ሊቢያ ውስጥ ጠፍቶ የነበረው 2500 ኪሎ የዩራኒየም ንጥረ ነገር መገኘቱ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, LNA
በምሥራቃዊ ሊቢያ የሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ ጠፋ ያለውን ከፍተኛ መጠን ያለው የዩራኒየም ንጥረ ነገርን ማግኘታቸውን አስታወቁ።
ሁለት ሺህ አምስት መቶ ኪሎ ግራም የሚመዝን ዩራኒየም የያዙት አስር በርሜሎች የተገኙት ሊቢያ ከቻድ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ መሆኑን የታጣቂዎቹ ኃይል የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊ አስታውቋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የአውቶሚክ ኃይል ተቆጣጣሪ ድርጅትም ንጥረ ነገሩ ስለመገኘቱ የወጣውን ሪፖርት “ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገ” መሆኑን አስታውቋል።
ተቆጣጣሪው ተቋም መርማሪዎች ስሙን ያልጠቀሱት ስፍራን ከጎበኙ በኋላ ንጥረ ነገሩ መጥፋቱን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነበር ያስታወቁት።
አካባቢው ከሊቢያ መንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሚገኝ ግዛት መሆኑም ተገልጿል።
ዩራኒየም ተፈጥሯዊ ማዕድን ሲሆን ከተጣራ ወይም ከዳበረ በኋላ ለኑክሌር መሳሪያ ግልጋሎት ሊውል ይችላል።
ጠፋ የተባለው የዩራኒየም ንጥረ ነገር ግን አሁን ባለበት ደረጃ ለኑክሌር ጦር መሳሪያ ግልጋሎት ሊውል ያመይችል ሲሆን፣ ነገር ግን ለመሳሪያው ምርት እንደ ጥሬ ዕቃ መጠቀም እንደሚቻል ባለሙያዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከ20 ዓመት በፊት በወቅቱ የሊቢያ መሪ የነበሩት ኮሎኔል ጋዳፊ አገራቸው የኑክሌር፣ ባዮሎጂካል እና የኬሚካል ጦር መሳሪያዎችን እንዲኖሯት ፍላጎት እንደሌላት ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።
ከአስር ዓመት በፊት የሊቢያው አምባገነን መሪ ኮሎኔል ሙአማር ጋዳፊ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ፣ አገሪቱ በተፎካካሪ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አንጃዎች መካከል ተከፋፍላለች።
በዚህም ዓለም አቀፍ ድጋፍ ያለው የሊቢያ ጊዜያዊ መንግሥት በዋና ከተማዋ ትሪፖሊ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ሌላኛው ኃይል ደግሞ ምሥራቃዊውን የአገሪቱን ክፍል ተቆጣጥሮ ይገኛል።
አሁን የጠፋው ዩራኒየም የተገኘበት ደቡባዊው የሊቢያ አካባቢ በሁለቱ ኃይሎች ቁጥጥር ስር አይደለም።
ምሥራቃዊውን የሊቢያ ኃይል የሚደግፈው እና እራሱን የሊቢያ ብሔራዊ ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ኃይል ነው 2.5 ቶን የሚመዝነውን ዩራኒየም ማግኘቱን የስታወቀው።
የተለያዩ አካባቢያዊ፣ የሃይማኖት እና የጎሳ ታጣቂዎች ጥምረት የሆነው ብሔራዊ ሠራዊቱት ከ50 ዓመት በፊት ኮሎኔል ሙአማር ጋዳፊን ወደ ሥልጣን ባመጣው መፈንቅለ መንግሥት ተሳታፊ በነበሩት ፊልድ ማርሻል ኻሊፋ ሃፍታር የሚመራ ነው።
የሊቢያ ብሔራዊ ሠራዊት እንዳስታወቀው ዩራኒየሙ የተገኘው ቀደም ሲል ተከማችተውበት ነበረው አምስት ኪሎ ሜትር ርቆ ከሚገኝ ስፍራ ተደብቆ ነው።
የዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኃይል ድርጅት ተቆጣጣሪዎች ቦታውን ባለፈው ዓመት ለመጎብኘት ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም፣ በተለያዩ የሊቢያ ሚሊሻዎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ ስለነበረ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ተደርጓል።
በኔቶ ኃይሎች ድጋፍ የአምባገነኑ ጋዳፊ መንግሥት መውደቁን ተከትሎ በነዳጅ ሃብት የበለጸገችው የሰሜን አፍሪካዋ ሊቢያ ሕግ አልባ እና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች የሚሸጡባት ስፍራ ሆናለች።
ከአስር ዓመት በፊት የመንግሥታቱ ድርጅት ያወጣው ሪፖርት ከሊቢያ በድብቅ የወጡ የጦር መሳሪያዎች በሌሎች የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ ግጭቶችን እያባባሱ ነው ብሎ ነበር።
አሁን የተገኘው ዩራኒየም ያልተጣራ ጥሬ ንጥረ ነገር ሲሆን “አሁን ባለበት ሁኔታ ምንም አይነት ጨረር አይኖረውም” ሲሉ በኑክሌር ጉዳዮች ላይ የሚሰራ ተቋም ባለሙያ የሆኑት ስኮት ሮይከር ለቢቢሲ ተናግረው “ለኑክሌር ጦር መሳሪያ ፕሮግራም ወይም ኑክሌር ኃይል ማመንጫነት ግብአት ሊሆን ይችላል” ብለዋል።
ንጥረ ነገሩን ለኃይል ማመንጫነት የሚጠቀሙ አገራት በይፋዊ ግብይት የሚገዙት መሆኑን ባለሙያው ተናግረው “ምናልባት ትርፍ ለማግኘት በአንድ ወገን ተሰርቆ ሊሆን ይችላል” እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች ይኖራሉ ብለዋል።
አስካሁን ንጥረ ነገሩ ከነበረበት ቦታ ለምን፣ መቼ እና በማን እንደተወሰደ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።












