በታዋቂው የሆሊዉድ ዳይሬክተር አባቱ እና በእናቱ ግድያ የተከሰሰው ሮብ ራይነር

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሎስ አንጀለስ ዐቃቤ ሕግ የሆሊውድ ዳይሬክተር እና ተዋናይ የሆኑትን ወላጆቹን በመግደል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለው ልጃቸው ላይ የወንጀል ክስ መሥርቷል።
ከሆሊውድ ዳይሬክተር እና ተዋናይ ሮብ ራይነር እንዲሁም ከባለቤታቸው ፎቶግራፈር ሚሼል ራይነር ግድያ ጋር በተያያዘ ልጃቸው ኒክ ራይነር በቁጥጥር ሥር ውሏል።
የ32 ዓመቱ ኒክ ራይነር ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ የግድያ ወንጀል ክሶች እንደቀረቡበት ዐቃቤ ሕግ ናታን ሆችማን ተናግረዋል። እናት እና አባቱ ባለፈው እሑድ ቤታቸው ሳሉ ተገድለው ተገኝተዋል።
ኒክ ራይነር አደገኛ መሣሪያ የሆነ ስለት በመጠቀምም ክስ ቀርቦበታል። በክሱ ላይ ኒክ ራይነር እናት እና አባቱን ለመግደል ስለት ተጠቅሟል የሚል ልዩ ክስ መካተቱም ተገልጿል።
"ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ያለ ይግባኝ የዕድሜ ልክ እስራት ወይም የሞት ቅጣት ሊፈረድበት ይችላል" ብለዋል ዐቃቤ ሕግ።
የሞት ቅጣት እንዲፈረድበት ዐቃቤ ሕግ ስለመጠየቁ መረጃ አልሰጡም። ኒክ ራይነር አስፈላጊው የጤና ምርመራ ከተደረገለት በኋላ ፍርድ ቤት ቀርቦ በይፋ ክሱ ይመሠረታል።
ወላጆቹ በብሬንትውድ፣ ካሊፎርኒያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በስለት በተደጋጋሚ ተወግተው ሞተው ከተገኙ በኋላ በቁጥጥር ሥር ውሏል።
የሟቾቹ የ28 ዓመት ሴት ልጅ ሮሚ ራይነር ባለፈው እሑድ ወደ ቤት ስትገባ እናት እና አባቷ በርካታ ቦታ በስለት ተወግተው እንዳገኘቻቸው የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘግቧል።
ሮብ ራይነር በተለያዩ ዘውጎች በርካታ ሙገሳ የተቸራቸው ፊልሞችን አዘጋጅቷል።
'ዌን ሀሪ ሜት ሳሊ'፣ 'ዚስ ኢዝ ስፓይናል ታፕ'፣ 'ስታንድ ባይ ሚ'፣ 'ሚዝሪ' እንዲሁም 'ኧ ፊው ጉድ ሜን' ከታዋቂ ፊልሞቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
ባለቤቱ ሚሼል ሲንገር ራይነር ተዋናይት፣ ፎቶግራፍ አንሺ እና ፕሮዲዩሰር እንዲሁም የፎቶግራፍ ኤጀንሲ እና ፕሮዳክሽን ኩባንያ የሆነው የራይነር ላይት መሥራች ነበረች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ78 ዓመቱ ሮብ ራይነር እና የ68 ዓመቷ ሚሼል ራይነር እሑድ ከሰዓት መሞታቸውን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አረጋግጠዋል። ፖሊስ እንዳለው ኒክ ራይነር ከግድያው ከሰዓታት በኋላ ነው በቁጥጥር ስር የዋለው።
መርማሪዎች እስካሁን ለግድያው ምክንያት ይሆናል ብለው ያሰቡት ነገር እንደሌለ ገልጸው፣ ምርመራው እንደቀጠለ አስታውቀዋል።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ያነጋገራቸው ምንጮች እንዳሉት ሮብ ራይነር እና ባለቤቱ ከመገደላቸው ከአንድ ቀን በፊት በነበረ ድግስ ላይ አባት እና ልጅ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲነታረኩ ነበር።
የሮብ ጠበቃ ታዋቂው የሕግ ባለሙያ አለን ጃክሰን መሆኑም ተገልጿል። ጠበቃው በሎስ አንጀለስ ፍርድ ቤት በመድፈር የተከሰሰው ታዋቂ ፊልም ሠሪ ሀርቪ ዌይንስታይንን ወክሎ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዐቃቤ ሕግ ናታን ሆችማን "የቤተሰብ አባላትን የሚመለከቱ ክሶች ልብ የሚሰብሩ እና ከባድ ናቸው። ብዙውን ጊዜ የሚፈጸሙት ወንጀሎች ጭካኔ የተሞሉ ናቸው" ብለዋል።
ኒክ በፊልሙ ዘርፍ በውስን ደረጃ የሚታወቅ ባለሙያ ነው። የአባቱን ያህል ዝናን አላተረፈም።
በአውሮፓውያኑ 2016 የተለቀቀው የ'ቢይንግ ቻርሊ' ፊልም አጋር ፀሐፊ ሲሆን አባቱ በአዘጋጅነት ተሳትፏል።
ፊልሙ በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ የሚንገላታ ወጣት ታሪክ ላይ ያጠነጥናል። በተወሰነ ደረጃ ፊልሙ የኒክን የሱስ ሕይወት ያሳያል።
ሮብ ራይነር ስለ ሱስ እና ስለ መኖሪያ ቤት እጥረት በይፋ በመናገር ይታወቃል። አልፎም በፖሊቲካው ዓለም ለዲሞክራቶች ግልጽ ድጋፍ ያደርግ ነበር። የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደርን በይፋ በመተቸትም ይታወቃል።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ የጥንዶቹ ሞት "እጅግ አሳዛኝ ነው" ቢሉም አስከትለው ያሰፈሩት ሐዘኔታ የጎደለው አስተያየት ከባድ ወቀሳን አስከትሎባቸዋል።
ትራምፕ በጽሁፋቸው ሮብን ክፉኛ የወቀሱ ሲሆን፣ ስለሳቸው በተደጋጋሚ ያወራ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በርካታ ሪፐብሊካኖች ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ያጋሩት መልዕክት ትክክል አይደለም ሲሉ ትችታቸውን አሰምተዋል።
ሞት "ለቤተሰብ ትልቅ ሐዘን ይዞ የሚመጣ ነገር ነው። ይህ ፖለቲካ አሊያም የፖለቲካ ተቀናቃኞችን የምናጠቃበት ጊዜ አይደለም" ሲሉ ሐሳባቸውን አጋርተዋል።
ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የሮብ የሥራ አጋር የነበሩ የሆሊውድ የፊልም ባለሙያዎች በትራምፕ አስተያየት የተሰማቸውን ቁጣ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውሮፓውያኑ 2016 በተደረገ ቃለ ምልልስ ላይ ኒክ እንደተናገረው ለዓመታት የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ ነበር። ማገገሚያ ማዕከሎች በተደጋጋሚ የገባ ሲሆን፤ ጎዳና የወጣበት ጊዜም ነበር።
"ነገሮችን በራሴ መንገድ ለማከናወን የጎዳና ተዳዳሪ መሆን ግዴታዬ ነበር" ሲል በወቅቱ ተናግሯል። ሊሞት ይችል እንደነበር ገልጾም "ሁሉም ነገር የዕድል ጉዳይ ነው" ብሏል።
ሎስ አልጀለስ ታይምስ ያወጣው ዘገባ እንደሚጠቁመው፤ ኒክ ለዓመታት ከሱስ ጋር ታግሏል።
"በአባቱ እገዛ ታሪኩን ለዓለም ነግሯል" ሲልም ዘገባው ያትታል።
ኒክ በአውሮፓውያኑ 2015 አካባቢ ከአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ተላቆ 'ቢይንግ ቻርሊ' ፊልም ላይ መሥራት ችሏል።
በ2016 በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገረው በልጅነቱ ከአባቱ ጋር "እምብዛም ትስስር አልነበረውም"።
ከፊልሙ ዝግጅት ጋር በተያያዘ መላው ቤተሰቡ የሠራውን ስህተት በማመን ለወደፊቱ በተሻለ መንገድ የማገገም ሒደት እንደሚኖራቸው ገልጸው ነበር።
ሮብ በወቅቱ በሰጠው ቃለ ምልልስ ከልጁ አስተያየት ይልቅ ለባለሙያዎች ምልከታ ቅድሚያ መስጠቱን አምኗል።
"ሕክምናው እየሠራ እንዳልሆነ ሲነግረን አልሰማነውም" ሲልም ተናግሯል።
ባለቤቱ ሚሼል ራይነርም የሥነ ልቦና ባለሙያዎች "ኒክ የውሸት ነው የታመመ የሚመስለው፤ እያጭበረበረ ነው" እንዳሏቸው ገልጻ፤ ይህንን የባለሙያዎች ምልከታ አምና መቀበሏን ተናግራለች።
ኒክ ሄሮይን መጠቀም ለማቀም የወሰነው በራሱ መንገድ እንደሆነ ገልጿል።
"ከጥሩ ቤተሰብ ነው የተገኘሁት። የጎዳና ተዳዳሪ ሆኜ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም የለብኝም ብዬ ወሰንኩ" ሲል ለሎስ አንጀለስ ታይምስ ተናግሯል።
'ቢይንግ ቻርሊ' ከወጣ በኋላ ኒክ በፊልም ዘርፍ ብዙም አልሠራም።
የሎስ አንጀለስ የፖሊስ ኃላፊ የሆኑት ጂም ማክዶኔል "ይህ ወንጀል ለቤተሰቡ እና ለሚወዷቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለመላው ከተማዋም ልብ የሚሰብር ነው። በዚህ አሳዛኝ ክስተት ለተጎዱ ሁሉ ጥልቅ ሐዘናችንን እንገልጻለን" ብለዋል።
የኒክን እናት እና አባት ለሞት ያበቃው ትክክለኛ መንስዔ፣ ግድያው የተፈጸመበት መንገድ እና ጊዜ በይፋ ለመግለጽ የአስከሬን ምርመራው መጠናቀቅ እንዳለበት ተገልጿል።















