ዩኬ በትናንሽ ጀልባ ድንበር ለሚያቋርጡ ጥገኝነት አልሰጥም አለች

ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ ይሆናል የተባለው ሕግ በትናንሽ ጀልባ ተሳፍረው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለሚገቡ ስደተኞች ጥገኝነት ሊከለክል ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሺ ሱናክ አምስት ቅድሚያ ከሚሰጧቸው ርዕሶች አንዱ በጀልባ ተሳፍረው የሚመጡ ስደተኞች ጉዳይ ነው።

የሰብዓዊ መብት ማሕበር የሆነው የብሪታኒው ቀይ መስቀል አዲሱን ዕቅድ “አሳሳቢ” ብሎታል።

የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሱዌላ ብሬቨርማን ቀጣይ ማክሰኞ አዲሱን ዕቅድ ይፋ እንደሚያደርጉት ይጠበቃል።

አሁን ባለው ሕግ መሠረት ጥገኝነት ጠያቂዎች ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ ዩኬ ውስጥ መቆየት ይችላሉ። በአዲሱ ሕግ መሠረት ግን ዩኬ መቆየት ሳይሆን ሩዋንዳ አሊያም ሌላ ሶስተኛ ሃገር ይላካሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሺ ሱናክ እሑድ ዕለት ሜይል ለተሰኘው ጋዜጣ፤ “ወደዚህ በሕገ-ወጥ መንገድ ከመጣችሁ፤ እንደትቆዩ አይፈቀድላችሁም። እንዳትሳሳቱ” ሲሉ ተናግረዋል።

ሱናክ በሚቀጥለው አርብ ለዩኬ-ፈረንሳይ ስብሰባ ወደ ፓሪስ ያቀናሉ። ከኢማኑኤል ማክሮን ጋር የሚደረገው ስብሰባ በፈረንጆቹ ከ2018 በኋላ የመጀመሪያው ነው።

ሁለቱ መሪዎች በጀልባ የሚመጡ ስደተኞች ጉዳይ የመወያያ ርዕሳቸው ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ በጀልባ አቋርጠው ዩኬ የሚገቡ ስደተኞች “ለአንዴና ለመጨረሻጊዜ ለማስቆም” ቃል ገብተዋል።

“ሕገ-ወጥ ጥገኝነት ለብሪታኒያ ግብር ከፋዮች ፍትሐዊ አይደለም። በሕጋዊ ለሚመጡ ስተደኞችም ፍትሐዊ አይደለም። ወንጀለኞች በሕገ-ወጥ መንገድ ሰው እንዲያስተላልፉ መፍቀዱም ፍትሐዊ አይደለም። ይሄን አስቆማለሁ ብዬ ቃል የገባሁት እፈፅማለሁ” ሲሉ ለሜል ጋዜጣ ተናግረዋል።

የብሪታኒያው ቀይ መስቀል ማሕበር አዲሱ መመሪያ ስደተኞች ሕይወታቸውን ሰጥተው ከመሰደድ ወደኋላ የሚያደርጋቸው አይደለም ይላል።

ፍሪደም ፍሮም ቶርቸር የተሰኘው ለስደተኞች እርዳታ የሚሰጥ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ደግሞ አዲሱን መመሪያ “ተግባራዊነት የሚጎድለው” ብሎታል።

አዲሱ የመንግሥት መመሪያ ግልፅ አይደለም። ወደ ሩዋንዳ ስደተኞችን የመመለሱ ሥራ ለጊዜው ቆሟል። የዩኬ መንግሥት ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ስደተኞችን ስለመመለስ የገባው ስምምነትም የለም።

ባለፈው ዓመት የዩኬ መንግሥት መመለሻ በሌለው ቲኬት ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ስምምነት ገብቶ ነበር።

ነገር ግን ይህ ስምምነት ከፍተኛ ተቃውሞ ከገጠመው በኋላ ለጊዜው እንዲቆም ተደርጓል።

የስምምነቱ ተቃዋሚዎች ሩዋንዳ ለስደተኞች ምቹ ሃገር አይደለችም፤ አልፎም ስምምነቱ ሰብዓዊ መብት ጥሷል ሲሉ ይከራከራሉ።

መንግሥት በእንግሊሽ ቻናል በኩል በጀልባ የሚመጡ ስደተኞች አስቆማለሁ ቢልም እስካሁን ይህ አልተሳካለትም።

በፈረንጆቹ 2022 ከ45 ሺህ በላይ ስደተኞቭ በእንግሊዝ ቻናል በኩል አቋርጠዋል።