አውስትራሊያ 220 ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ከአሜሪካ ልትገዛ ነው፣ ቻይና ተቃወመች

የፎቶው ባለመብት, U.S. NAVY
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት 220 ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች ለአውስትራሊያ በሽያጭ እንዲተላለፉ ሲወስን ቻይና ተቃውሟዋን አሰማች።
ይህን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ተግባራዊ የሚሆነው የአሜሪካ ኮንግረስ ይሁንታ የሚፈልግ ሲሆን በዚህም 895 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ታገኛለች።
ቶማሆውክ የተባለው ሚሳኤል አውስትራሊያ ከአሜሪካ በሚቀርብላት ቨርጅን-ክላስ በተሰኘው ሰርጓጅ መርከብ ላይ የሚጠመድ ነው።
የአውስትራሊያ መከላከያ ሚኒስትር ሪቻርድ ማርልስ ሚሳኤሉ ለአገራቸው “ትልቅ አቅምን” የሚፈጥር ነው ብለዋል።
“ከባሕር ዳርቻዎቻችን ባሻገር የአውስትራሊያን ደኅንነት የምንጠብቀው በዚህ መንገድ ነው” ሲሉ ለአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ የሚሳኤል ሽያጩ የአውስትራሊን አቅም ከፍ ከማድረጉም በላይ በጋራ ጉዳዮች ላይ ከአሜሪካ እና ከአጋር አገራት ጋር አብሮ የመሥራት አቅምን ከፍ ያደርጋል ብሏል።
አውስትራሊያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ መካከል የተደረሰው ወታደራዊ ስምምነት በቀጠናው የቻይናን እንቅስቃሴ እና መስፋፋት የሚገዳደር ነው።
ከቀናት በፊት ይፋ የተደረገውን የሦስቱ አገራት ወታደራዊ ስምምነትን ቻይና አጥብቃ ተቃውማለች። ቤይጂንግ የሦስቱ አገራት ስምምነት የኑክሌር ጦር መሳሪያ የመታጠቅ እሽቅድድም አደጋን ይፈጥራል ብላለች።
ከቻይና በተጨማሪ በርካታ አንጋፋ የሚባሉ የአውስትራሊያ ፖለቲኞች ስምምነቱን ኮንነዋል።
የቀድሞ የአውስራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፖል ኬቲንግ ውሳኔው ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የሠራተኛ ፓርቲ መንግሥት ትልቁ ስህተት የሆነ ውሳኔ ነው ሲሉ የሦስቱን አገራት ወታደራዊ ስምምነት ተችተዋል።
ሌላኛው ማልኮም ተርንቡል የተባሉ የቀድሞ መሪ ደግሞ የዩናይትድ ኪንግደም ምጣኔ ሃብት መሠረታዊ የሆነ ችግር እንዳለበት በመጥቀስ አገሪቱ ዘላቂ አገር መሆኗ አጠራጣሪ ነው ብለዋል።












