞቹ የቀድሞ እስረኞች የዩክሬን አነስተኛ ግዛት የሆነችው ባኽሙትን ለመያዝ በተደረገው ፍልሚያ ወቅት መሞታቸውን የቢቢሲ የሩሲያ ቋንቋ አገልግሎት ያገኘው ዝርዝር መረጃ ያሳያል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር የጥይት እጥረት ፈጥሯል በሚል ፕሪጎዢን ቀሪዎቹን ተዋጊዎች ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ከጦርነት ግንባር እንዲወጡ አድርጎ ነበር።

ይህ ከፊያ ለብሶ በኢስታንቡል አየር ማረፊያ የታየው ወጣት ከዩክሬን የጥይት ጭረት እንኳን ሳያገኘው ነበር የወጣው።

ከዩክሬን ከወጣ በቀጣዩ ወር “ዘመቻ ለፍትሕ” የተባለ ኦፐሬሽንን እንዲቀላቀል በቴሌግራም የጥሪ መልዕክት ደረሰው።

የቫግነር ተዋጊዎች በዩክሬን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የቫግነር ተዋጊዎች በዩክሬን
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ደቡባዊቷን የሩሲያ ከተማ ሮስቶቭ ኦንዶንን በመቆጣጠር በፕሬዚዳንት ፑቲን ላይ አመጽ በማስነሳት ዓለምን ካስደነገጡት የቫግነር ታጣቂዎች መካከል ወጣቱ አንዱ ሆነ።

ታጣቂው ወጣት ፕሪጎዢንን ለመጨረሻ ጊዜ ያየው በዚያ ወቅት ነበር። ፕሪጎዢን መኪና ወስጥ ገብቶ ሰልፊ ፎቶ ተነስቶ ከተማዋን ለቆ ወጣ።

ቫግነር ታጣቂዎቼን ይዤ ወደ ዋና ከተማዋ ሞስኮ እገሰግሳለሁ ያለውን ዛቻ ተወው። ፕሬዚዳንት ፑቲን የቫግነር ተዋጊዎች ከሩሲያ ጦር ጋር እንዲቀላቀሉ ወይም ከፕሪጎዢን ጋር ወደ ቤላሩስ እንዲሄዱ መፍቀዳቸውን ተከትሎ ስምምነት ላይ ተደረሰ።

ይህ ስምምነት ሲደረስ ነበር ባለ ከፊያው ፈርጣማው ወጣት የቫግነር ቅጥረኛነቱ እንዳከተመ የተረዳው።

“ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ አንዳንዶች ቤላሩስ፣ ሌሎች ደግሞ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ አሰቡ። ብዙም እርግጠኛ ያልነበረ እና ያልጠራ ሁኔታ ስላልነበር ለእኔ እንደማይሆን ወሰንኩ” ይላል ቅጥረኛው ተዋጊ።

ስምምነቱ ከተደረሰ ከሁለት ወራት በኋላ ነሐሴ አጋማሽ ላይ ፕሪጎዢንን የጫነ የግል ጄት ከሞስኮ በስተሰሜን ተከስክሶ እሱ እና ሌሎች በርካታ የቫግነር አመራሮች ተገደሉ። ከግድያው በስተጀርባ የክሬምሊን ባለሥልጣናት አሉበት ቢባልም ይህንን አስተባብለዋል። ነገር ግን የቫግነር ታጣቂዎች ይህንን አይቀበሉትም።

“ሰውየውን [ፕሪጎዢንን] ሲገድሉት ሩሲያ ውስጥ የቀረኝ ነገር እንደሌለ ተረዳሁ” ይላል።

ወጣቱ ያሉትን አማራጮች እያየ በነበረበት ወቅት በተለያዩ አገራት ውስጥ ያሉ የቫግነር ቡድን ንብረቶች በሩሲያ መንግሥት እና ጦር ቁጥጥር ስር እየገቡ መሆናቸውን ተመለከተ።

ወጣቱ ፓስፖርት፣ የቆጠባት ገንዘብ እንዲሁም የውጊያ ልምድ አለው። ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ቀደም ሲል ተዋግቶ ወደነበረባት ወደ ሶሪያ ለመብረር ወሰነ።

በሶሪያ የሚገኙ ቅጥረኛ ወታደሮች ከሩሲያ ጦር ውል እንደተሰጣቸው ሁለት ምንጮች ለቢቢሲ ሩሲያ አገልግሎት ተናግረዋል።

የቫግነር መሰራች እና መሪ የቭገኒ ፕሪጎዢን

የፎቶው ባለመብት, WAGNER TELEGRAM ACCOUNT / GETTY

የምስሉ መግለጫ, የቫግነር መሥራች እና መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን

ሶሪያ የደረሰው ወጣት ምርጫው በሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ስር ሆኖ መዋጋት ወይም ቁጭ ማለት ብቻ ነበር።

ይህንን ውል መፈረም ስላልፈለገም ለሁለት ወራት ያህል ሥራ ፈትቶ ተቀመጠ። ነገር ግን ክፍያው አልተቋረጠበትም። ከዚያም አፍሪካ ውስጥ ሥራ ለመፈለግ የወሰነ ሲሆን፣ ይህንንም ማንም አልተቃመውም።

በተመሳሳይ ወቅት የሩሲያ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ዩኒስ ቤክ ወደ ሰሜን እና ምዕራብ አፍሪካ አቀኑ።

ሚኒስትሩ ከሩሲያ ወታደራዊ መረጃ አገልግሎት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ሆነው ቫግነር ሲንቀሳቀስባቸው የነበሩ አገራትን ሊቢያን፣ ቡርኪናፋሶን፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክን፣ ማሊን እንዲሁም ኒጀርን ጎበኙ።

ምክትል የመከላከያ ሚኒስሩ “ከቫግነር ጋር የተደረጉ ስምምነቶች ይከበራሉ” ነገር ግን ስምምነቶች የሚፈጸሙት “በቀጥታ ከሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ጋር ይሆናል” የሚል መልዕክት ማስተላለፋቸውን በዩናይትድ ኪንግደም ተቀማጭነቱን ያደረገው የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት የምርምር ቡድን (ሩሲ) ገልጿል።

በአፍሪካ የሚገኙ አንዳንድ የቀድሞ የቫግነር ኃይል አባላት በአሁኑ ወቅት አማጺያንን እየተፋለሙ ላሉ አንዳንድ አገራት ወታደራዊ ድጋፍ እየሰጡ ይገኛሉ።

በምላሹም ታጣቂዎቹ ስትራጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብቶችን ያገኛሉ። በቅርቡ ወታደሮች ሥልጣን የተቆጣጠረባቸው ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ ከቀድሞ ቅኝ ገዢያቸው ፈረንሳይ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማቋረጥ ከሩሲያ ጋር ቅርበት ፈጥረዋል።

የምርምር ቡድኑ ያወጣው ሪፖርት ሩሲያ ሊቲየም፣ ወርቅ እና ዩራኒየም ባሉ ማዕድናት ላይ ፍላጎት እንዳላት ገልጿል።

የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር “አፍሪካን ኮርፕስ” (የአፍሪካ ጦር ክፍል) የምልመላ ማስታወቂያዎች በዘንድሮው ዓመት ታኅሣሥ ወር ላይ ታይተዋል።

ባለ ከፍያው ወጣት በኋላ ላይ ያሰበው የአፍሪካ አገር ውስጥ እንደደረሰ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ቅጥረኝነትን እንደማንኛውም ሥራ የሚመለከተው ይህ ወጣት፤ ከዩክሬን እና ከቤላሩስ በተሻለ የወደፊቱ በአፍሪካ ውስጥ ብሩህ መሆኑን ተናግሯል።

ካርታ

አብዛኞቹ የቀድሞ ታጣቂ አጋሮቹ በሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ አዲስ በተቋቋሙ የጦር ክፍሎች ውስጥ እያገለገሉ እንደሆነ ያስረዳል።

ይሁን እንጂ ከየቭጌኒ ፕሪጎዢን ጋር ግንኙነት የነበራቸው አንድ ምንጭ ልጁ ፓቬል፣ በቫግነር ላይ የተወሰነ ቁጥጥር እንዳለው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ሞስኮ ከሩሲያ ጥቅም ጋር በማይጋጭ ሁኔታ ተተኪው በአፍሪካ ውስጥ የአባቱን ሥራ እንዲቀጥል ፈቅዳለች” ሲሉ ምንጩ ገልጸዋል።

በ20ዎቹ መጨረሻ ላይ ያለው ፓቬል በሩሲያ ብሔራዊ ጥበቃ፣ ሮስግቫርዲያ ስር ያለውን የቫግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን መምራቱን አስመልክቶ አንዳንድ መላምቶች ነበሩ።

የሩሲ ሪፖርት እንደሚያመለክተው የቫግነር ጉዳይ በብሔራዊ ወታደራዊ መረጃ አገልግሎት እና በብሔራዊ ጥበቃ አመራሮች መካከል ፉክክር አስነስቷል።

የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ቫግነር በብሔራዊ ጥበቃ፣ ሮስግቫርዲያ ስር መካተቱን እና አባላቱ ምናልባትም ወደ ዩክሬን እና አፍሪካ ተሠማርተው ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

የፕሪጎዢን ልጅ ፓቬል በቡድኑ ላይ ስላለው ሚና ምንም ዓይነት ይፋዊ መግለጫ ያልተሰጠ ሲሆን፣ ቢቢሲም ይህንን አስመልክቶ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

የቫግነር ይፋዊ የቴሌግራም ቻናል አሁንም ባልተገለጹ ሩቅ አካባቢዎች የምልመላ ማስታወቂያዎችን ይለጥፋል። ሆኖም የቫግነር ተዋጊዎች የት እንዳሉ እና በማን እንደተቀጠሩ ያለው መረጃ አናሳ ነው።

ለሩሲያ በቫግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ሽፋንን በመጠቀም ዓለም አቀፋዊ ዓላማዋን ማሳካት እንድትችል፣ ሊጣልባት የሚችለውን ማዕቀብ ማስወገድ እንዲሁም ተሳትፎዋን እንድትክድ አስችሏታል።

የቫግነር ተዋጊዎች አመጽ ባስነሱበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንዳንድ የቀድሞ የቫግነር ተዋጊዎች የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴርን ጥሪ በጥርጣሬ ዐይን ነው የሚያዩት ወይም አይቀበሉትም።

ቢቢሲ ከቀድሞ የቫግነር ተዋጊዎች ጋር ባደረገው ውይይት አብዛኞቹ አባላት ቡርኪናፋሶን ጨምሮ በአፍሪካ ለመቆየት መወሰናቸውን ተረድቷል። ሌላኛው መዳረሻቸው የሚሆነው ደቡብ ሩሲያ፣ ቼቼኒያ ግዛት ነው።

የቼቼን መሪ ራምዛን ካዲሮቭ 3 ሺህ የሚሆኑት ተዋጊዎች የጦሩን የአክማት ልዩ ኃይል ቡድን ይቀላቀላሉ ሲሉ ከወራት በፊት መናገራቸውን የሩሲያ መንግሥታዊው የዜና ወኪል ታስ ዘግቧል።

ታዋቂው የቫግነር አመራር አሌክሳንደር ኩዝኔትሶች ወይም በቅጽል ስሙ ራቲቦር ከቼቼን መሪው ጋር ቀርቦ ለቀድሞ ጓዶቹ ባስተላለፈው መልዕክት “ሁሉም ነገር በቫግነር ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ነው። አንድ ነው። አሠራራችን ላይ የሚቀየር ነገር አይኖርም። ምንም አይለወጥም” ብሎ ነበር።

ከሦስት ሺዎቹ ውስጥ ምን ያህሉ እንደመጡ ቢቢሲ ማረጋገጥ አልቻለም።

ከፑቲን ጋር በመጀመሪያ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ወደ ቤላሩስ እንዲሄዱ በቀረበላቸው ጥሪ በአሁኑ ወቅት ከ100 ያነሱ ተዋጊዎች የአገሪቱን ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ኃይሎችን በማሠልጠን ላይ እንዳሉ የአገሪቱ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን የሚቆጣጣረው ቤላሩስኪ ሃጂን የተሰኘው የምርምር ተቋም አስታውቋል።

በኒጀር ፈረንሳይ እንድትወጣ እና ለሩሲያ የተደረገ የድጋፍ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኒጀር ፈረንሳይ እንድትወጣ እና ለሩሲያ የተደረገ የድጋፍ ሰልፍ

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በማሊ የቀድሞ ቫግነር ተዋጊዎች መገኘት አርዕሰ ዜና ሆኖ ነበር።

በአገሪቱ ያሉት የቱዋሬግ ተገንጣይ አማጺያን እና እስላማዊ ተዋጊዎች በቫግነር ተዋጊዎች እና በማሊ ጦር ላይ የደፈጣ ጥቃት መፈጻማቸውን ዘገባዎች አስነብበዋል።

የቫግነር ይፋዊ የቴሌግራም ቻናል አንድ አዛዥን ጨምሮ አንዳንድ ተዋጊዎቹ መገደላቸውን ቢጠቅስም ምን ያህል እንደሆኑ ቁጥራቸውን አልጠቀሰም።

የሩሲያ ጦር ደጋፊ የቴሌግራም ቻናሎች በበኩላቸው በርካታ የቀድሞ የቫግነር ተዋጊዎች መሞታቸውን የዘገቡ ሲሆን፣ ይህም በአህጉሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አባላቱ የሞቱበት ስፍራ አድርጎታል።

ቅጥረኞቹ የሩሲያ ኮርፕስ አባላት እንደነበሩ ቢታወቅም የጦር ክፍሉም ሆነ የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ምንም ዓይነት ይፋዊ አስተያየት አልሰጡም።

ባለ ከፍያው ፈርጣማው ወጣት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቢቢሲ ለሚልክለት መልዕክቶች ምላሽ አልሰጠም። ሆኖም በእናቱ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ የሐዘን መግለጫ የሻማ ፎቶ ተለጥፎ ታይቷል።