የጀርመን ፖሊስ በጎን ኮኬይን እያቀረበ ነው ያለውን የፒዛ ሬስቶራንት ወረረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጀርመን ፖሊስ ለደንበኞቹ ከፒዛ ጋር በጎን ኮኬይን እያቀረበ ነው ያለውን የፒዛ ሬስቶራንት ወረረ።
ደንበኞቹ በሬስቶራቱ የምግብ ዝርዝር ላይ 40ኛውን ቁጥር ሲያዙ በጎን ኮኬይን የተሰኘውን አደንዛዥ ዕጽ ይቀርብላቸዋል ተብሏል።
ባለስልጣናቱ ይህንን በተመለከተ ከምግብ ተቆጣጣሪዎች በተሰጣቸው ጥቆማ መሰረት የአደንዛዥ ዕጽ መኮንኖች ሬስቶራንቱን ሲከታተሉት እንደነበር የአገሪቱ የወንጀል ዳይሬክተር ሚካኤል ግራፍ ቮን ሞልትኬ ገልጸዋል።
ፖሊስ የፒዛ ሬስቶራንቱን ስራ አስኪያጅ በቁጥጥር ስር ለማዋል ወደ መኖሪያ ቤቱ ባቀናበት ወቅት የ36 ዓመቱ ግለሰብ የነበረውን አደንዛዥ ዕጽ በመስኮት ሲወረውረው ውጭ ቆመው በነበሩ ፖሊሶች “እቅፍ ውስጥ” እንደገባ አስረድቷል።
ፖሊስ በግለሰቡ መኖሪያ ቤት ባደረገው ፍተሻ 1.6 ኪሎግራም የሚመዝን ኮኬይን፣ 400 ግራም ካናቢስ (ዕጸፋርስ) እና 268 ሺህ ዩሮ በጥሬገንዘብ ማግኘቱ ተዘግቧል።
የሬስቶራንቱ ስራ አስኪያጅ ከቀናት በኋላ የተለቀቀ ሲሆን ሬስቶራንቱን እንደገና ከፍቶ ፒዛ እና ኮኬይን በጥምር ለደንበኞቹ ማቅረቡን ቀጥሏል። መርማሪዎች ይህንን ዕድል በመጠቀም የኮኬይን አቅርቦት ሰንሰለት በማሰሰስ ከሳምንታት በኋላ በምዕራብ ጀርመን ያለውን ዋነኛ ማዕከል መቆጣጠር ተችሏል።
ወደ 150 የሚጠጉ ፖሊሶች በምዕራብ ጀርመን ግዛት የሚገኙ ሁለት የዕጸ ፋርስ እርሻዎችን ወርረው የዕጸ ፋርስ ክምችት ማግኘታቸው ተዘግቧል።
ፖሊስ የ12 ግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ቤቶች ላይ ወረራ የፈጸመ ሲሆን በዚህም የአደንዛዥ ዕጽ ኦፕሬሽን ኃላፊ ነው የተባለ የ22 ተጠርጣሪን ጨምሮ ሶስት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
በዚህ ወረራ ወቅት የጦር መሳሪያዎች፣ ገንዘብ እና ውድ ሰዓቶች ተገኝተዋል ።
የፒዛ ሬስቶራንቱ ስራ አስኪያጅ ከሃገር ለመውጣት ሲሞክር በድጋሚ ተይዞ እስር ቤት ገብቷል። “በምግብ ዝርዝሩ ላይ ቁጥር 40 ፒዛ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚሸጡ ፒዛዎች አንዱ ነበር” ሲሉ ሞልትኬ ተናግረዋል።
ፖሊስ በአደንዛዥ ዕጹ ዝውውር ተሳትፈዋል ያላቸውን እንዲሁም የፒዛ እና የኮኬይን ጥምር ዋጋን ይፋ አላደረገም።












