በሊቢያ ለኑክሌር ግንባታ የሚውል የዩራኒየም ንጥረ ነገር መጥፋቱን ተመድ አስታወቀ

የኑክሌር ምልክት ያለባቸው በርሜሎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሊቢያ ውስጥ ከሚገኝ አንድ የማከማቻ ስፍራ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ኪሎ ግራም የሚመዝን የዩራኒየም ንጥረ ነገር መጥፋቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኑክሌር ተቆጣጣሪ አካል አስታወቀ።

ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ (አይኤኢኤ) ሊቢያ ውስጥ በሚገኝ እና ስፍራውን በይፋ ባልጠቀሰው ቦታ ላይ ተቆጣጣሪዎቹ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ባደረጉት ጉብኝት ነው የንጥረ ነገሩ መጥፋት የታወቀው።

ተቆጣጣሪዎቹ በማከማቻው ስፍራው ከዚህ ቀደም የነበሩ ከሁለት ቶን በላይ የሚሆኑ የዩራኒየም ንጥረ ነገር የያዙ 10 በርሜሎች የደረሱበት አለመታወቁን ገልጿል።

የዩራኒየም ንጥረ ነገር ክምችቱ በአግባቡ እና በሚታወቅ አካል ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ካልተያዘ የጨረር አደጋ እና የኑክሌር ጦር መሳሪያ ስጋት ያስከትላል ተብሏል።

የአውቶሚክ ኃይል ኤጀንሲው ባወጣው መግለጫ የጠፋው የዩራኒየም ንጥረ ነገር “እንዴት ከነበረበት ስፍራ ሊወጣ እንደቻለ እና አሁን ያለበትን ቦታ” በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ምርመራ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

ለኑክሌር ግንባታ የሚውለው እና 2.5 ቶን የሚመዝነው ዩራኒየም ከነበረበት ስፍራ መቼ እንደጠፋ የታወቀ ነገር የለም።

የዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኃይል ድርጅት ተቆጣጣሪዎች ቦታውን ባለፈው ዓመት ለመጎብኘት ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም፣ በተለያዩ የሊቢያ ሚሊሻዎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ ስለነበረ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ተደርጓል።

ተቆጣጣሪው አካል እንዳለው የዩራኒየም ንጥረ ነገሩ ተከማችቶ የነበረበት ቦታ የሊቢያ መንግሥት ኃይሎች ከሚቆጣጠሩት አካባቢ ውጪ ነው።

ከአስር ዓመት በፊት የሊቢያው አምባገነን መሪ ኮሎኔል ሙአማር ጋዳፊ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ፣ አገሪቱ በተፎካካሪ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አንጃዎች መካከል ተከፋፍለለች።

በዚህም የሊቢያ ጊዜያዊ መንግሥት በዋና ከተማዋ ትሪፖሊ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ሌላኛው ኃይል ደግሞ ምሥራቃዊውን የአገሪቱን ክፍል ተቆጣጥሮ ይገኛል።