የትግራይ ሠራዊት አዛዦች "መፈንቅለ መንግሥት አውጀዋል" ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ከሰሱ

 ጌታቸው ረዳ

የፎቶው ባለመብት, TPLF/FB

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በአዲስ እንዲዋቀር ወስነናል ያሉት የትግራይ ሠራዊት አዛዦች "መፈንቅለ መንግሥት አውጀዋል" ሲል የፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ጽህፈት ቤት ከሰሰ።

የሠራዊቱ አዛዦች ሐሙስ ጥር 15/2017 ዓ.ም. ያወጡትን መግለጫ ተከትሎ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በጉዳዩ ለመነጋገር አስቸኳይ የካቢኔ ስብሰባ ጠርተዋል።

"በሠራዊት አዛዦች ስም የወጣው መግለጫ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የማያውቀው እና በማንኛውም መንገድ ሕጋዊነት እና የሞራል ተቀባይነት የሌለው ያልተገባ ተግባር ነው" በማለት የጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱን እና ሁኔታውን በመገምገም ለሕዝቡ ዝርዝር ማብራሪያ እንደሚሰጥ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ጥር 15/ 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አትቷል።

የሠራዊት አዛዦቹ የሰጡት መግለጫ "የጦርነት አዋጅ እና ሥርዓት አልበኝነት" የሚያስከትል በመሆኑ የትግራይ የፀጥታ አባላት ሁኔታውን "ልብ ብለው በመገንዘብ አትኩሮት እንዲነፍጉት እና ከዚህ ውጪ የሚመጣው ማንኛው ዓይነት ትዕዛዝን ተግባራዊ እንዳያደርጉ እናሳስባለን" ሲል የጊዜያዊ አስተዳደሩ ተማጽኗል።

በኮሎኔል ገብሬ ገብረጻድቅ የተነበበው የሠራዊቱ አዛዦች መግለጫ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊነቱን በአግባቡ አልተወጣም በማለት የሌሎች መጠቀሚያ ሆኗል የሚል ክስ አቅርቧል።

በመግለጫው በጊዜያዊ አስተዳደሩ "ቁልፍ ሥልጣን የነበራቸው አመራር እና አባላት ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውጪ የሕዝብን ጥቅም ወደ ጎን በመተው ክህደት በመፈጸም የውጭ ኃይል መሣሪያ ሆነዋል" ብሏል።

ነገር ግን መግለጫው በሕዝብ ጥቅም ላይ ስለደረሰው ጉዳትም ሆነ "የውጭ ኃይል" የተባለው አካልን ማንነት በተመለከተ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር የለም።

ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ፓርቲው በሊቀመንበሩ እና በምክትል ሊቀመንበሩ በሚመራ ቡድኖች ተከፍሎ ሲካሰስ መቆየቱ ይታወሳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን በዶ/ር ደብረጽዮን በሚመራው ሌላኛው ቡድን ምክንያት ሥራውን በአግባቡ ለማከናወን እንቅፋት እንደገጠመው በመግለጽ ክስ ሲሰነዝር ቆይቷል።

በድርጅቱ ሊቀመንበር የሚመራው የህወሓት ቡድን ከዚህ ቀደም ያሳለፈውን ውሳኔ እንደሚደግፍ የገለጸው የወታደራዊ አመራሮቹ መግለጫ፣ ድጋፉን ለዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን መስጠቱን በተዘዋዋሪ አመልክቷል።

በንባብ የቀረበው መግለጫ በአመዛኙ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር "ድክመቶች" ላይ የሚያተኩር እና አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም እየሞከረ ነው በማለት ወቅሷል።

በዚህም ምክንያት "የተዳከመ" እና "ተልዕኮውን የዘነጋ" ያለውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማጠናከር አመራሮቹ ተነስተው በሌሎች መተካት እንዳለባቸው አሳስቧል።

በዚህም መሠረት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ለተካሄደውን የህወሓት 14ኛ ጉባኤ እውቅና በመስጠት በጉባኤው ውሳኔ መሠረት የጊዜያዊ አስተዳደር የአመራሮች ለውጥ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

አወዛጋቢ የነበረው የህወሓት 14ኛ ጉባኤ በምርጫ ቦርድ እና ጥቂት በማይባሉ የድርጅቱ አመራሮች ዕውቅና ያልተሰጠው ሲሆን በአመራሮች እና በአባላት መካከልም ለተፈጠረ መከፋፈል ምክንያት ሆኗል።

በርካታ አመራሮች እና አባላት እራሳቸውን ባገለሉበት የህወሓት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር እና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ከ17 በላይ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከጉባኤው ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል።

የሠራዊቱ አመራር አባላት መግለጫ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በትግራይ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ በአካባቢያዊ እና በአውራጃዊነት መከፈሉን በመጥቀስ፣ በወሳኝ የአመራር ውድቀት ምክንያት "የሕዝቡ ጥቅም ተዘንግቶ ወደ መጠቃቃት አምርቷል" ብሏል።

ከጊዜያዊ አስተዳደሩ በተጨማሪ በትግራይ ክልል ያሉ የመገናኛ ብዙኃንን የወቀሰው መግለጫ ሚዲያዎች የግለሰብ ፖለቲከኞችን ግላዊ ፍላጎት ማሳኪያ እና "የውጭ ኃይሎች መሳሪያ" ሆነዋል በማለት በስም ያልጠቀሳቸውን ሚዲያዎች ከሷል።

በስብሰባቸው ላይ ተመሳሳይ አቋም ያስተጋቡት ወታደራዊ አመራሮቹ "ህወሓት የትግራይን ጊዜያዊ አስተዳደር ለማሻሻል ያሳለፈው ውሳኔ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን" ድጋፋቸውን መግለጻቸውን አሳቋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሠራዊቱን ወክለው በጊዜያዊ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት የሆኑትን ግለሰቦች በመገምገም "እምነት የሚጣልባቸው ያልሆኑትን" በሌሎች እንዲተኩ መወሰናቸውንም ገልጿል።

እንዲሁም ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሠራዊቱ ላይ የሚካሄደውን የስም ማጥፋት ዘመቻን መከላከል ባለመቻሉ "በክህደት" ወንጅለውታል።

አቶ ጌታቸው እና ዶ/ር ደብረጽዮን የሚመሩት የህወሓት ቡድኖች ግንኙነት ሻክሮ በባለፉት ወራት ከፍተኛ መፈራቀቅ የተከሰተ ሲሆን የደብረጽዮን ቡድን ጊዜያዊ አስተዳደሩ በድጋሚ እንዲዋቀር በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያርብ ነበር።

ሁለቱ ወገኖች ባለፈው ኅዳር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ባደረጉት ውይይት ይኸው ጥያቄ ተነስቶ፣ በክልሉ ምርጫ ተካሂዶ መደበኛ አስተዳደር እስኪቋቋም ድረስ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሥራ ላይ እንደሚቆይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መገለጹ ይታወሳል።