የማላዊ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ከኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጅምላ መቃብር ጋር በተያያዘ የታሰረውን የእንጀራ ልጃቸውን ጎበኙ

የማላዊ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ፒተር ሙታሪካ ከኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጅምላ መቃብር ጋር ተያይዞ በእስር ላይ የሚገኘውን የእንጀራ ልጃቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ጎበኙ።
የእንጀራ ልጃቸው ታዲኪራ ማፉቡዛ በመዲናዋ ሊሎንግዌ በእስር ላይ ይገኛል።
ታዲኪራ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በቁጥጥር ስር የዋለው በጥቅምት አጋማሽ በሃገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል 30 የሚሆኑ የኢትዮጵያ ስደተኞችን አስከሬኖችን የያዘ የጅምላ መቃብር ጋር ንክኪ አለው በሚል ተወንጅሎ ነው።
ግለሰቡ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና በግድያ ወንጀል ተከሷል።
ታዲኪራ በቀረበበት ክስ ላይ አስተያየቱን ከመስጠት ተቆጥቧል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሙታሪካ ከእስር ቤቱ ጉብኝት በኋላ ምንም አይነት ቃለ መጠይቅም ሆነ መግለጫ አልሰጡም።
ነገር ግን ከቀናት በፊት ባወጡት መግለጫ የእንጀራ ልጃቸው እስር በቤተሰቡ እና በፓርቲያቸው ዲሞክራቲክ ፕሮግረሲቭ ፓርቲ ደጋፊዎች ላይ የተቃጣ የፖለቲካ ሴራ አካል እንደሆነም ገልጸዋል።
በሳቸው አስተዳደር ወቅት ሚኒስትሮች የነበሩ እና ጠባቂያቸውም ከሙስና ጋር በተያያዘ ክስ ተመስርቶባቸው እስር ቤት ይገኛሉ።
ሙታሪካ ወደ ስልጣን የመጡት በአውሮፓውያኑ 2014 ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2020 በፕሬዚዳንት ላዛሩስ ቻኩዌራ ተሸንፈውም ስልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል።
የፖሊስ ቃለ አቀባይ ፒተር ካላያ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት የታዲኪራ የፍርድ ሂደት የሚካሄደው ወንጀሉ ከተፈጸመበት ቦታ አቅራቢያ በምትገኘው ምዙዙ በተሰኘች ስፍራ ነው። ነገር ግን ችሎቱ መቼ እንደሚጀመር ቀን አልተወሰነም።
ጥቅምት ወር አጋማሽ ፖሊስ በአንድ መቃብር ውስጥ በጅምላ የተቀበሩ 25 አስከሬኖችን ጨምሮ በአጠቃላይ 30 አስከሬኖችን በሰሜን ምዚምባ ወረዳ በሚገኝ ጫካ ውስጥ አግኝቷል።
አስከሬናቸው በቁፋሮ የወጣ ሲሆን የአስከሬን ምርመራ ቢካሄድም ስለ አሟሟታቸው ዝርዝር የወጣ መረጃ የለም።
ሁሉም አስከሬኖች በድብቅ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲወሰዱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደሆነ ተሰምቷል።
የአካባቢው ወጣቶች ደኑ ውስጥ የሚያውክ ሽታ እንዳለ መጠቆማቸውን ተከትሎ ነበር አስክሬኖቹ በቁፋሮ የተገኙት።
ይህ የጅምላ መቃብር ከተገኘ በኋላ በቅርብ ርቀት ሌላ የጅምላ መቃብር ተገኝቶ ተጨማሪ አራት አስክሬኖችን ፖሊስ አውጥቷል።
የማላዊ የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር ጃን ሴንዴዝ “በጣም የሚያሳዝን ነው። አስከፍቶናል። መንግሥታችን እንዲህ ያለ ድርጊትን በጽኑ ያወግዛል። ትክክል አይደለም። በጎ አይደለም” ሲሉ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረው ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም፣ ኢትዮጵያ ከማላዊ መንግሥት ጋር በመተባበር ስለ ክስተቱ ምርመራ እያደረገች ነው ሲሉ በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
አምባሳደር መለስ፣ በክስተቱ ሐዘን እንደተሰማቸው ገልጸው፣ የምርመራውን ውጤት ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉም መናገራቸው ይታወሳል።
ያለፈው ሰኔ የመንግሥታቱ ድርጅት ባወጣው መግለጫ በማላዊ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በርካታ የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙና ብዝበዛ እንደሚደርስባቸው ማስታወቁ አይዘነጋም።
ድዛሌካ በተሰኘው የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በወንዶች፣ በሴቶች እና በሕጻናት ላይ መጠነ ሰፊ ብዝበዛ እንደሚደርስ ይፋ የተደረገው በተባበሩት መንግሥታት የመድኃኒት እና የወንጀል ጽሕፈት ቤት (ዩኤንኦዲሲ) እና የማላዊ ፖሊስ ባደረጉት የጥምረት ክትትል ነው።
ማላዊ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከሚፈተኑ አገራት አንዷ ናት።
ከኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ሌሎም የአፍሪካ ቀንድ አገራት ወንዶች፣ ሴቶችና ሕጻናት ጭምር በማላዊ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ አውሮፓ እና አሜሪካ ለማቅናት ይሞክራሉ።
ጉዟቸው ግን በስቃይና በእንግልት የተሞላ ባስ ሲልም ለሞት የሚዳርግ ነው።












