ኢትዮጵያ በሰዎች ዝውውር ሲፈለግ የነበረውን ኤርትራዊ ለጣልያን አሳልፋ ሰጠች

ስደተኞች በባሕር ሲጓዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሰዎችን በማዘዋወር ወንጀል በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው ተመስገን ገብሩ ገብረመድኅን ኢትዮጵያ ውስጥ ተይዞ ለጣልያን ተላልፎ መሰጠቱ ተዘገበ።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የጣልያን የፍትሕ ሚንስትር ምንጭን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ኤርትራዊው ግለሰብ በሰዎች ዝውውር ወንጀል ለሁለት ዓመታት ሲፈለግ ነበር።

የሮይተርስ ምንጭ እንዳሉት፣ የ35 ዓመቱ ግለሰብ “ቀጠና ተሻጋሪ የሆና ስደተኞችን ከሰሜን አፍሪካ ወደ አውሮፓ የሚያዘዋውር ቡድን ቁልፍ አባል ነው”።

ባሳለፍነው ሳምንት ኔዘርላንድስ በዓለም አቀፍ ወንጀሎች በጥብቅ የምትፈልገው ኤርትራዊ የሰዎች አዘዋዋሪ ተወልደ ጎይቶም ከኢትዮጵያ ተላልፎ መሰጠቱ ይታወሳል።

በቅፅል ስሙ ወሊድ የሚባለው ተወልደ ጎይቶም፣ ለኔዘርላንድስ ተላልፎ ከመሰጠቱ በፊት፣ በሊቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በመዝረፍ፣ በማሰቃየት እንዲሁም ጭካኔ የተሞላባቸው አረመኔያዊ የሰዎች ዝውውር በመፈጸም ወንጀል በአምስት ክሶች የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ አሳልፎበት ነበር።

አሁን ለጣልያን ተላልፎ የተሰጠው ተመስገን ገብሩ ገብረመድኅን የተከሰሰው የዓለም አቀፍ የወንጀል ቡድን ውስጥ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በማካሄድ ነው።

በቁጥጥር ሥር የዋለውም በአዲስ አበባ አየር ማረፊያ እንደሆነ ተዘግቧል።

በሲሲሊ፣ ፓሌርሞ የተሰየሙ ዳኞች ተመስገን ገብሩ ገብረመድኅንን ጨምሮ ሌሎችም በሰዎች ዝውውር የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እአአ በ2020 ማዘዣ አውጥተው እንደነበር የሮይተርስ ዘገባ ይጠቁማል።

ግለሰቡ በኢንተርፖል ከሚፈለጉ መካከል አንዱ ሲሆን፣ የወንጀል ቡድኑ ውስጥ ያሉ ተባባሪዎቹ ወደሚንቀሳቀሱበት አውስትራሊያ እየተጓዘ ሳለ ነው በቁጥጥር ሥር የዋለው።

ባለፉት አሥርታት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በሜድትራኒያን ባሕር አቆራርጠው ጣልያን ገብተዋል። ጉዟቸው በእንግልት የተሞላ እንዲሁም ሕይወታቸውን እስከማጣት የሚያደርስ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ለሰው አዘዋዋሪዎች ከፍለው ነው የሚጓዙት።

የጣልያን ዐቃቤ ሕግ በሜድትራኒያን ባሕር የሚደረጉ የስደተኞች ዝውውሮች ላይ በርካታ ምርመራዎች እንደተከፈተ ቢዘገብም፣ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል።