በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች በድርቅ ሳቢያ በተባባሰው ኮሌራ 48 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ነሐሴ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች የተቀሰቀሰው እና ለ48 ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት የሆነው የኮሌራ ወረርሽኝ እንዲስፋፋ ድርቅ ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ለቢቢሲ ገለጸ።
በኢኒስቲትዩቱ የበሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ወሰን በዚህ ዓመት በኮሌራ ከተያዙት 2 ሺህ 170 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ጠቁመዋል።
ኃላፊው የኮሌራ ወረርሽኝ ኦሮሚያ ክልል በ15 እንዲሁም በሶማሌ ክልል በሦስት ወረዳዎች በድምሩ 170 ቀበሌዎች ላይ መከሰቱን የገለጹት ኃላፊው፣ ከኦሮሚያ ክልል 1 ሺህ 880 ከሶማሌ ክልል ደግሞ 290 ሰዎች ተይዘዋል ብለዋል።
ከ18 ወረዳዎች ውስጥ በአምስቱ በሸታውን መቆጣጠር እንደታቸለም ነው ኃላፊው የተናገሩት።
ሕይወታቸው ካለፉት መካከል ሰላሳ አንዱ በኦሮሚያ ክልል ነዋሪ ሲሆኑ፣ የተቀሩት በሶማሌ ክልል የሚኖሩ ናቸው።
በክልሎቹ በበሽታው የመያዝ ምጣኔ ከ100 ሺህ ሰው 120 እንዲሁም የሞት ምጣኔው ከተያዙት 2.1 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል።
አቶ መስፍን ወረርሽኙ ካለፈው ዓመት ዓመት አንጻር መጨመሩን የገለጹ ሲሆን፣ ለመጨመሩ በአካባቢዎቹ የተከሰተው ድርቅ ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ድርቁ የንጹህ ውሃ እጥረትን በማስከተል፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ የደርቅ የአየር ንብረት ሁኔታ እንዲሁም የመጸዳጃ ቤት ሽፋን አነስተኛ መሆን ለበሽታው መስፋፋት መንስኤ መሆኑን አንስዋል።
“ከፍተኛ የውሃ እጥረት መኖሩ ይህንን ወረርሽኝ አባብሶታል. . . የምግብ እና የውሃ እጥረት መኖሩ ለወረርሽኙ መስፋፋት ቀዳሚ እና ዋና መንስኤ ነው” ሲሉም አክለዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት በሽታው በተከሰተባቸው አከባቢዎች 23 ጊዜያዊ የኮሌራ ሕክምና ጣቢያ በማቋቋም አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነም ተመላክቷል።
ወረርሽኙ “አሁንም ከወቅቱ ጋር ተያይዞ” ወደ ሌሎች ክልሎች የመስፋፋት ዕድል እንዳለው የተናገሩት አቶ መስፍን፣ መሥሪያ ቤታቸው ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ቀድሞ ለመከላከል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እያከናወነ እንደሆነ አስረድተዋል።
በወረርሽኙ ከኢትዮጵያ በተጨማሪም በሶማሊያ፣ በኬንያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ በናይጄሪያ፣ በማላዊ እና በሞዛምቢክ ብዙ ሰዎች እንደተያዙ አንስተዋል።
አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት ዋናው የኮሌራ ምልክት ሲሆን፣ በፍጥነት ወደ ሕክምና መሄድ በሽታውን ለመቆጣጠር ወሳኙ እርምጃ ነው።
የግል እና የአካባቢን ንጽህናን መጠቀም፣ ንጹህ ወይም የፈላ አሊያም በኬሚካል የታከመ ውሃን መጠቀም ከበሽታው ራስን ለመከላከል ጠቃሚ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።












