ፊፋ የአፍሪካ እግር ኳስ ማኅበርን መቆጣጠር የሚፈልገው ለምን ይሆን?

የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ

ከእግር ኳስ ታግደው የነበሩት የቀድሞው የአፍሪካ እግር ኳስ ማኅበራት (ካፍ) ፕሬዝዳንት፤ “አፍሪካን የሚቆጣጠራት ፊፋ” ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ማዳጋስካራዊው አህመድ አህመድ ለሁለት ዓመት ያህል እግር ኳስ ያለበት ድርሽ እንዳይሉ ታግደው ነበር።

እግዳቸውን ጨርሰው የተመለሱት አህመድ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ ፊፋ አፍሪካን የሚፈልጋት ለስትራቴጂ ነው ይላሉ።

የ63 ዓመቱ አህመድ የካፍ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት በፈረንጆቹ 2017 ሲሆን፣ ለሦስት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ የፊፋን ሕግ ጥሰዋል ተብለው ነው ከመንበራቸው የወረዱት።

የተጣለባቸው እግድ ያበቃው አህመድ የእናት አገራቸው ማዳጋስካርን እግር ኳስ ለማሳደግ እንደሚሠሩ ይናገራሉ።

በሌላ በኩል የቀድሞ ጓዳቸው የነበሩት የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ያለማንም ተቀናቃኝነት ድጋሚ የዓለም እግር ኳስ ማኅበር አለቃ ሆነው ተመርጠዋል።

“ፊፋን እመራለሁ” ብሎ የመጣ ዕጩ ባለመገኘቱ፤ ኢንፋንቲኖ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ውስጥ በተካሄደው ምርጫ ሥነ ሥርዓት አሸንፈዋል።

የፊፋ ፕሬዝዳንት ምርጫ ዕለተ ሐሙስ መጋቢት 07/2015 ዓ.ም. በሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ ተካሂዷል።

አህመድ እንደሚሉት ከእግር ኳስ እንዲታገዱ የተደረጉት የኢንፋንቲኖን ትዕዛዛት ባለመቀበላቸው ነው።

“እገዳዬ ፖለቲካዊ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ስፖርት የተናገሩት አህመድ፣ ሞሮኮ ውስጥ ፊፋ እና ካፍ የመረረ ግጭት ውስጥ ገብተው እንደነበር ያወሳሉ።

የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ካፍ ከዓለም አቀፉ ተቋም ፊፋ ጋር ያለውን ቁርኝት ሟቋረጥ መፈለጉን ተከትሎ ኢንፋንቲኖ ስብሰባውን ረግጠው ወጥተው ወደ አየር ማረፊያ ሄደው ነበር።

ሴኔጋላዊቷ ዋና ፀሐፊ ፋጥማ ሳሞራ የአፍሪካ እግር ኳስ ተወካይ ሆነው ለስድስት ወራት ማገልገላቸውም የሚታወስ ነው።

የፊፋ ዋና ፀሐፊ ፋጥማ ሳሙራ፣ የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያን እንፋንቲኖ እና የቀድሞው የካፍ ፕሬዝዳንት አህመድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፊፋ ዋና ፀሐፊ ፋጥማ ሳሙራ፣ የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያን እንፋንቲኖ እና የቀድሞው የካፍ ፕሬዝዳንት አህመድ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ምንም እንኳ ፋጥማ በጣም አግዛን የነበረ ቢሆንም ከስድስት ወራት በላይ እርዳታ ስላልፈግን አቋረጥነው። ይሄ ደግሞ ኢንፋንቲኖን አስቆጣ” ይላሉ አህመድ።

“ኢንፋንቲኖ ስብሰባውን ረግጦ ሲወጣ አንዳንድ ሰዎች ‘የሞት ፊርማ ነው የፈረምከው’ ሲሉኝ ነበር። በእግር ኳስ ደግሞ የሞት ፊርማ ምንድነው? የሥነ ምግባር ኮሚቴ ብለው አቋቁመው እሱን በመጠቀም አስወገዱኝ።”

ካፍ፤ ከፊፋ የመጣለትን ምክረ-ሐሳብ አልቀበልም ባለ በአንድ ወሩ አህመድ ሥነ ምግባር ሳይጥሱ አልቀሩም ተብለው ምርመራ ተከፈተባቸው።

መቀመጫውን ዙሪክ ያደረገው ፊፋ ከአንድ ውስጥ አዋቂ በደረሰኝ መረጃ መሠረት ነው በማለት ነበር ምርመራ የጀመረው።

በፈረንጆቹ ኅዳር 2020 የፊፋ የሥነ ምግባር ኮሚቴ፤ አህመድን የአምስት ዓመት እግድ እና የ200 ሺህ ዶላር ቅጣት ጣለባቸው።

ኮሚቴው አህመድ ታማኝነታቸውን አጓድለዋል፣ ስጦታ ሰጥተዋል እንዲሁም ተቀብለዋል፤ መንበራቸውን በዝብዘዋል፤ አልፎም ለተለያዩ ፕሪጀክቶች የሚውል ገንዘብን አዛብተዋል ሲል ነው የቀጣቸው።

ነገር ግን በ2021 ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የግልግል ዳኝነት (ካስ) ቅጣታቸውን በግማሽ አቀለላቸው። ይህን ተከትሎ አህመድ “ቅጣቱ ድሮም ፖለቲካዊ” ነበር ማለት ጀመሩ።

“ቅጣቱ መቅለሉ የተወቀስኩባቸው ነገሮች ለትርጉም መዛባት የተጋለጡ መሆኑን ያሳያል” ይላሉ።

በምላሹ ፊፋ በፃፈው ደብዳቤ አህመድ በፊፋ እና በግልግል ዳኝነት ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል፤ ኢንፋንቲኖ ናቸው ያስወገዷቸው የሚሉ ወሬዎች ሐሰተኛ ናቸው የሚል መግለጫ አወጣ።

የፊፋው ቃል አቀባይ ብራያን ሰዋንሰን ፊፋ ባለፉት ዓመታት ያመጣቸውን ለውጦች ጠቅሰው፤ “ድርጅቱ ያቋቋመው የሥነ ምግባር ኮሚቴ ነፃ እና ገለልተኛ ነው” ሲሉ ተናገሩ።

“የእሱን [የኢንፋንቲኖን] ስም ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱ፤ ፊፋ አሁን ውጤታማ መሆኑን የሚቆረቁራቸው ናቸው” ሲሉ አከሉ።

አህመድ እና ኢንፋንቲኖ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አህመድ እና ኢንፋንቲኖ

“ፊፋ አፈናውን ማቆም አለበት”

የቀድሞው የፊፋ ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተርን ጨምሮ በርካቶች፣ ፊፋ አፍሪካ ውስጥ ‘ቅኝ ግዛት እያራመደ ነው’ ሲሉ ይወቅሱታል።

ፊፋ አባላቱ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ እንዳይገባባቸው ቢያግድም፣ በአፍሪካ ጉዳይ ግን ጣልቃ እየገባ ነው ይላሉ ተቺዎች።

አሁን ሥልጣን ላይ ካሉ አሊያም ከቀድሞ የካፍ ባለሥልጣናት ከተወሰኑት በስተቀር ስለፊፋ የሚናገሩ ማግኘት ከባድ። ብዙዎች እንደሚገምቱት ሰዎች ስለፊፋ ምንም የማይሉት የሚደርስባቸውን በመፍራት ነው።

ሁለት ምሳሌዎች እናንሳ። ሁለቱም ከፋጥማ ሹመት ጋር የሚያያዙ ናቸው።

ሴኔጋላዊቷ ዋና ፀሐፊ ወደ ሥልጣን ሲመጡ በርካታ የካፍ ባለሥልጣናት አስተያየት ቢሰጡም በይፋ ስማቸው እንዲነሳ አልፈለጉም። ከአንድ ሰው በቀር።

የጊኒ-ቢሳው እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ማኑዌል ናሺሜንቶ፤ አብዛኛዎቹ የካፍ አባላት ሹመቱን እንደሚቃወሙት በወቅቱ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ማኑዌል “ካፍ የአፍሪካ ነው። የሌላው ዓለም እግር ኳስ ማኅበራት የማይቀበሉትን እኛ ለምን እንቀበላለን?” ሲሉ ጠየቁ።

ከአንድ ዓመት በኋላ የጊኒ-ቢሳው እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ ሊካሄድ አንድ ቀን ሲቀረው ማኑዌል በፊፋ የአስር ዓመት እገዳ ተጣለባቸው።

ፊፋ፤ ፕሬዝዳንቱ በአገራቸው በአንድ ወንጀል ውስጥ ተሳትፈዋል ሲል ነው ያገዳቸው። የአገሪቱ ፖሊስ ግን ምርመራ አድርጎ ሰውየው ነፃ ናቸው ማለቱ ይታወሳል።

ማኑዌል አስር ዓመት ሲታገዱ፤ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የጦር ወንጀለኛ ናቸው ተብለው የተፈረደባቸው የመካከለኛ አፍሪካ ሪፐብሊክ እግር ኳስ ፕሬዝደንት ፓትሪስ ኤድዋርድ ለሰባት ዓመት ነው የታገዱት።

ሌላኛው ምሳሌ በፊፋ የሥነ ምግባር ኮሚቴ የግማሽ ሚሊዮን ዶላር ቅጣት የተላለፈባቸው የላይቤሪያው ሙሳ ቢሊቲ ጉዳይ ነው።

የመሰላቸውን በመናገር የሚታወቁት የቀድሞው የካፍ ሥራ አስፈፃሚ አባል፤ ለኢንፋንቲኖ ቅርብ የሆኑ ሰዎች “የፋጥማን ሹመት ከደገፍክ ቅጣቱ ይነሳልሃል” ሲሉ ነግረውኛል ይላሉ።

“ሰዎቹ ‘ኢንፋንቲኖን ከተቃወምክ እንቀጣሃለን’ አሉኝ። እኔ ደግሞ መጥታችሁ የአፍሪካን እግር ኳስ ከምትወሰዱ መቀመቅ መውረድ እመርጣለሁ አልኳቸው” ሲሉ በአንድ ወቅት ለቢቢሲ ስፖርት ተናግረው ነበር።

“ፊፋ አፈናውን ማቆም አለበት” ይላሉ ሙሳ።

ሙሳ፤ ምንም እንኳን በፊፋ የተቀጡት የካቲት 2019 ቢሆንም ቅጣት የተላለፈባቸው ግን በይፋ ወጥተው ፊፋን በተቃወሙ በሳምንቱ ማለትም ወር ሐምሌ ነበር።

“አንድ ሰው ከተቃወመ በቀጣዩ ቀን ከስድስት ዓመት በፊት ጥፋት ፈፅሞ ነበር ብለህ ትቀጣዋለህ። ስለዚህ እስካልተቃወመ ድረስ ያጠፋው ጥፋት ምንም ማለት አይደለም ማለት ነው?” ይላሉ።

በሌላ በኩል የሴራ ሌዮን እግር ኳስ ፕሬዝዳንት ኢሻ ጆሃንሰን ለስምንት ዓመታት ያህል ምርጫ ሳያካሂዱ መንበራቸውን እንደተቆናጠጡ አሉ። ነገር ግን የፊፋ ሕግ በየአራት ዓመቱ ምርጫ መካሄድ አለበት ይላል።

የአፍሪካ 54 አገራትን በአባልነት የያዘው እና 54 ድምፅ ያለው ካፍ በዓለም ትልቁ የእግር ኳስ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ነው። ከካፍ ቀጥሎ ትልቅ ድምፅ ያለው የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ነው።

ስለዚህ ፊፋ የአፍሪካ እግር ኳስ ማኅበራትን ያዘ ማለት ከፍተኛ ድምፅ ያዘ ማለት ነው።

“የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበርን እንደፈቀዱ ማሾፈር ስለማይችሉ አፍሪካን ለድምፅ ሲሉ ይይዟታል” ይላሉ አሕመድ።