ለጤንነትና ለአካባቢ ምቹ በመሆን የተመረጡ አምስት ምግቦች

ዋካሜ

የፎቶው ባለመብት, Stacy Michelson/BBC

በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች በአብዛኛው የሚመገቡት ከሦስት ሰብሎች የሚዘጋጁ ምግቦችን ነው። እነዚህም ሩዝ፣ በቆሎና ስንዴ ሲሆኑ እነሱም 60 በመቶውን የምድራችን ነዋሪ የሚያስፈልገውን የካሎሪ መጠን የሚያስገኙ ናቸው።

ነገር ግን ከእነዚህ ውስን ሰብሎች ከሚዘጋጁ ምግቦች በቂ ካሎሪ ቢያገኝም ቫይታሚንና ሚነራሎችን በበቂ ሁኔታ ለማግኘት ግን አዳጋች ነው።

አንድ አዲስ ጥናት 50 ለጤናና ለተፈጥሮ አካባቢ ተስማሚ ያላቸውን ምግቦች "የመጪው ዘመን ምግቦች" በማለት ይፋ አድርጓል። የትኞቹ ምግቦች ናቸው ቀዳሚ ተብለው በዝርዝሩ ውስጥ የሰፈሩት?

ሞሪንጋ (ሽፈራው)

የሞሪንጋ ዛፍ

የፎቶው ባለመብት, Stacy Michelson/BBC

የምስሉ መግለጫ, ድርቅን የሚቋቋመው ሞሪንጋ (ሽፈራው)

የሞሪንጋ ዛፍ በስፋት የሚጠቀሰው "ተአምረኛው ዛፍ" እየተባለ ነው። ዛፉ በቶሎ የሚያድግና ድርቅን የሚቋቋም ሲሆን ምንጩም የእስያ አህጉር ነው። የዛፉ የተለያዩ ክፍሎች ለመድሃኒትነት ጭምር ያገለግላሉ።

በቫይታሚን ኤ እና ሲ እንዲሁም በካልሺየምና በፖታሺየም የበለጸገው የዛፉን ቅጠል በዓመት ሰባት ጊዜ መሰብሰብ ይቻላል። ቅጠሉ የተለያዩ ሥጋ ነክ ምግቦችን ለመስራትም ያገለግላል። ፍሬውም ሾርባን በመሳሰሉ ምግቦች ውስጥ ቢጨመር ጤናማ የሆነ ኮሌስትሮል በሰውነታችን ውስጥ እንዲፈጠር ያደርጋል።

የሞሪንጋ ቅጠል ተፈጭቶ ከተዘጋጀ ለወጥ፣ ለጭማቂ፣ ለሾርባና ለሻይ ያገለግላል።

ዋካሜ (የባህር አረም)

ዋካሜ አረም

የፎቶው ባለመብት, Stacy Michelson/BBC

የምስሉ መግለጫ, ዋካሜ ዓመቱን ሙሉ ሊመረት ይችላል

ጃፓኖች ለክፍለ ዘመናት ዋካሜ የተባለውን የባህር ውስጥ አረም እያመረቱ ለምግብነት ሲጠቀሙ ኖረዋል። በተጨማሪም ይህን እጽዋት ለስጦታና ለግብርም ይሰጡ ነበር።

ይህ አረም በአሁኑ ወቅት በፈረንሳይ፣ በኒውዚላንድና አርጀንቲና ባህሮች ላይ የሚመረት ሲሆን ያለምንም ማዳበሪያና ጸረ ተባይ ዓመቱን በሙሉ ምርት ይሰጣል። እንዲደርቅ የሚደረገውም በፀሐይ ሙቀት ነው።

የደረቀው የባሕር አረም ጨዋማ ጣዕምን ምግብ ላይ ከመጨመሩ ባሻገር ለጤና ተስማሚ የሆነ ንጥረ ነገርን ለተመጋቢዎች ይሰጣል።

ከተለያዩ አይነት የባሕር ውስጥ አረሞች መካከል ለስላሳውና ቡናማው ዋካሜ የተባለው የደም ግፊትን የመቀነስ፣ የደም መርጋትን የመከላከልና ሌሎችም የጤና ጥቅሞች እንዳሉት ተመስክሮለታል።

ይህ የባሕር ውስጥ አረም አዮዲንና ኦሜጋ 3 የተባሉ ንጥረ ነገሮች ዋነኛ ምንጭ ሲሆን በተለይ የእንስሳ ተዋጽኦዎችን ለማይመገቡ ሰዎች ጥቅማቸው የጎላ ነው።

ፎኒዮ

የፎኒዮ ንጥረ ነገር

የፎቶው ባለመብት, Stacy Michelson/BBC

የምስሉ መግለጫ, ጥንታዊው ፎኒዮ አዲሱ ተመራጭ ጥራጥሬ ሆኗል

ማሊ ውስጥ የሚገኙት የባምባራ ማኅበረሰብ አባላት እንደሚሉት ይህ ጣፋጭ የምግብ አይነትን ለማዘጋጀት ቀላል ከመሆኑ የተነሳ "የሚያዘጋጀውን ሰው አያሳፍርም" ሲሉ ያሞካሹታል።

ፎኒዮ ከ5 ሺህ ዓመታት በፊት ግብጽ ውስጥ ይመረት እንደነበር የሚነገርለት ሲሆን ድርቅን የሚቋቋሙ ጥቁርና ነጭ ዝርያዎች አሉት። ይህ የጥራጥሬ ዘር በምዕራብ አፍሪካ የሳህል አካባቢ ከ60 እስከ 70 ቀናት ውስጥ ይበቅላል።

የፎኒዮ ፍሬ የአሸዋን ያህል ጥቃቅን ሲሆኑ ለምግብነት ከመዋሉ በፊት ገለባው መወገድ አለበት። ይህም በእጅ የሚሰራ ሲሆን ሴኔጋል ውስጥ አዲስ ሥራ የጀመረ ማምረቻ ይህንን ግሉትን ከተባለ ንጥረ ነገር ነጻ የሆነውን ምርት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ አቅዷል።

ፎኒዮ በአይረን፣ በዚንክና ማግኒዢየም የምግብ ንጥረ ነገሮች የዳበረ ሲሆን እንደሩዝ ሊበላ ይችላል። ከዚሁ ሰብል ቢራ ሊጠመቅ ይችላል ተብሏል።

ኖፓሊስ ቁልቋል (በለስ)

ኖፓሊስ ቁልቋል( በለስ)

የፎቶው ባለመብት, Stacy Michelson/BBC

የምስሉ መግለጫ, ኖፓሊስ ቁልቋል (በለስ)፣ ዓይነት ሁለት፣ የስኳር ታማሚዎችን ይረዳል።

ይህ በሜክሲኳዊያን የተለመደ ምግብ የሆነው ቁልቋል (በለስ)፣ የተለያየ ክፍሉ በተለያየ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ለምግብነት ይውላል።

ይህን የቁልቋል አይነት በማዕከላዊና ደቡብ አሜሪካ፣ በአውስትራሊያ እንዲሁም አውሮፓ ውስጥ በቀላሉ ይበቅላል።

አንዳንድ ጥናቶች እንዳመለከቱት ከዚህ እጽዋት ውስጥ የሚገኘው አሰር ከሰውነታችን ውስጥ የተጠራቀመን ስብ ለማስወጣት ይረዳል። በተጨማሪም፣ አይነት ሁለት፣ የስኳር ህመም ላለባቸው ሰዎች ስኳር መጠናቸውን ለመቀነስ እንደሚያገለግልም ይነገርለታል።

ይህንን የቁልቋል አይነት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመገቡ በአንዳንዶች ላይ ማስቀመጥ፣ ማቅለሽለሽና ባልተለመደ ሁኔታ የሆድ መነፋት ሊያጋጥማቸው ይችላል።

ባምባራ (ጣፋጭ ለውዝ)

ባምባራ (ጣፋጭ ለውዝ)

የፎቶው ባለመብት, Stacy Michelson/BBC

የምስሉ መግለጫ, ባምባራ (ጣፋጭ ለውዝ) የፕሮቲን ዋና ምንጭ ነው

ባምባራ ብዙ ቅባት የሌለው ሲሆን የጣፋጭ ለውዝ ዓይነት ነው። የባምባራ ፍሬ ለም ባልሆነ አፈር ላይ የሚበቅል በመሆኑና የያዘውን የናይትሮጅን መጠን ወደ መሬት በመልቀቅ መሬቱን ለም የማድረግ ኃይል አለው። በዚህም ምክንያት በዘላቂ የምግብ ዋስትና ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችን ትኩረት መሳብ ችሏል።

በባህላዊ መልኩ በአፍሪካ የሚመረተው ባምባራ በደቡባዊ ታይላንድና በማሌዥያ አንዳንድ አካባቢዎችም ይበቅላል። በመቀቀል፣ በመቁላት፣ በመጥበስና በዳቦ ውስጥ በመጨመር ለምግብነትም ይሰናዳል።

በምስራቅ አፍሪካ ሾርባ ለመስራትም ዋና ግብዓት በመሆን ያገለግላል። "የተሟላ ምግብ" በመባልም ይታወቃል።

በፕሮቲን የበለፀገ በመሆኑ እንዲሁም የደም ስሮችን እድገት የሚያፋጥነውንና የሰውነትን በሽታ መከላከል አቅም የሚረዳውን -ዚንክ የያዘውን የአሚኖ አሲድ ሜቲኦናይን ምንጭ በመሆኑ፤ የታይሮይድ እጢን ሥራ የሚቆጣጠረውንና ለበሽታ መከላከል የሚረዳውን ሴሌኒየም ንጥረ ነገረ በመያዙ ነው የተሟላ የሚለው ስያሜ የተሰጠው።

ባምባራ አትክልትን ብቻ ለሚመገቡ፣ ጥቂት የእንስሳት ተዋፅኦን ለሚመገቡ እንዲሁም እጽዋት ላይ የተመሠረተ የአመጋገብ ሥርዓት ላላቸው ሰዎች ፕሮቲን በመያዙ ወሳኝ ምግብ ነው ።

አሁን እያጋጠመ ባለው የምግብ አቅርቦት ችግር ወደፊት የሚኖሩን ምግቦች በቀላሉ የሚመረቱና በቀላሉ የበለፀጉ መሆን እንዳለባቸውም ጥናቱ ይመክራል።