የሕዝብ ተወካዮች የአፍሪካ ኅብረት መንግሥትን እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን እንዲያሸማግል ጠየቁ

በኦሮሚያ ክልል በመንግሥት እና በታጣቂው ቡድን መካከል የሚካሄደውን ግጭት ለማሸማገል የአፍሪካ ኅብረት ጣልቃ እንዲገባ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እንደራሴዎች ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናገሩ።
አስራ ሁለት ገዢውን የብልጽግና ፓርቲን ወክለው በኦሮሚያ ክልል የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በክልሉ እየተካሄደ ያለው ግጭት የሕዝቡን ሕይወት እና ንብረት እያወደመ በመሆኑ፣ ትኩረት እንዲያገኝ በሚያደርጉት ጥረት ለአፍሪካ ኅብረት ጥሪ ማቅረባቸውን እንደራሴዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብር ቡድንነት በፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ ግጭቶች እና በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸው በተለያዩ ጊዜያት ተዘግቧል።
በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ባሉ ዞኖች ውስጥ እየተካሄደ ባለው ግጭት ጉዳት ከሚደርስባቸው ነዋሪዎች በተጨማሪ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለመፈናቀል መዳረጋቸው ተነግሯል።
በአማጺው ቡድን እና በመንግሥተ መካከል ንግግር ተካሂዶ ሰላም እንዲወርድ ከአገር ውስጥ እና ከውጭ ጥሪዎች ቢቀርቡም አስካሁን ተጨባጭ እርምጃ ሳይወሰድ ችግሩ ባለበት ቀጥሏል።
“ሰው እየሞተ ሕዝብ እየተሰቃየ ነው” ያሉት 12ቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አህጉራዊው ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት የተካሄደውን ጦርነት ለማስቆም እንዳረገው ሁሉ፣ በኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ችግር በማሸማገል እንዲረዳ ጥያቄ አቅርበዋል።
የምሥራቅ ወለጋ፣ ጅማ አርጆ ወረዳ ተመራጭ እና ከኦሮሚያ የተመረጡ የምክር ቤት አባላት አስተባባሪ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ብዙአየሁ ደገፋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም ችግሩን በንግግር ለመፍታት ፍላጎት እንዳለ በሁለቱም ወገኖች የተገለጸ ቢሆንም ተጨማባጭ እርምጃ ባለመወሰዱ ነው የአፍሪካ ኅብረት በአሸማጋይነት ጣልቃ እንዲገባ የጠየቁት።
ባለፈው የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በክልሉ ምክር ቤት በተናገሩበት ወቅት፣ መንግሥት ሸኔ በማለት የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወደ ሰላም የሚመጣ ከሆነ በራቸው ክፍት መሆኑን ገልጸው ነበር።
አቶ ሽመልስ በክልሉ ለሚካሄደው የልማት ሥራ ሰላም ወሳኝ መሆኑን እና በክልሉ ውስጥ ሰላም ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ በመጥቀስ ለዚህም “ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ እንደ ሸኔ ያሉ ኃይሎች በንግግር ወደ እርቅ እንዲመጡ” ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጥሪውን በአውንታዊነት እንደሚመለከተው በመግለጽ ለድርድሩ ስኬታማነት ያስፈልጋሉ ያላቸውን ጉዳዮች በመግለጽ ፍላጎቱን አሳውቆ ነበር።
በሁለቱም ወገን የሰላም ፍላጎት እንዳለ ከተገለጸ አንድ ወር እንደሞላው የሚጠቅሱት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ፣ አስካሁን ግጭቱን በማስቆም ሰላም የሚያመጣ ምንም አይነት ተጨባጭ እርምጃ ባለማየታቸው የአፍሪካ ኅብረትን ተሳትፎ በደብዳቤ እንዲጠይቆ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።
የብልጽግና አባላት የሆኑት እንደራሴዎች የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሚያ ክልል ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር እንዲደራደር በይፋ ሲጠይቁ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ከጥቂት ወራት በፊት 10 ነጥቦችን የያዘ ጥያቄ ያረቡ ሲሆን፣ ከመንግሥታት ምን አይነት ምላሽ እንዳገኙ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ከአስራ ሁለቱ የምክር ቤት አባላት መካከል አንዱ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ብዙአየሁ ደገፋ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ከዚህ ቀደም ጥያቄያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለኦሮሚያ ምክር ቤት እንዲሁም ለፓርቲያቸው ለብልጽግና አቅርበው ምላሽ ሲጠብቁ ነበር።
እንደራሴዎቹ ለጥያቄያቸው የተሰጣቸው ምላሽ ወይም የገጠማቸው ተቃውሞ ካለ በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ አሁን ዋናው ጉዳይ ሰላም የሚመጣበትን መንገድ መፈለግ ስለሆነ “እሱን ወደፊት እንመጣበታልን” በማለት ረ/ፕሮፌሰር ብዙአየሁ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በመንግሥት እና በታጣቂው ቡድን መካከል ችግሩን በሰላም ለመፍታት ፍላጎት መኖሩ መልካም ነገር መሆኑን የገለጹት ተወካዩ፣ ነገር ግን ወደዚያ የሚያደርስ ተጨባጭ እርምጃ ሳይወሰድ ጊዜው እየሄደ በሕዝቡ ላይ የሚደርሰው ችግር ባለበት ቀጥሏል ብለዋል።
ለንግግሩ መጀመር “አደራዳሪ እና ተደራዳሪዎችን በመሰየም እንዲሁም ቦታ እና ጊዜ በመወሰን ለሕዝቡ በማሳወቅ” ለሰላም ፍላጎቱ ተግባራዊነት ቀጣይ እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ ሰኞ መጋቢት 11/2015 ዓ.ም. ለአፍሪካ ኅብረት ባቀረቡት ጥሪ ላይ፣ ኅብረቱ በትግራይ ውስጥ ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት ለማስቆም ካበረከተው አስተዋጽኦ አንጻር፣ በኦሮሚያ ክልል ለዓመታት የተካሄደውን ግጭት ኅብረቱ “አቅልሎ በመመልከቱ” ማዘናቸውን ገልጸዋል።
ከአንድ ወር በፊት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ ተከትሎ፣ ታጣቂው ቡድን በሰጠው ምላሽ ንግግር ለመጀመር አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጦ ነበር።
በዚህም ገለልተኛ የሦስተኛ ወገን የውጭ አሸማጋዮች፣ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት በተጨማሪ የፌደራል መንግሥቱ ተሳታፊ መሆን፣ በፖለቲካ ተሳትፏቸው ምክንያት የታሰሩ ሰዎች እንዲለቀቁ እና ሌሎችም ሁኔታዎች ቀድመው መልስ ማግኘት እንዳለባቸው ጠይቆ ነበር።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ከቃል ባሻገር በመንግሥት እና በአማጺው ቡድን መካከል ንግግር ለማድረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ የጠየቁ ሲሆን፣ “ከፌደራል መንግሥቱ እና ከኦሮሚያ ክልል አራት አራት ተወካዮች” ለድርድሩ እንዲመደቡ ሀሳብ አቅርበዋል።
ይህ በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት ዝም ተብሎ ከተተወ የሕዝቡን ስቃይ ከማባሱ በተጨማሪ ወደ ሌላ ችግር ሊሸጋገር እንደሚችል የሚጠቅሱት እንደራሴዎቹ “ከሰላም ጥሪ ባሻገር ቀጣይ ተጨባጭ እርምጃ መወሰድ አለበት” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኦሮሚያ ክልል ሕዝብን በመወከል ከተሰየሙት ከ170 በላይ እንደራሴዎች መካከል ለምን 12ቱ ብቻ ይህንን ጥያቄ እንዳቀረቡ ከቢቢሲ የተጠየቁት ረ/ፕሮፌሰር ብዙአየሁ ከክልሉ ተመራጮች ባሻገርም ድጋፍ እንዳለቸው ተናግረዋል።
ጉዳዩን ይዘው የሚንቀሳቀሱት 12ቱ እንደራሴዎች በዋናነት የሰላም ችግር ካለበት አካባቢ የተወከሉ መሆናቸውን በማመልከት “ከኦሮሚያ ባሻገር እያቀረብነው ያለውን ጥያቄ ከአማራ እና ከደቡብ ክልል የተወከሉ የምክር ቤት አባላትም ድጋፍ አለን” ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ለአፍሪካ ኅብረት ያቀረቡትን ጥሪ በተመለከተ ከኅብረቱ በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በውጭ አገራት ያሉ እና የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ቡድኖች ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ እንዲገቡ በቀረበው ጥሪ መሠረት በርካታ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አገር ቤት መግባታቸው ይታወሳል።
ከእነዚህም መካከል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አንዱ ሲሆን፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከዚሁ ቡድን በመለየት በትጥቅ እንቅስቃሴው ቀጥሏል። ባለፉት አራት ዓመታትም ቡድኑ በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ በስፋት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን መንግሥት ‘ሸኔ’ ሲል የሚጠራው ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት በሽብርተኛነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሰይሞ ሕገወጥ ቡድን ሆኗል።
በምዕራብ እና በደቡብ የአገሪቱ ክፍሎች የሚንቀሳቀሰው ይህ ታጣቂ ቡድን በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጽማቸው ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ቡድኑ ግን ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ እንደማያደርግ በተደጋጋሚ ሲያስተባብል ቆይቷል።












