አፕል በኮንጎ ታጣቂዎች ከሚቆጣጠሯቸው ቦታዎች ማዕድናትን በመጠቀም ተከሰሰ

ማዕድን የሚያወጣ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ታጣቂዎች ከሚቆጣጠሯቸው ቦታዎች ማዕድናትን በመጠቀም በሚፈጸሙ ጥሰቶች ተባባሪ ሆኗል የሚል ክስ ቀረበበት።

ክሱን ያቀረበው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥት በፈረንሳይ እና ቤልጂየም ነው።

የኮንጎን መንግሥት በመወከል ክሱን ያቀረቡት ጠበቆች አፕል ኩባንያ በምስራቅ ኮንጎ አንዳንድ ማዕድን ማውጫን የሚቆጣጠሩ ታጣቂዎች በሚፈጽሙት ወንጀል ተባባሪ ሆኗል ሲሉ ይከራከራሉ።

ኩባንያው በበኩሉ የቀረበበትን ክስ በጽኑ ውድቅ አድርጎ ማዕድናቱን የሚያገኝበት መንገድ ኃላፊነት በተሞላው መልኩ ከትክክለኛ ምንጮች ነው ብሏል።

የፈረንሳይ እና ቤልጂየም ባለስልጣናት ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይቻላል ወይ የሚለውን ለመወሰን በቂ ማስረጃዎች መኖሩን የሚመለከቱ ይሆናል።

የአፕል አቅርቦት ሰንሰለት "በደም ማዕድናት" መበከሉን የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠበቆች በሰጡት መግለጫ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ጠበቆቹ እንደሚሉት ከሆነ ቆርቆሮ፣ ታንታለም እና ቱንግስተን የተባሉትን ማዕድናት ከኮንጎ የግጭት አካባቢዎች ተወስደው "በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ዝውውር" ላይ እየተቸበቸቡ ነው።

"እነዚህ ተግባራት ሚሊሻዎች እና የሽብር ቡድኖችን በገንዘብ በመደገፍ የግጭት አዙሪት እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም ለግዳጅ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ እና የአካባቢ ውድመት አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው" ብለዋል።

አፕል በበኩሉ የማዕድናቱ አቅራቢዎች በኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው እንደሆነ በመግለጽ ክሱን አልተቀበለውም።

የኩባንያው ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት " በዚህ ዓመት መጀመሪያ በአካባቢው ያለው ጦርነት ተባብሶ በቀጠለበት ወቅት አቅራቢዎቻችንን እና ማዕድን አጣሪዎቻችንን ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ከሩዋንዳ የሚመጡ ቆርቆሮ፣ ታንታለም፣ ቱንግስተን እና ወርቅን ማገድ እንዳለባቸው አሳውቀናቸዋል" ብለዋል።

"ይህንን እርምጃ የወሰድነው ነጻ ኦዲተሮች ወይም የኢንዱስትሪ ማረጋገጫ ዘዴዎች አስፈላጊውን መስፈርቶች አሟልተዋል የሚለውን ለማጣራት ፈታኝ ስለሆነ ነው" ብለዋል።

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቃዊ ክፍል የዓለማችን የማዕድናት መገኛ ዋነኛ ምንጭ ነው። የዓለም አቀፉ የማዕድናትን መቀራመት ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ ኮንጎን ለአስር ዓመታት ያህል የጦርነቶች ቀጣና አደርጓታል።

የመብት ተሟጋቾች ከፍተኛ መጠን ያላቸው ማዕድናት ከህጋዊ አውጭዎች እንዲሁም የታጣቂ ኃይሎች ከሚቆጣጠሯቸው ማዕከላት ወደ ጎረቤት ሩዋንዳ ተዘዋውረው በትልልቅ ኩባንያዎች አማካኝነት በስልኮቻችን እና ኮምፒውተሮቻችን እንደሚገኙ ሲያሳውቁ ቆይተዋል።

ሩዋንዳ ከዚህ ቀደም የኮንጎ መንግሥት በአፕል ላይ የጀመረውን ህጋዊ እርምጃ የሚዲያን ቀልብ ለመሳብ ነው ስትል ስታጣጥል ቆይታለች።

ምንም አይነት የግጭት ማዕድናትን ለቴክኖሎጂ ኩባንያው አልሸጥም ስትል ውድቅ አድርጋለች።