ግብፅ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ “ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው” ማለቷ ኢትዮጵያን አስቆጣ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Foreign Affairs
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹኩሪ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ “ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው” ማለታቸው ኢትዮጵያን አስቆጣ።
የኢትዮጵያ መንግሥት “ኃላፊነት የጎደለው ነው” ባለው ግብፅ መግለጫ መቼ እንደተሰጠ ግልጽ ባይሆንም፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን የሳሚ ሹክሪ መግለጫ “ሌላ የግብፅ ማስፈራሪያ ነው” በማለት አጣጥሎታል።
ባለፈው ሳምንት ሳሚ ሹኩሪ የግድቡ ግንባታ በግብፅ እና በሱዳን ፍላጎት ላይ ጉልህ የሆነ ተጽእኖ እንደማያሳድር ኢትዮጵያ ማረጋገጥ የማትችል ከሆነ ግብፅ የሕዝቧን ፍላጎት ታስከብራለች ብለው ነበር።
ሳሚ ሹኩሪ በካይሮ ከኬንያው አቻቸው አልፍሬድ ሙቱዋ ጋር የካቲት 30/2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ “ኢትዮጵያ የሁለቱን የታችኛው ተፋሰስ አገራት ፍላጎትን ከግምት ማስገባት እና ከባድ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ አለባት” ስለማለታቸው የግብፅ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ሳሚ ሹኩሪ በዚሁ መግለጫቸው፤ “ይህ የማይሆን ከሆነ ግብፅ ያለምንም ጥያቄ የሕዝቧን ፍላጎት ታስከብራለች እንዲሁም ወደዚህ የሚያመራ እርምጃ ትወስዳለች” ብለው ነበር።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ሐሙስ መጋቢት 07/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ “የግብፅ ማስፈራሪያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር እና የአፍሪካ ኅብረት ድንጋጌን በግልጽ የሚጥስ ከመሆኑም በተጨማሪ፤ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን የተፈራረሙትን የመርሆች ስምምነትን የሚተላለፍ ነው” ብሏል።
ግብፅ በማስፈራራት ፍላጎቷን ልታሳካ አትችልም ያለው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ግብፅ የዓለም አቀፉ የግንኙነት መርሆችን እየጣሰች መሆኗን ልብ ሊሉ ይገባል ብሏል።
“የዓለም አቀፍ ሕግን ተከትሎ በመከባበር እና በመተማመን በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ሦስቱ አገራት ድርድር ቢያደርጉ መግባባት ላይ ሊደረስ ይችላል።”
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጨምሮም፣ ኢትዮጵያ አሁንም በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ሁሉንም አሸናፊ የሚደርግ ስምምነት እንዲደረስ ዳግም ጥሪ ታደርጋለች ብሏል።
ሕዳሴ ግድብ በአረብ ሊግ አጀንዳ
ባለፈው ሳምንት ግብፅ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የአረብ ሊግ ምክር ቤት ቋሚ አጀንዳ እንዲሆን ማስደረጓ ካይሮን እና አዲስ አበባን ያወዛገበ ሌላኛው ጉዳይ ነበር።
የምክር ቤቱን ፕሬዝዳንትነት ከሊቢያ ተወካይ የተረከቡት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹኩሪ፤ የአረብ ሊግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአረብ ሊግ ምክር ቤት ቋሚ አጀንዳ እንዲሆን አስወስነዋል።
ሳሚ ሹኩሪ የግድቡ ጉዳይ ቋሚ አጀንዳ እንዲሆን መወሰኑ የአረብ ሊግ የግብፅ እና የሱዳን መብቶችን ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለው ነበር።
ሽኩሪ አዲስ አበባ፣ ከካይሮ እና ከካርቱም ጋር አሳሪ የሆነ ሕጋዊ ስምምነት ላይ ሳትደርስ በግድቡ ግንባታ፣ ሙሌት እና ሥራ ቀጥላበታለች ሲሉ መክሰሳቸው ይታወሳል።
ለዚህም አሁን ግድቡ የአረብ ሊግ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ በመሆኑ ኢትዮጵያ፣ የግብፅ እና የሱዳንን ፍላጎት በመቀበል አዎንታዊ እርምጃ እንድትወስድ የሚያሳስብ ነው ብለው ነበር።
ይህንን የአረብ ሊግ ውሳኔን ተከትሎ ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ምላሽ የሰጠች ሲሆን፣ የአባይ ጉዳይ በአገራቱ መካከል በሚካሄድ ውይይት የሚፈታ መሆኑን በመጥቀስ የሊጉን ውሳኔ ተቃውማለች።

የፎቶው ባለመብት, PMO
የግደቡ አሞላል እና ሥራ እንዲሁም የአባይ ወንዝ አስተዳደር እና አጠቃቀም ለሚመለከታቸው የአፍሪካ አገራት መተው ያለበት ጉዳይ ነው ያለው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፤ የአባይ ወንዝ እና የተፋሰሱ አገራት መገኛቸው አፍሪካ ስለመሆኑ ለሊጉ ማስታወስ አይኖርብንም ብሎ ነበር በመግለጫው።
110 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ግብፅ፤ ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ የውሃ ድርሻዬን ይቀንሳል የሚል ስጋት አላት።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሕዝቦቿ 55 በመቶ የኤሌክትሪ ኃይል እንደማያገኙ በማስታወስ፤ ሁሉን ተጠቃሚ በሚያደርግ መርህ ላይ በመመርኮዝ ግድቡን በመገንባት የውሃ ደርሻዬን የመጠቀም መብት አለኝ ትላለች።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ከ10 ዓመታት በፊት ጀምሮ ግብፅ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ በግድቡ አሞላል እና ኦፕሬሽን ከስምምነት ለመድረስ በርካታ ድርድሮችን ቢያደርጉም ይህ ነው የተባለ ውጤት አልተመዘገበም።
ከጥቂት ወራት በፊት የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 83 በመቶ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌትም መጠናቀቁን ይፋ ተደርጎ ነበር።
ግድቡ በአሁኑ ወቅት በሁለት ተርባይኖች አማይካይነት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ሥራ ጀምሯል።












