ምባፔ በክለቡ ታሪክ ከፍተኛው ጎል አስቆጣሪ ሆነ

ምባፔ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ኪሊያን ምባፔ 201ኛ ጎሉን ለፓሪስ ሴይን ዠርሜይን በማስቆጠር የክለቡ የምንግዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ክብረ ወሰንን ያዘ።

ምባፔ ከኖንት ጋር በነበረው ጨዋታ በኤዲሰን ካቫኒ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን ለመስበር እስከ 92ኛ ደቂቃ መጠበቅ ነበረበት።

ከጥቂት ወራት በፊት 24 ዓመት የደፈነው ፈረንሲያዊ ተጫዋች በዓለማችን ከሚገኙ ድንቅ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሆኗል።

ኪሊያን ምባፔ እአአ 2017 ከሞናኮ ፒኤስጂን ከተቀላቀለ በኋላ በ247 ጨዋታዎች ለክለቡ 201 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።

ምባፔ ገና በወጣትነት ዕድሜው በሁለት የዓለም ዋንጫ ፍጻሜዎች ላይ ተጫውቷል። በ2018 የዓለም ዋንጫ ክብርን ሲያገኝ፤ በኳታሩ 2022 ደግሞ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን የወርቅ ጫማ ወስዷል።

በ2021 የኔሽንስ ሊግ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ያነሳው ምባፔ፤ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ አርጀንቲና ላይ ሦስት ጎሎችን ማስቆጠሩ ይታወሳል።

እአአ 2017 ላይ ከሞናኮ ወደ ፒኤስጂ ከተዘዋወረ በኋላ ከክለቡ ጋር የሊግ 1 ዋንጫዎችን ከማንሳቱም በላይ ባለፉት 4 የውድድር ዘመን የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ጨርሷል።

ኪሊያን ምባፔ ፓሪስ ሴይንት ዠርሜይንን ከሞናኮ የተቀላቀለው በ180 ሚሊዮን ዩሮ ነበር። ይህም በዓለማችን ሁለተኛው ውድ የእግር ኳስ ተጫዋች ዝውውር ነው።

ከምባፔ በልጦ በአንደኛነት የተቀመጠውና ብቸኛው ዝውውር የብራዚላዊው አጥቂ ኔይማር ነው። ኔይማር ከባርሴሎና ወደ ፓሪስ ሴይንት ዠርሜይን የተዘዋወረው በ222 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን፣ ወቅቱም በአውሮፓውያኑ 2017 ነበር።

ምባፔ፤ በዚህ የውድድር ዘመን እስካሁን 30 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን 8 ኳሶችን ደግሞ ለጎል አመቻችቶ አቀብሏል።

ምባፔ ከኳስ ችሎታው በተጨማሪ አስደናቂ ፍጥነትን የተላበሰ ተጫዋች ነው። በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ፈረንሳይ ፖላንድን 3 ለ 1 ባሸነፈችበት ጨዋታ ምባፔ ያስመዘገበው ፍጥነት በሰዓት 35.3 ኪሎ ሜትር ነበር።

በሊጉም በሰዓት ከ36 ኪሎ ሜትር ፍጥነት በማስመዝገብ ፈጣኑ ተጫዋች እንደሆነም ተጠቅሷል።