90+7 የተቆጠረ ጎል፡ የአልሸነፍ ባይነት ምልክት ወይስ ተዘናግተው እንደነበረ ማሳያ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትናንት ምሽት በኤሚሬትስ ስታዲየም የነበረው ‘ድራማዊ ክስተት’ በስታዲየሙ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ክስተት ነው እየተባለ ነው።
'ድራማዊው ክስተት’ እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው የባለሜዳዎቹ በጨዋታው መጀመሪያ ዝንጉነት ወይስ የአልሸነፍ ባይነት ተጋድሎ የሚለው ግን ደጋፊዎችን ያከራከረ ነው።
በ26ኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ አርሰናል በርንዝመዝን በኢሚሬትስ አስተናግዶ ነበር።
ታዲያ ባለሜዳዎቹ መድፈኞች 2 ለ 0 ከመመረት ተነስተው በባከነ በጭማሪ ሰዓት ላይ ባስቆጠሩት የማሸነፊያ ጎል ተጋጣሚያቸውን 3 ለ 2 መርታት ችለዋል።
የአርሰናል መዘናጋት ‘ወንጀል’ ነበር
ለጎል ዶት ኮም የሚጽፈው የአርሰናል ተንታኙ ክሪ ዊቲ ጨዋታው በተጀመረ ገና 9 ሴኮንዶ ላይ የተጋጣሚ ቡድኑ አጥቂ ቢሊንግ በቀላሉ ጎል እንዲያስቆጠር መፈቀዱ ‘ወንጀል’ ነው ይላል።
ጨዋታው እንደተጀመረ ነበር የበርንመዝ ተጫዋቾች ኳሷን ወደ አርሰናል የግብ ክልል ይዘው ሄደው በቀላሉ ጎል ማስቆጠር የቻሉት።
ኳስ ለጎል አስቆጣራዊ ቢሊንግ ስትሻገር የአርሰናል ተከላካዮች ዝንጉ ሆነው ነበር። ተከላካዩ ገብርኤል ማጋሌዥ ኳስ በእግሩ ስር አልፋ ወደ ጎል አስቆጣሪ ቢሊንግ እንድትሄድ ፈቅዶ ነበር። ሌላኛው የአርሰናል ተከላካይ ዊሊያም ሳሊባም ጎል አስቆጣሪውን አልያዘመው ነበር።
ይህ ደካማ እና አደገኛ የነበረው የአርሰናል አጀማመር ቡድኑ ትልቅ ዋጋ ማስከፈል ይችል ነበር ይላል ዊቲ።
‘አልሸነፍ ባይ መድፈኞች’
መድፈኞቹ የመጀመሪያው ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ኳስ ተቆጣጥረው አጥቅቶ በመጫወት ጎል ለማስቆጠር ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገው ነበር።
በድጋሚ ጎል ማስቆጠር የቻሉት ግን ላለመወርድ እየታገሉ ያሉት በርንዝመዞች ነበሩ። ማርኮ ሴኔሲ ከማዕዘን ምት የተሻገረችውን ኳስ በጭንቅላቱ በግሩም ሁኔታ ኳስን ከመረብ ሲያገናኝ መድፈኞቹ አንገት ባንገት ከሚከተሏቸው ሲቲዎች ያላቸውን የ5 ነጥብ ርቀት ማስጠበቅ አይልቻሉም የሚል እምነትን ፈጥሮ ነበር።
ይሁን እንጂ እስከ 60ኛው ደቂቃ ድረስ 2ለ0 ሲመሩ የነበሩት መድፈኞች በደጋፊዎቻቸው ድጋፍ ታጅበው አጥቅተው በመጫወት በቶማስ ፓርቴ አማካይነት ነብስ የዘራች ጎልን በ62ኛ ደቂቃ ላይ ማስቆጠር ቻሉ።
ከዚህ በኋላ ነበር ሚኬል አርቴታ አማካዩን ሪስ ኔልሰንን ወደ ሜዳ ካስገባ በኋላ ሁኔታዎች መቀያየር የጀመሩት።
ፓርቴ ነብስ የዘራችውን ጎል ካስቆጠረ ከ8 ደቂቃዎች በኋላ ተከላካዩ ቤን ዋይት ከሪስ ኔልስን የተሻገረለትን ኳስ ወደ ጎል ቀየራት።
ቤን ዋይት ለመጀመሪያ ግዜ ለአርሰናል ያስቆጠራት ጎል ቡድኑን አቻ ከማድረጓም በላይ መድፈኞቹ ይህን ጨዋታ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ አማላካች ነበረች።
ይሁን እንጂ መድፈኞቹ አቻ ከሆኑ በኋላ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የማሸነፊያ ጎል ለማስቆጠር 27 ደቂቃዎችን መጠበቅ ነበረባቸው።
“ኳሷ ወደ እኔ ስትመጣ፤ ‘ምናለህ አንድ ዕድል ባገኝ’ ብዬ እያሰብኩ ነበር። በቀኝ እግሬ ተቆጣጠርኩት ገዛ ወደ ግራ እግሬ መጣ። በጣም ደስተኛ ነኝ” ሲል በ90+7 ደቂቃ ላይ ለአርሰናል የማሸነፊያውን ድንቅ ጎል ያስቆጠረው ኔልሰን ለቢቢሲ ስፖርት ተናግሯል።












