በቦረና እና በጉጂ ማኅበረሰቦች መካከል ቅራኔን የፈጠረው የኦሮሚያ ክልል ውሳኔ

የቦረና ታዳጊ እና አባት

የፎቶው ባለመብት, ERIC LAFFORGUE/ART IN ALL OF US

የኦሮሚያ ክልል ከተሞችን እና ዞኖች እንደ አዲስ ማደራጀቱን ያስታወቀው ከሦስት ሳምንታት በፊት ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ ውሳኔ በተለይም የምሥራቅ ቦረና ዞን ምሥረታ ተቃውሞን እና ቅሬታዎችን እያስተናገደ ይገኛል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በጉጂ ዞን ቦሬ ወረዳ በተፈጠረ ተቃውሞ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉ እና ሁለት ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ዘግቦ ነበር።

ክልላዊው መንግሥት ምሥራቅ ቦረናን የክልሉ 21ኛ ዞን በማድረግ እንደ አዲስ ያቋቋመ ሲሆን፣ የዞን መቀመጫ ኔጌሌ ቦረና ነው ብሏል።

ይህ አዲስ የተቋቋመው ዞን ከቦረና ዞን፤ ሞያሌ፣ ጉጂ እና ዋጪሌ ወረዳዎችን እንዲሁም ሞያሌ ከተማን አልፎም ከጉጂ ዞን ሊበን፣ ጉሚ ኤልደሎ ወረዳዎችን እና ኔጌሌ ቦረና ከተማን፤ በተጨማሪ ከባሌ ዞን መደ ወላቡ፣ ኦቦርሶ እና ሃረና ቡሉቅ የተባሉ ወረዳዎችን በማካተት የተዋቀረ ነው።

የጉጂ ዞን መቀመጫ ኔጌሌ ቦረና (ከዚህ በፊት ኔጌሌ ተብላ የምተጠራው ከተማ) የነበረች ሲሆን፣ አሁን ግን አዶላ ሬዴ እንደምትሆን ተገልጿል።

የሰው ሕይወት እስከማጥፋት የደረሰው ተቃውሞ እና ቅሬታ በተለይም በኔጌሌ ቦረና ጉዳይ የተነሳ ነው።

የጉጂ ማኅበረሰብ ይህንን ጉዳይ “ከቤት እንደመባረር” ያዩታል። በተጨማሪም በባሌ ዞን ያሉ አንዳንድ ወረዳዎች በአዲሱ ዞን መካተታቸው ሕብረተሰቡን ማስከፋቱን ማኅበረሰብ አንቂዎች እና አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን በይፋ መግለጫ አልሰጠም። ነገር ግን ይህንን ውሳኔ ተከትሎ የአገር ሽማግሌዎች፣ የጉጂን ማኅበረሰብ በመወከል ከክልሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተናል ብለዋል።

የአገር ሽማግሌዎቹ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ “ውሳኔው እንደማይቀለበስ” እንደተነገራቸው ገልጸዋል።

ነገር ግን ሦስቱ ማኅበረሰቦች [ቦረና፣ ጉጂ እና አርሲ] በጋራ በመመካከር “የዞኑን ስያሜ መቀየር እንደሚችሉ” እንደተነገራቸው አክለዋል።

“የታቸኮለ ውሳኔ”

በማኅበራዊ ሚዲያዎች አስተያታቸውን የሚሰጡና ቢቢሲ ያናገራቸው የጉጂ ተወላጆች ይህን የመንግሥት ውሳኔ “አንዱን ማኅበረሰብ ከሌላው የማበላለጥ ነው” ይላሉ።

የጉጂ ተወላጅ የሆኑት እና በአሁን ወቅት በዩናይትድ ኪንግደም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩት እልፍነህ ኡዴሳ (ዶ/ር) “ይህ ውሳኔ የጉጂ እና የአርሲን ማኅበረሰብ ቅራኔ ውስጥ ከቷል” ይላሉ።

“በአርሲ እና በጉጂ በኩል ያለውን ብናይ፣ ይህ ዞን መቋቋሙ ሲነገር እኒህን ሁለት ጎሳዎች በመጉዳት የቦረናን ጎሳ ደግሞ እንደጠቀመ ነው የተወሰደው። እንደምሰማው ማኅበረሰቡ አዝኗል።”

ምሑሩ፤ ይህን ውሳኔ በሚመለከት የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሰጡት ምላሽ ሕዝቡ የበለጠ ቅሬታ እንዲሰማው አድርጓል ይላሉ።

እልፍነህ (ዶ/ር) እንደሚሉት አዲሱ ዞን ሲቋቋም “የተሄደበት መንገድ ትክክል ያልሆነ፤ ሕብረተሰቡን ያላሳተፈ እና በጣም የታቸከለ ነበር” በማለት ወንድማማች የሆነው ማኅበረሰብ እንዲጋጭ መንገድ እንደከፈተ ይጠቅሳሉ።

“ከመሬታችን ላይ ወርቅ እና የተለያዩ ማዕድናት ቢያወጡም፣ መሠረተ-ልማት ሳይሰሩልን አሁን ደግሞ እኛን በመናቅ ይህን ውሳኔ ወስነዋል የሚል ትልቅ ቅሬታ አለ።”

የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

“ቦረና የባሕል ማዕከል ነው”

ከሁለቱም ማኅበረሰቦች የወጡ አንቂዎች እና ምሑራን ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ኔጌሌ በመባል የምትታወቀውን፤ አሁን ደግሞ ኔጌሌ ቦረና የተሰኘችውን ከተማ ለእነሱ እንደምትገባ ይናገራሉ።

ዘመናት ያስቆጠሩ ፎቶዎችን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተፃፃፏቸውን ደብዳቤዎች እንዲሁም በአፈ ታሪክ አዛውንቶችን በማጣቀስ ይህች ከተማ የማን እንደነበረች ይገጻሉ።

አቶ ጃተኒ ዲዳ፤ የቦረና ባሕል እና ታሪክ አጥኚ ሲሆኑ በርካታ መፃሐፍትን አሳትመዋል።

“የኢትዮጵያም ሆነ የኦሮሚያ ድንበር አለ። በጋራ መሬት አለን። ይሁን እንጂ እንደ ሕዝብ እና እንደ ጎሳ ሰው የራሱ ወገን አለው” የሚሉት ተመራማሪው፤ ኔጌሌ ቦረና ውስጥ በአብዛኛው የቦረና ጎሳ እንደሚኖር ጠቅሰው “በታሪክም ሆነ በባሕልም ከተማዋ የቦረና ነች” ይላሉ።

ኔጌሌ ቦረና የምትገኝበትን ጨምሮ ያለው አካባቢ ሊበን በመባል የሚታወቅ እንደሆነ የሚጠቅሱት ተመራማሪው “መሬት በቦረና ማኅበረሰብ ማዕከል እና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። ከዚህ በተጨማሪ በአፈ-ታሪክ ሊበን በተለያየ ጊዜ ተጠቅሷል” ሲሉ ይገልጻሉ።

ለምሳሌ በቦረና የገዳ ሥርዓት አስተዳደር ውስጥ “ከለቻው የሚታሠርለት ሊበን ውስጥ ብቻ” እንደሆነና ይህም ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ማሳያ ነው ይላሉ።

አቶ ጃተኒ አክለው በፖለቲካ አስተዳደር ይህቺ ከተማ የቦረና ተወላጆች ከተማ መሆኗ በግልጽ የሚታወቅ ጉዳይ ነው።

“ቀርሳ ቢልቢሎ”

በቅርቡ የመንግሥት ውሳኔ መሠረት 21ኛ ዞን በመሆን የተቋቋመው የምሥራቅ ቦረና ዞን፤ ለረዥም ጊዜ ኔጌሌ በመባል የምትታቀው ከተማ አሁን ኔጌሌ ቦረና መቧሏ የተቃውሞ ምንጭ ሆኗል።

የጉጂ ማኅበረሰብ የዚህች ከተማ ስም በቅርብ ዓመታት ኔጌሌ መሆኗን በመናገር አንዲያውም ከዚህ ቀደም ሌላ ስም ነበራት ይላሉ።

መምህር እልፍነህ ኡዴሳ (ዶ/ር) ይህች ከተማ በተለያዩ መጠሪያዎች ትጠራ እንደነበር ጠቅሰው ልዩ ልዩ ጎሳዎች ይኖሩባት እንደነበር ያስረዳሉ።

“በዚህ አካባቢ የጉጂ፣ የአርሲ፣ የቦረና እና የሶማሊ ጎሳዎች ነበረበት። ስሟ በዚያ ወቅት ቀርሳ ቢልቢሎ ይባል ነበር።”

በአካባቢዋ ይኖሩ በነበሩ ልዩ ልዩ ጎሳዎች መካከል ግጭት በመፈጠሩ ማኅበረሰቡ ለችግር ተጋልጦ እንደነበርም ያወሳሉ።

“እነዚህ ጎሳዎች መካከል የተፈጠረው የተካረረ ግጭት እንዲቆም ሰንጋ አርደው፤ ተመራርቀው ሰላም በማውረድ የመሬቷን ስም ኔጌሌ ብለዋታል፤ ኔጌሌ ማለት ሰላም እንደማለት ነው” ሲሉ ወደ ኋላ ተመልሰው ታሪካዊ ዳራዋን ያስታውሳሉ።

ምሑሩ አክለው ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ሥፍራው ኔገሌ በመባል እንደሚታወቅ ያስረዳሉ።

ከዚያም በኋላ በነበረው አወቃቀር የጉጂ እና የቦረና መሬቶች እንዲሁም ሌሎችንም ወረዳዎች በመጨመር የቦረና አውራጃ በመባል በአንድነት ይተዳደሩ እንደነበር ታሪክ በማጣቀስ ይናገራሉ።

እንደሳቸው ሐሳብ ይህ ውሳኔ የቀደሙት መንግሥታት ይህንን ማኅበረሰብ በመከፋፈል ለመግዛት ያደረጉት ጥረት ነው።

መፍትሔው ምንድነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የክልሉ መንግሥት የ21ኛው እና አዲሱን ዞን ምሥረታ ይፋ ባደረገበት ወቅት ዞኑ ለረዥም ዘመናት የቆየውን የልማት፣ የሰላም፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄን የሚመልስ ነው ሲል ገልጾ ነበር።

አክሎም “በድንበር አካባቢ ያለውን ሕገ-ወጥነት ለመግታት እና የሰላም እጦትን ለመፍታት” ዞኑን ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን አመልክቷል።

ሚልኬሳ ሚደጋ (ዶ/ር) በፌዴራሊዝም ጉዳዮች የተለያዩ ጥናቶችን የሠሩ ምሑር ናቸው። በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ኃላፊ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን አሁን መኖሪያቸውን ሰሜን አሜሪካ አድርገዋል።

ምሑሩ፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባለሥልታን የነበሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥትን በፅኑ በመተቸት ይታወቃሉ።

ሚልኬሳ፤ በቅርቡ የክልሉ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ “የሕዝቡን ፍላጎት መሠረት ያደረገ አይደለም” ሲሉ ይተቻሉ። እንዲውም ውሳኔው በማኅበረሰቦች መካከል ግጭትን ያባብሳል በማለት “መሬት የብሔር ወይም የሕዝብ ነው። ወደታች ስትወርድ የጎሳም ይሆናል” ይላሉ።

“ይህን መሬት በአካባቢው ከሚኖረው ማኅበረሰብ ፍላጎት ውጪ እንደፈለጉት ለማድረግ መሞከር አምባገነንነት ነው።”

ምሑሩ መፍትሔ ነው የሚሉትን ሲያስረዱ “በሕብረሰተቡ ፍላጎት መሠረት ማስተዳደር ነው። ሕብረተሰቡ አሁን ምን ይፈልጋል በማለት መጠየቅ ይቻላል” ሲሉ ሐሳባቸውን ይሰነዝራሉ።

አቶ ጃተኒ ዲዳ በበኩላቸው፤ ልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ተቻችለው በሚኖሩበት ወቅት “ይህ ወንድማማች የሆነ ጎሳ ለጥላቻ እና ግጭት መዳረጉ እርግማን ነው” ይላሉ።

አልፍነህ ኡዴሳ (ዶ/ር) ደግሞ “የተቻኮለ እና ሕዝቡን ሳያወያዩ የተደረሰበት ነው” ያሉትን ውሳኔ መንግሥት ወደኋላ ተመልሶ ማየት አለበት የሚል አስተያየት ይሰጣሉ።

አክለው “የቅርብ ወንድማማች ናቸው” ያሏቸው ሁለቱ ማኅበረሰቦች ወደ አንድነት በመምጣት ያላቸውን ልዩነት እንዲፈቱ ይመክራሉ።