ዝነኛው የሬስሊንግ ኮከብ ሃልክ ሆጋን በ71 ዓመቱ ህይወቱ አለፈ

ሃልክ ሆጋን መድረክ ላይ ልብሱን እየቀደደ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከዝነኛ የአሜሪካ ሬስሊንግ (ነጻ ፍልሚያ) ኮከቦች አንዱ የሆነው ሃልክ ሆጋን ትናንት ሐሙስ በ71 ዓመቱ በፍሎሪዳ በሚገኘው ቤቱ ህይወቱ አለፈ።

በመዝገብ ስሙ ቴሪ ጂን ቦሌያ የተባለው ኮከብ፤ በወርቃማ ፀጉሩ እና ጎልቶ በሚታየው ሪዙ ይበልጥ ይታወቃል።

እ.አ.አ በ1977 የፕሮፌሽናል ሬስሊንግ ሙያውን የጀመረው ሆጋን፤ ወደ ዝና ማማ ላይ የወጣው ከዚህ ቀደም ወርልድ ሬስሊንግ ፌዴሬሽን( WWF) ተብሎ ይጠራ ለነበረው እና በአሁኑ ሰዓት ወርልድ ሬስሊንግ ኢንተርቴይመንት (WWE) ተብሎ ለሚታወቀው ኩባንያ በ1983 ከፈረመ በኋላ ነበር።

ሬስሊንግ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ መሆን በጀመረባቸው ዓመታት ከነበሩ ታዋቂ ገጸ ባህሪያት አንዱ ሃልክ ሆጋን ነበር።

ከሬስሊንግ ታዋቂነቱ በኋላ ከ2005 እስከ 2007 በቪኤች 1 ላይ ይተላለፍ በነበረው 'ሆጋን ኖውስ ቤስት' የተባለ ዝግጅትም (reality show) ታዋቂነትን አትርፏል።

የሆጋን ማናጀር ክሪስ ቮሎ፤ የሬስሊንግ ኮከቡ በፍሎሪዳ ክሊርዋተር በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ውስጥ በቤተሰቦቹ ተከብቦ ህይወቱ ያለፈው በልብ ድካም ምክንያት ነበር።

ሆጋን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀንደኛ ደጋፊ ነበር።

ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማህበራዊ ሚዲያ ድረ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት "በዛሬው ዕለት አንድ ታላቅ ወዳጄን አጣሁ" ብለዋል።

"ሃልክ ሆጋን ከጅምሩ አንስቶ የአሜሪካ ዳግም ታላቅ ትሆናለች ደጋፊ (MAGA) ነበር፤ ጠንካራ፣ አይበገሬ፣ ብልህ፣ ግን ትልቅ ልብ ያለው ሰው ነበር። በሪፐብሊካን ብሔራዊ ኮንቬንሽን ላይ ያደረገው ንዝረት የሚፈጥር ንግግር ከሳምንቱ ድምቀቶች አንዱ ነበር" በማለት ጽፈዋል።

የደብሊው ደብሊው ኢ ኮከቡ በግንቦት ወር የአንገት ቀዶ ጥገና እና በሰኔ ወር ደግሞ የልብ ቀዶ ጥገና አድርጎ ነበር። ቤተሰቡ ኢንስታግራም ላይ ባወጡት ልጥፍ "ጀግና አጥተናል" ብለዋል።

"ከአራት አስርት ዓመታት በላይ በሕይወታቸው ላይ ተጽዕኖ ያሳደረባቸው እና በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አድናቂዎች ላይ ትቶት የሄደው አስደናቂ ትዝታ ሁላችንንም ያጽናናናል" ሲሉ ጽፈዋል።

 ሃልክ ሆጋን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፖሊስ መኮንንኖች ሐሙስ ጠዋት ለደረሳቸው የአደጋ ጥሪ ምላሽ በመስጠት በቦታው ሲገኙ ሆጋን ከባድ የህክምና ችግር እያጋጠመው እንደነበር ተገልጿል።

ጥሪው ከደረሰ ከአንድ ሰዓት ገደማ በኋላ ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን ህይወቱ ያለፈው እዚያው ነው። ፖሊስ፤ አሟሟቱን በተመለተ ምንም ዓይነት አጠራጣሪ ሁኔታ እንደሌለ የገለጸ ሲሆን ቢሆንም ግን ምርመራ ይደረጋል ተብሏል።

የሬስሊንግ ኩባንያው ደብሊው ደብሊው ኢ ባወጣው መግለጫ፤ በሃልክ ሆጋን ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል።

"በፖፕ ባህል ውስጥ እጅግ ታዋቂ ከሆኑት ሰዎች አንዱ የሆነው ሆጋን፤ በ1980 ዎቹ ደብሊው ደብሊው ኢ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ ረድቷል" ብሏል።

የሆጋን ከህይወት በላይ ግዙፍ ስብዕና እና ተሰጥኦው ፕሮፌሽናል ሬስሊንግ ይበልጥ ለህዝብ ተደራሽ እንዲሆን ረድቷል።

ስድስት ጊዜ የደብሊው ደብሊው ኢ ሻምፒዮን የነበረ ሲሆን የኩባንያው ታዋቂ ዝግጅት በሆነው 'ሬስልማኒያ' ላይም ለስምንት ጊዜ ያህል የዝግጅቱ ዋና ድምቀት ነበር።

በ1953 በአሜሪካ ጆርጂያ ግዛት የተወለደው ሆጋን በፕሮፌሽናል ሬስሊንግ ታሪክ እጅግ ታዋቂ ከሆኑት ግለሰቦች አንዱ ነበር። "ሃልክ" የሚለው ቅጽል ስሙ ከታዋቂ የኮሚክ መጽሐፍ ገጸ ባህሪ የተወሰደ ነው።