የስፔን የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች ለ11 ቀናት በመርከብ ስር ተደብቀው የተጓዙ ሰዎችን አገኙ

በመርከቧ ላይ የተደበቁት ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, SALVAMENTO MARITIMO

የምስሉ መግለጫ, በመርከቧ የታችኛ ክፍል ውስጥ የተደበቁት ሰዎች

ከናይጄሪያ በመነሳት የ11 ቀናት ጉዞ አድርጎ ወደ ስፔን በደረሰ መርከብ የፊት ክፍል ጫፍ ላይ ሦስት ሰዎች ተንጠላጥለው መገኘታቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

በስፔን የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች ይፋ የተደረገ ፎቶግራፍ እንደሚያሳየው በነዳጅ ጫኝ መርከቧ ፊት ለፊት የታችኛ ክፍል ጫፍ ላይ የተቀመጡ ሰዎችን አሳይቷል። የሰዎቹ እግርም ከባሕሩ ውሃ ከአንድ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ ሆኖ ይታያል።

በመርከቧ አካል ላይ ተንጠልጥለው አውሮፓ የደረሱት ሦስቱ ሰዎች በአቅራቢያ ወደ ሆስፒታል ተወስደው የህክምና እርዳታ እንደተደረገላቸው ተገልጿል።

ነገር ግን ሰዎቹ መርከቧ ለአስራ አንድ ቀናት በተጓዘችበት ጊዜያት ሁሉ እዚያ ቦታ ላይ ሆነው መጓዛቸውን በተመለከተ አስካሁን የታወቀ ነበር።

የማልታን ሰንደቅ ዓላማ የምታውለብልበው አልቲኒ የተባለችው መርከብ ከናይጄሪያ ተነስታ ነው የስፔን ደሴት ወደ ሆነችው ግራን ካናሪስ የደረሰችው።

የባሕር ላይ ጉዞዎችን የሚከታተለው ድረ ገጽ እንደሚለው ነዳጅ የጫነችው መርከብ ከ2,700 ማይሎች የውሃ ላይ ጉዞ በኋላ ነው ወደ ስፔኗ ደሴት የደረሰችው። የተገኙትም ሰዎች ይህንን ያህል ርቀት በመርከቧ አካል ላይ ተደብቀው ሳይጓዙ እንዳልቀሩ ይታመናል።

ሦስቱ ሰዎች መርከቧ ከወደብ ላይ መልህቋን ከጣለች በኋላ እዚያው በሐኪሞች ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን፣ በማስከተልም ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የስፔን ዜና አገለግሎት ዘግቧል።

ከመርከቦች የፊት ክፍል ግርጌ ላይ የሚገኘው እና የጉዞ መስመራቸውን እንዲከተሉ በሚያገለግለው ክፍል ላይ ሰዎች ተደብቀው ሲገኙ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።

ከሁለት ዓመት በፊት አንድ የ14 ዓመት ታዳጊ በተመሳሳይ ከሌሎች ሰዎች ጋር ከናይጄሪያ ሌጎስ ተነስቶ ወደ ግራን ካናሪያ ደሴት ደርሶ ነበር።

ልጁ ለአንድ የስፔን ጋዜጣ እንደተናገረው በነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ተደብቆ ለ15 ቀናት ተጉዟል።

በጉዞው ላይ ጨው ያለበትን የባሕር ውሃ እየጠጡ እና በየተራ እየተኙ መጓዛቸውን የገለጸው ታዳጊ፣ ደሴቷ ላይ ሲደርሱ ህክምና ለማግኘት ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ተናገሯል።

“በጣም ደክመን ነበር። ጉዞው እንደዚህ ከባድ ሊሆን ይችላል ብዬ አላሰብኩም ነበር” ብሏል ታዳጊው።

በዚያው ዓመት በተመሳሳይ ሁኔታ የኖርዌይ በሆነችው ቻምፒዮን ፑላ በተባለችውና ከናይጄሪያ ነዳጅ ጭና በተነሳችው መርከብ ላይ አራት ሰዎች ተደብቀው ላስ ፓልማስ ደሴት ደርሰው ነበር። በወቅቱ የወጡ ሪፖርቶች እንዳሉት ሰዎቹ በመርከቧ ውስጥ ተደብቀው ለ10 ቀናት ተጉዘዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጀልባዎች በመሳፈር ከምዕራብ አፍሪካ በመነሳት የስፔን ንብረት ወደ ሆነችው ካናሪ ደሴት የሚደርሱት ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።