የኬንያ ፍርድ ቤት መንግሥት ልውጥ ዘረመል ሰብሎች ላይ ያደረገውን እገዳ የማንሳት ውሳኔ ቀለበሰ

ጂኤምኦ በቆሎ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኬንያ ፍርድ ቤት መንግሥት ልውጥ ዘረ መል ሰብሎች ላይ የነበረውን እገዳ የማንሳት ውሳኔ በጊዜያዊነት ቀለበሰ።

የኬንያ መንግሥት ልውጥ ዘረመል ሰብሎችን ማብቀል፣ ወደ ሃገር ውስጥ ማስገባት እና ማከፋፈል ላይ ለአመታት ተጥሎ የነበረውን እገዳ ከሰሞኑ ማንሳቱ ይታወሳል።

ውሳኔው በጊዜያዊነት መታገዱንም የዘገቡት የኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ናቸው።

ፍርድ ቤቱ ወደዚህ ብያኔ የደረሰው የኬንያ አርሶ አደሮችን በመወከል አንድ ጎትጓች ቡድን ክስ ማቅቡረቡን ተከትሎ ነው። የእገዳው መነሳት “ሥርዓቱን የተከተለ ህገወጥ” ነው ሲል ተከራክሯል።

ሃገሪቱ በአራቱ ዝናባማ ወቅቶች ዝናብ ባለመዝነቡ ምከንያት ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት አጋጥሟታል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ለአስር ዓመታት በዘረ መል ሰብሎች ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ እንዲነሳ ውሳኔ አስተላልፏል።

እገዳውን ማንሳት ማለት የኬንያ አርሶ አደሮች ልውጥ ዘረመል ሰብሎችን ማሳደግ እንዲሁም በዘረ መል ምህንድስና የተመረቱ ምግቦችን እና የእንስሳት መኖዎችን ወደ ሃገር ውስጥ ያስገባሉ ማለት ነው።

ከነዚህም ውስጥ ዘረመሉ የተሻሻለው ነጭ በቆሎ ይገኝበታል።

 የሰው ልጅ ምግብ እና የሳይንስን ልኅቀት ትስስርን ከሚያሳየው ጂኤምኦ (የዘረ መል ለውጥ) ጋር በተያያዘ በርካታ ውዝግቦች ተነስተዋል።

ለአስርት ዓመታትም የአካባቢ ጥበቃ ተከራካሪዎች፣ ኩባንያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የሸማቾች ጥበቃ ማኅበር፣ የዓለም ንግድ ድርጅቶችንም በማከራከር እና በማወዛገብ ቀጥሏል።

ጂኤምኦን የሚደግፉ አካላት ይህ ሳይንስ ብዙ ምርት እንዲገኝ፣ በሽታን ወይም ድርቅን የሚቋቋሙ ባህሪያትን እንዲዳብር እና ሌሎችንም ጉዳዮች ያነሳሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ የሚነሱት ስጋቶች በሰው ጤና እና በአካባቢ ላይ ሊደርስ የሚችል ጉዳት፣ በባህላዊ የግብርና አሰራር ላይ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ እንዲሁም የኩባንያዎች የበላይነት እና የቴክኖሎጂው “ከተፈጥሮ ውጪ” ነው የሚሉ ናቸው።

ሰው ሠራሽ የዘረ መል ለውጥ የተደረገባቸው ምግቦች ጎጂዎች ናቸው የሚለው አሁንም እንዳከራከረ ነው።

ካንሰርን ጨምሮ ሌሎች እክሎችን እንደሚያስከትሉ በርካታ ሪፖርቶች ቢወጡም በጤና ደረጃ በሳይንስ የተረጋገጠ ሪፖርት አይደለም የሚሉም አልታጡም