ሙሴቬኒ ምዕራባውያን በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን መብት ዙሪያ ‘ጊዜ እያባከኑ ነው’ አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ምዕራባውያን አገራት የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችን መብቶች በአፍሪካ አገራት ላይ በኃይል ለመጫን እየጣሩ ነው ሲሉ ወቀሱ።
ሙሴቬኒ ይህን ያሉት አገራቸው የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን በተመለከተ አዲስ ሕግ እያረቀቀች ባለችበት ወቅት ነው።
የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ወንጀል በሆነባት ኡጋንዳ እየተረቀቀ ያለው ሕግ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ላይ የበለጠ ጠንካራ ቅጣት የሚጥል ነው።
ይሁን እንጂ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አዲሱን ረቂቅ የኡጋንዳ ሕግን እየተቹ ይገኛሉ።
ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ትናንት ሐሙስ መጋቢት 07/2015 ዓ.ም. በአገሪቱ ፓርላማ ቀርበው ንግግር ሲያደርጉ፣ የምዕራባውያን “እንግዳ የሆነ ባህል” ያሉትን የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት እንድንፈቅድ ማዕቀብ በመጣል ጫና ያሳድራሉ ብለዋል።
“ምዕራባውያን የራሳቸውን አሰራር በሌሎች ላይ ለመጫን የሚያባክኑትን ጊዜ ማቆም አለባቸው” ብለዋል።
አውሮፓውያኑ የአጎት እና የአክስት ልጅ ጋር ትዳር ይመሰርታሉ ያሉት ሙሴቬኒ፤ “እዚህ [ኡጋንዳ] የአንድ ጎሳ አባልን ማግባት ነውር ነው። እነሱ የቅርብ ዘመድ እንዳያገቡ ማዕቀብ እንጣል? ይህ የእኛ ሥራ አይደለም” ሲሉ ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ተናግረዋል።
ሙሴቬኒ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያንን አፈንጋጭ ብለው የገለጿቸው ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ብዙ ምክክር መደረግ አለበት ብለዋል።
ኡጋንዳ አሁን ላይ እያረቀቀች ባለችው ሕግ መሠረት በተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ውስጥ ያለ ወይም እራሱን የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት አፍቃሪ ብሎ የሚገልጽ ሰው እስከ 10 ዓመታት የእስር ጊዜን እንዲያሳልፍ ያዛል።
የኡጋንዳ መንግሥት በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የውጭ አገራት መንግሥታት ተቋማት እና ምዕራባውያን ኤጀንሲዎች የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን እያስተዋወቁ ነው በማለት ይከሳል።
ኡጋንዳ ምንም እንኳ ፀረ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ሕግ ቢኖራትም፣ በቅርብ ዓመታት በፍላጎት ላይ በተመሠረት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙት ምክንያት የተቀጣ ሰው የለም።












