በታዋቂው የሆሊዉድ ዳይሬክተር እና ሚስቱ ግድያ ወንድ ልጃቸው ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በታዋቂው የሆሊዉድ ዳይሬክተር ሮብ ራይነር እና ሚስቱ ሚሼል ሲንገር ግድያ ወንድ ልጃቸው ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተሰምቷል።
ጥንዶቹ በሎስ አንጀለስ ቤታቸው ሳሉ ተገድለው መገኘታቸውን የከተማዋ ፖሊስ አስታውቋል።
የ32 ዓመቱ ኒክ ራይነር በቁጥጥር ስር መዋሉንና ያለዋስትና እንደሚቆይ ፖሊስ ገልጿል።
የሟቾቹ የ28 ዓመት ሴት ልጅ ሮሚ ባለፈው እሑድ ወደ ቤት ስትገባ እናት እና አባቷ በርካታ ቦታ በስለት ተወግተው እንዳገኘቻቸው የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘግቧል።
ሮብ ራይነር በተለያዩ ዘውጎች በርካታ ሙገሳ የተቸራቸው ፊልሞች ዳይሬክተር ነበር።
ዌን ሀሪ ሜት ሳሊ፣ ዚስ ኢዝ ስፓይናል ታፕ፣ ስታንድ ባይ ሚ፣ ሚዘሪ እንዲሁም ኧ ፊው ጉድ ሜን ከታዋቂ ፊልሞቹ መካከል ናቸው።
የ78 ዓመቱ ሮብ ራይነር እና የ68 ዓመቷ ሚሼል እሑድ ከሰዓት መሞታቸውን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አረጋግጠዋል።
ፖሊስ እንዳለው ኒክ ራይነር ከግድያ ከሰዓታት በኋላ ነው በቁጥጥር ስር የዋለው።
መርማሪዎች እስካሁን ለግድያው ምክንያት ይሆናል ብለው ያሰቡት ነገር እንደሌለ አስታውቀው ምርመራ እንደቀጠለ አስታውቀዋል።
ሮብ ሳይነር ብዙውን ጊዜ ስለ ሱስ እና ስለ መኖሪያ ቤት እጥረት በይፋ በመናገር ይታወቃል።
አልፎም በፖሊቲካው ዓለም ለዲሞክራቶች ግልፅ የሆነ ድጋፍ ያደርግ ነበር።
የጥንዶቹ ሞት "እጅግ አሳዛኝ ነው" ያሉት ትራምፕ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ሮብን ክፉኛ የወቀሱ ሲሆን ስለሳቸው በተደጋጋሚ ያወራ እንደነበር ተናግረዋል።
ሮብ ራይነር የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደርን በይፋ በመተቸት ይታወቃል።
የቀድሞው የትራምፕ አጋር የሆኑት ማርጆሪ ቴይለር ግሪንን ጨምሮ በርካታ ሪፐብሊካኖች ትራምፕ በማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው ያጋሩት መልዕክት ትክክል አይደለም ሲሉ ትችታቸውን አሰምተዋል።
ሞት "ለቤተሰብ ትልቅ ሀዘን ይዞ የሚመጣ ነገር ነው። ይህ ፖለቲካ አሊያም የፖለቲካ ተቀናቃኞችን የምናጠቃበት ጊዜ አይደለም" ሲሉ ሐሳባቸውን አጋርተዋል።
ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የሮብ የሥራ አጋር የነበሩ የሆሊዉድ ሰዎች በትራምፕ አስተያየት የተሰማቸውን ቁጣ ሲገልፁ ታይተዋል።















