በደቡብ ሶሪያ በተነሳ ሁከት ወደ 600 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት አስታወቀ

በሞተር ላይ ተጭነው የሚሄዱ ተዋጊዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ግጭቱ የተቀሰቀሰው በቤዶኤ እና በድሩዝ ማኅበረሰቦች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ነው

በደቡባዊ ሶሪያ በተቀሰቀሰው ሁከት 594 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ የሚከታተለው ድርጅት አስታወቀ።

መቀመጫውን በዩኬ ያደረገው የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ በሱዌይዳ ግዛት ከእሁድ ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የጭካኔ ድርጊት መፈጸሙን ገልጿል።

146 ተዋጊዎች እና 154 ሰለማዊ ዜጎችን ጨምሮ 300 የድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት ተገድለዋል።

ከእነዚህም ውስጥ 83ቱ በመንግሥት ኃይሎች "ያለ ምክንያት ተገድለዋል" ሲል የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ሐሙስ ማምሻውን ይፋ አድርጓል።

ቢያንስ 257 የመንግሥት ሠራተኞች እና 18 የቤዶኤ ተዋጊዎች ሲገደሉ ሦስት የቤዶኤ ሰላማዊ ሰዎች በድሩዝ ተዋጊዎች መገደላቸውንም ገልጿል።

ግጭቱ የተቀሰቀሰው በቤዶኤ እና በድሩዝ ማኅበረሰቦች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ነው።

እስራኤል ባደረገችው የአየር ጥቃት ደግሞ ሌሎች 15 የመንግሥት ሠራተኞች መሞታቸው የተመዘገበ ሲሆን እስራኤል ድሩዞችን ለመጠበቅ እና የመንግሥት ወታደሮች ከሱዋይዳ ለቅቀው እንዲወጡ ለማድረግ በሚል ድብደባ መፈጸሟን ተናግራለች።

የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ይፋ ያደረጋቸውን ሟቾች ቁጥር ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልተቻለም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሆኖም የደኅንነት ምንጮች የሟቾችን ቁጥር 300 መሆኑን ሲገልፁ ሌላ የክትትል ቡድን ደግሞ፣ ሶሪያ ኔትወርክ ፎር ሂውማን ራይትስ፣ ቢያንስ የ169 ንፁኅን ዜጎች ሕይወት ማለፉን መረጃ መሰብሰቡን አስታውቋል።

በርካታ የድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት ከሚገኙባት የሱዋይዳ ከተማ የመንግሥት ኃይሎች ለቅቀው በመውጣታቸው ሐሙስ ዕለት አካባቢው ተረጋግቷል።

ነዋሪዎች የደረሰውን ጉዳት እና የተፈጸመውን ዝርፊያ እንዲሁም በጎዳናዎች ላይ አስከሬኖች ማገኘታቸውን ተናግረዋል።

የሶሪያ መንግሥት ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ መግባት የጀመሩት በድሩዝ እና በቤዶኤ መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ነው።

ከዚያ በኋላ ግን ጦርነቱ ተባብሶ በርካታ የድሩዝ አባላት ተገድለዋል።

የሶሪያ መንግሥት ወታደሮቹ ከመውጣታቸው በፊት ረቡዕ አመሻሽ ላይ የተኩስ አቁም ማድረጉን አስታውቋል።

ሆኖም አንድ ታዋቂ የድሩዝ መሪ ሼክ ሂክማት አል ሃጅሪ "ግዛታችን ሙሉ በሙሉ ከወንበዴዎች ነፃ እስኪወጣ ድረስ" በማለት ውጊያው እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የሼክ ሃጅሪ ተከታዮች ከመንግሥት ኃይሎች ጋር እየተፋለሙ ሲሆን ከእስራኤል ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚሞክሩ ይነገራል።

ሌሎች የሱዌዳ ድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት ደግሞ ከአዲሱ የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት ጋር በቅርበት ለመስራት እየሞከሩ ነው።

በእስራኤል እና በኃይል በያዘችው የጎላን ተራሮች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የድሩዝ ማህበረሰብ ይገኛል።

ሐሙስ ዕለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል በሶሪያ ላይ ጥቅሟን በኃይል በመጫን ለመቀጠል እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

በግጭቱ ውስጥ የእስራኤል ጣልቃ ገብነት በከፊል ድሩዞችን ለመጠበቅ የተደረገ ነው ያሉት ኔታንያሁ ግን የሶሪያ ጦር በደቡብ የአገሪቱ ክፍል እንዳይሰማራ ለመከላከል መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

"ይህ ደግሞ ወደፊት ፖሊሲያችን ይሆናል፤ ከደማስቆ በስተደቡብ ወዳለው ግዛት የሶሪያ ጦር ሠራዊት እንዲገባ አንፈቅድም እንዲሁም በድሩዝ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዲደርስ አንፈቅድም" ሲሉ ተናግረዋል።

ረቡዕ ዕለት የእስራኤል አየር ኃይል በደማስቆ በሚገኘው የሶሪያ የመከላከያ ሚኒስቴር ላይ በፈጸመው ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

የቀድሞው ፕሬዚደንት በሽር አል አሳድ መውረዳቸውን ተከትሎ እስራኤል በሶሪያ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ስትሰነዝር ቆይታለች።

የሶሪያ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ ረቡዕ ማምሻውን በቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ የእስራኤል ጥቃት አገራቸውን ለማተራመስ የተደረገ ሙከራ ነው ብለዋል።