በየጨዋታው 22 ሺህ ፓውንድ እየተቀጣ የፈረንሳይ ሊጉን ክለብ የሚመራው ወጣቱ አሠልጣኝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዊል ስቲል በሚኖርበት አካባቢ ወጣ ብሎ አስቤዛ መሸመት ከፈለገ ለፎቶ ተዘጋጅቶ መውጣት አለበት።
የአድናቆት አጭር የፅሑፍ መልዕክት እና ኢሜይል የሚልኩለት፤ በየመንገዱ ፎቶ አብረን እንነሳ የሚሉት ሰዎች እየተበራከቱ መጥተዋል።
ቤልጂየም የተወለደው እንግሊዛዊ የፈረንሳዩ ዋና ሊግ ቡድን የሆነውን ራንስ አሠልጣኝ ነው።
ዊል ስቲል፤ የሰሜን ምሥራቃዊ ፈረንሳዩ ክለብ አሠልጣኝ ሆኖ የተሾመው ባለፈው ጥቅምት የቀድሞው አሠልጣኝ ኦስካር ጋርሺያ ከተባረሩ በኋላ ነው።
ስቲል፤ ራንስን ማሠልጠን ከጀመረ ወዲህ ክለቡ ሽንፈት ገጥሞት አያውቅም። ሁለት ጊዜ ከሊጉ መሪ ፓሪስ ሴይን ዠርሜይን ገጥሞ አቻ ወጥቷል።
ራንስ፤ ስድስት ጊዜ የሊግ አንድ ዋንጫን ማንሳት የቻለ ቡድን ነው። በፈረንጆቹ 1959 በአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ ፍፃሜ ከሪያል ማድሪድ መጫወቱም የክለቡ ትልቅ ታሪክ ነው።
ሽንፈት ካጋጠመው ቆየት ያለው ራንስ፣ አሁን በሊግ 1 አስረኛ ደረጃን ተቆናጦ ተቀምጧል።
“ሜዳ ላይ ያለውን ጭንቀት እወደዋለሁ። ከውጭው ዓለም የሚመጣብኝን ጫና ለመርሳት እሞክራለሁ” ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።
የ30 ዓመቱ ዊል ስቲል በአውሮፓ ትላልቅ ሊጎች በዕድሜ ትንሹ አሠልጣኝ ነው።
“ባለፉት ጥቂት ወራት ስልኬ ያለእረፍት ያቃጭላል። አስቤዛ ልሸምት ወጣ ካልኩኝ ሰዎች ለፎቶ ይጠይቁኛል። የሥራው አንዱ አካል ስለሆነ ይህ መሆኑ አይረብሽኝም።”
ምንም እንኳ ዝናው እየናኘ በክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ ተወዳጅነቱ እየጨመረ ቢመጣም፣ በእግር ኳስ ሁኔታዎች እንዴት በቅፅበት ሊቀየሩ እንደሚችሉ አይዘነጋም።
ዊል ስቲል እንደሌሎች አሠልጣኞች የተለመደውን መንገድ ተከትሎ አይደለም ወደሥራው የመጣው።
ሼል ለተሰኘው ነዳጅ ማደያ ይሠሩ የነበሩት እንግሊዛዊ አባቱ ወደ ቤልጂየም ካቀኑ በኋላ ወንድ ልጅ ታደሉ። ዊል ስቲል።
ተወልዶ ያደገው ቤልጂየም ውስጥ ቢሆንም ቀንደኛ የዌስትሃም ደጋፊ ነው።
ወደ እንግሊዙ ላንክሻዬር ከተማ መጥቶ በማየርስካፍ ኮሌጅ የእግር ኳስ አሠለጣጠን ተምሮ፤ በፈረንጆቹ 2014 በቤልጂየሙ ክለብ ሲን-ትሩደን የምስል ተንታኝ ሆኖ ተቀጠረ።
ከአንድ ዓመት በኋላ አሠልጣኝ ያኒክ ፌሬራን ተከትሎ የሊዬርስ አሠልጣኝ ቡድን አባል ሆኖ ገባ። ነገር ግን አሠልጣኙ እና የቡድኑ አባላት ሲባረሩ እሱ ምክትል ሆኖ ቆየ።
ቢሆንም ቡድኑ በገንዘብ እጦት ምክንያት ሲንገዳገድ ጊዜ ስቲል ይህን ሥራውን ለቆ ቢርሾት የተባለውን ክለብ ያሠለጥን ገባ።
ዊል ስቲል የዚህ ቡድን ምክትል አሠልጣኝ ሆኖ ለሁለት ዓመት ያህል ካገለገለ በኋላ በ2021 የዋና አሠልጣኝነቱን መንበር ተረከበ።
ምንም እንኳ ክለቡ ከታችኛው ሊግ አድጎ በአውሮፓ ሊግ ከመሳተፍ በአንድ ነጥብ ቢመለስም ዊል ስቲል በክለቡ ቦርድ አማካይነት ወደ ምክትልነት እንዲመለስ ተነገረው።
“ለተወሰነ ጊዜ ያህል ራሴን አግልዬ ዘና ማለትን መረጥኩ” ይላል ፈረንሳይኛ አቀላጥፎ የሚናገረው ስቲል።
“ከሁለት ሳምንት በኋላ ስመለስ አዲስ አሠልጣኝ ቀጥረው፤ ምክትል እንድሆን ነገሩኝ። እኔ ግን ያደረጉት ነገር ስለጎረበጠኝ ሥራውን መልቀቅ መረጥኩ።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሳምንት 1.2 ሚሊዮን ብር
የቀድሞው የማንቸስተር ሲቲ አምበል ቪንሴንት ኮምፓኒ የአንደርሌኽት አለቃ በነበረበት ወቅት ቀርቦት ከቀድሞው የዋትፈርድ አሠልጣኝ ጋርሺያ ጋር አብሮ እንዲሠራ መከረው።
ነገር ግን ስቲል የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ደረጃ ኤ የአሠልጣኝነት ፈቃድ ስለሌለው ሥራውን በጥቂት ወራት ጊዜ መልቀቅ ነበረበት።
“ፈቃዱን ለማገኘት ወደ ቤልጂየም በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እየተመላለስኩ መማር ነበረብኝ። ነገር ግን ከሥራው ጋር ተደራርቦ ከአቅም በላይ ሆነብኝ” ይላል።
“በጣም ከአቅሜ በላይ ሲሆንብኝ የምኖርበት አቅራቢያ ሥራ ማግኘት እንዳለብኝ ተሰማኝ።”
ይህ ማለት ወደ ቤልጂየም ተመልሶ እንደ አዲስ የሥልጠና ሥራ መጀመር አለበት ማለት ነው።
ስቲል ይህን ሁሉ አልፎ ወደ ራንስ ተመልሶ የጋርሺያ ምክትል ሆኖ ባለፈው ዓመት ሐምሌ በቋሚነት ሥራውን ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ወርሃ ጥቅምት ጋርሺያ ከአሠልጣኝነቱ ሲሰናበት ክለቡ ፊቱን ወደሱ አዞረ።
ነገር ግን እሱ የያዘው ለምክትልነት እንጂ ለዋና አሠልጣኝነት የሚሆን ፈቃድ አይደለም። የፈረንሳይ ሊግ 1 ሕግ ዋናው አሠልጣኝ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ከፍተኛውን ፈቃድ እንዲይዝ ያዛል።
ለዚህ ነው እሱ አሠልጣኝ ሆኖ ጨዋታ በሚያከናውንበት ወቅት ክለቡ 22 ሺህ ፓወንድ [አሁን ባለው የምንዛሪ ገበያ ከ1.4 ሚሊዮን ብር በላይ] ለመክፈል የሚገደደው።
በወር አንድ አሊያም ሁለት ጊዜ ወደ ቤልጂየም እየተመላለሰ ፈቃዱን ለማግኘት ትምህርት እየወሰደ ይገኛል።
የራንስ ቦርድ አባላት ጋርሺያን ሲያሰናብቱ ስቲልንም የማሰናበት ኃይል ቢኖረውም ወጣቱን አሠልጣኝ መሞከር ፈለጉ።
ክለቡ ለመጀመሪያ ጊዜ በስቲል እየተመራ ወደ ሜዳ የገባው ጋርሺያ በቤተሰብ ጉዳይ ወደ ስፔን በሄደበት ወቅት ነው።
ቀጣዩ የራንስ ጨዋታ ደግሞ ከፒኤስጂ ነው። ስቲል ቡድኑን እየመራ ወደ ሜዳ ገባ። ሊዮኔል ሜሲና የቡድን አጋሮቹ የራንስ ተከላካይ መስመር መስበር ተሳናቸው። ፒኤስጂ በያዝነው የውድድር ዓመት ጎል ያላስቆጠረበት ሦስተኛው ጨዋታ ነበር።
ከአርሰናል በውሰት የመጣው አጥቂው ፎላሪን ባሎጋን የሊግ 1 ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ነው። 15 ጎሎችን በማስቆጠር ከኪሊያን ምባፔና ቤን ዬዴር ቀጥሎ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
“በጣም ደስ የሚል ስብዕና ያለው ልጅ ነው። በጣም ገራሚ እግር ኳሰኛ ነው” ሲል ስቲል ስለወጣቱ አጥቂ ይናገራል።
የዊል ስቲል ቤተሰብ እግር ኳስ አሠልጣኝነት መክሊታቸው ይመስላል። ታላቅ ወንድሙም ኤድ የቤልጂየሙ ክለብ ዩፔን ዋና አሠልጣኝ ሲሆን፣ ታናሹ ደግሞ በምክትልነት ያገለግላል።
ምንም እንኳ አሁን ባለበት ደስተኛ ቢሆንም ወደፊት በፕሪሚዬር ሊግ ክለብ አሊያም በቻምፒዮንስ ሊግ መሳተፍ እንደሚሻ አይደብቅም።












