ኢራን ከጥቃት የተረፈ የበለፀገ ዩራኒየም ልታገኝ እንድምትችል አንድ የእስራኤል ባለሥልጣን ተናገሩ

 የኢስፋሃን የኒውክሌር ማዕከል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሰኔ 15/2017 ዓ.ም. በአሜሪካ ጥቃት የተፈጸመበት የኢስፋሃን የኒውክሌር ማዕከል

ኢራን ባለፈው ወር በአሜሪካ ጦር ከተመቱባት ሦስት የኒውክሌር ማዕከላት ሕንጻዎች በአንዱ ስር የተቀበረውን የበለፀገ ዩራኒየም ማውጣት ትችላለች ብላ እስራኤል እንድምታምን አንድ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናገሩ።

ባለሥልጣኑ ለአሜሪካ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢራን ኢስፋሃን በተባለው ተቋም የበለፀገውን ዩራኒየም ለማውጣት እጅግ በጣም ከባድ እንደሚሆንባት እና ለማውጣት የምታደርገው ማንኛውም ሙከራ ከእስራኤል በኩል ሌላ ዙር ጥቃት እንሚያስከትልባት ገልጸዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በሰኔ ወር አሜሪካ በኢራን ላይ የፈጸመችው የአየር እና የሚሳዔል ጥቃት የአገሪቱን የኒውክሌር ተቋሞች "አውድሞታል" ሲሉ ደጋግመው ቢናገሩም፣ አንዳንድ የአሜሪካ የስለላ ተቋማት ግን የበለጠ ጥንቃቄ የተሞላበት አመለካከት ነው ያላቸው።

ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመሥራት ፍላጎት እንደሌላት በተደጋጋሚ ስታስተባብል፤ ዩራኒየም የምታበለጽገው ለሰላማዊ ዓላማ ነው ብላለች።

በዋሽንግተን ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት አጭር መግለጫ ላይ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የእስራኤሉ ከፍተኛ ባለሥልጣን እንዳሉት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አብዛኛው የኢራን የበለፀገ ዩራኒየም የተቀበረው ኢስፋሃን ውስጥ ነው።

ይህ የኢራን የኒውክሌር ግንባታ ማዕከል የወደመው አሜሪካ ሰኔ አጋማሽ ላይ ከባሕር ሰርጓጅ መርከቦች ላይ በተተኮሱ ክሩዝ ሚሳዔሎች ተመትቶ ነው።

ይሁን እንጂ በግምገማቸው ላይ ያሉ ስጋቶችን ያልጠቀሱት ባለሥልጣኑ፣ ነገር ግን ኢራን ጥቃት ከተፈጸመበት የኒውክሌር ተቋም ማንኛውም ቁሳቁስ ለማውጣት የሚሞክሩ ከሆነ ሊታይ ይችላል ብለዋል።

እንደ ባለሥልጣኑ ገለጻ የእስራኤል ግምገማ ኢራን ላይ በተፈጸመው ጥቃት ምክንያት የአገሪቱ የኒውክሌር መርሃ ግብር ለሁለት ዓመታት ወደ ኋላ ተመልሷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ እና የአስተዳደራቸው አባላት የኢራን የኒውክሌር ተቋማት በተፈጸማባቸው ጥቃት ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ሲሉ ጽኑ አቋም ይዘዋል።

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ አና ኬሊ ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን በላኩት መግለጫ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ ብዙ ጊዜ እንደተናገሩት አሜሪካ በኢራን ላይ በፈጸመችው ጥቃት የኒውክሌር ተቋማቷ ሙሉ በሙሉ ተደምስሰዋል" በማለት "ለቆራጥ መሪነታቸው ምስጋና ይግባውና መላው ዓለም ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው" ስትል እርምጃውን ገልጸዋለች።

የአሜሪካ የስለላ ተቋማት ግምገማ ግን ውድመቱን በተመለከተ ጥንቃቄ የተሞላበት አቋም ነው ያለው።

ሾልኮ የወጣ የመከላከያ የደኅንነት ተቋም መረጃ ዘገባ እንዳመለከተው በፎርዶ፣ በናታንዝ እና ኢስፋሃን ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ነገር ግን ሙሉ በሙሉ አለመውደማቸውን አመልክቷል።

በሰኔ ወር መገባደጃ ላይ የሲአይኤ ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ ለአሜሪካ ሕግ አውጪዎች እንደተናገሩት የኢራን ብቸኛ የብረታ ብረት ዩራኒየም ለማምረት የሚያስችል ተቋም መውደሙ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የመገንባት አቅም እንዳሳጣት ተናግሯል።

በሰኔ ወር ማብቂያ ላይ የሲአይኤ ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ ለአሜሪካ ሕግ አውጪዎች እንደተናገሩት የኢራን ብቸኛ የዩራኒየም ማምረቻ ተቋም በመውደሙ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የመገንባት አቅም እንደሌላት አስታውቀዋል።

የዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ተቋም ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ለሲቢኤስ እንደተናገሩት ዒላማ የተደረጉት ሦስቱ የኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች "በከፍተኛ ደረጃ ወድመዋል" ነገር ግን የተወሰነ ክፍላቸው "አሁንም ቆሟል" ብለዋል።

"በግልጽ ለመናገር አንድ ሰው እንዲሁ ተነስቶ ሁሉም ነገር ጠፍቷል የተረፈ ነገር የለም ማለት አይችልም" ብለዋል ፍሮሲ።

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማህሙድ ፔዜሽኪያን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ለወግ አጥባቂው ተንታኝ ተከር ካርልሰን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የአገራቸው የኒውክሌር ተቋማት "በከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል" ብለዋል።

"ስለዚህም ወደ ተቋማቱ የምንደርስበት ሁኔታ የለም" በማለት በአሁኑ ጊዜ ስለደረሰው ጉዳት ግምገማ ለማድረግ የሚቻልበት ዕድል እንደሌለ አመልክተዋል።