የኢትዮጵያ ወታደራዊ ማዕረጎች ቅደም ተከተል ምን ይመስላል? ማዕረጎቹ እንዴት ይሰጣሉ?

የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወታደራዊ ትርዒት ሲያቀርቡ

የፎቶው ባለመብት, PMO/FB

የምስሉ መግለጫ, የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወታደራዊ ትርዒት ሲያቀርቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ ቅዳሜ መስከረም 10/2018 ዓ.ም ለ66 የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት መኮንኖች ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረግ እንዲሰጥ አድርገዋል።

በዚህም ለአራት ሌ/ጄነራሎች የሙሉ ጄነራልነት ማዕረግ የተሰጣቸው ሲሆን፣ እነዙም ሌ/ጄነራል አለምሸት ደግፌ፣ ሌ/ጄነራል ደስታ አብቼ፣ ሌ/ጄነራል ይመር መኮንን እና ሌ/ጄነራል ድሪባ መኮንን ናቸው።

በተጨማሪም ሁለት መኮንኖች ከሜ/ጄነራልነት ወደ ሌ/ጄነራልነት ሲያደጉ፣ 17 መኮንኖች ደግሞ ከብ/ጄነራልነት ወደ ሜ/ጄነራልነት አድገዋል። 43 መኮንኖች ደገሞ ከኮሎኔል ወደ ብ/ጄነራልነት ከፍ ብለዋል።

ለመሆኑ በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ከታችኛው የተራ ወታደርነት አንስቶ አስከ ከፍተኛው ወታደራዊ መኮንንነት ደረጃ የሚሰጠው ማዕረግ ቅደም ተከተል እና የሚሰጥበት ሂደት ምን ይመስላል?

አንድ ወታደር የመጀመሪያ ምልምል ሆኖ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ሲቀላቀል "መሠረታዊ ወታደር" የሚል መጠሪያ ይኖረዋል።

ይህ መጠሪያ ከሌላው የማኅበረሰብ ክፍል የሚለየው ሲሆን፣ ወታደር ከሚለው የአጠቃላይ የሠራዊቱ አባላት የወል መጠሪያ ጋር የተዛመደ ነው።

አንድ መሠረታዊ ወታደር ቢያንስ ለሦስት ዓመት ካገለገለ በኋላ ለቀጣይ ማዕረግ ብቁ ነው ተብሎ ከታጨ ወደ ምክትል አስር አለቃ ማዕረግ ያድጋል።

በመሠረታዊ ወታደርነት የአገልግሎት ዘመኑ የጦር መሳሪያ መተኮስ፣ የተሰጠውን ግዳጅ መወጣት ኃላፊነት ብቻ የተጣለበት አንድ ወታደር ወደ ምክትል አስር አለቃነት ሲያድግ ግን ሌሎችንም የመምራት የማስተባበር ኃላፊነት ስለሚኖር ተጨማሪ ሥልጠናዎች ይሰጡታል።

ከዚህ ሥልጠና በኋላ የጓድ መሪ ወይንም የምክትል ጓድ መሪ የሚል ኃላፊነት ይደረብለታል።

አንድ ምክትል አስር አለቃ የሆነ ወታደር ሁለት ዓመት ካገለገለ በኋላ ክፍት የመሾሚያ ቦታዎች በሚባለው የሚኒስቴሩ አሠራር መሠረት ከበርካታ አቻ ማዕረግ ካላቸው የሠራዊቱ አባላት ጋር ተወዳድሮ ወደ አስር አለቃነት ያድጋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለአባላቱ ማዕረግ የሚጠቀምባቸው ምልክቶች ዓለም አቀፍ ሲሆኑ፣ በምክትል አስር አለቃነት በትከሻቸው ላይ የሚቀመጠው የቪ (V) ምልክት አንድ ብቻ ሲሆን፣ የሙሉ አስር አለቃ ደግሞ ሁለት የቪ ምልክት ይሆናል።

ከአስር አለቃ በኋላ የሚያገኘው የማዕረግ ዕድገት ሃምሳ አለቃነት ነው።

አንድ የሠራዊቱ አባል የሃምሳ አለቃ ማዕረግ ከደረሰ በኋላ ባለው አቅም ወደ መኮንንነት ወይንም መጋቢ የሃምሳ አለቃ በሚል ከፍተኛ የበታች ሹም ውስጥ ይካተታል።

የመኮንንነት ኃላፊነቶች ውጊያን የማቀድ፣ ሃብት የማደራጀት እንዲሁም የመምራት ኃላፊነቶች አሉበት።

መጋቢ የሃምሳ አለቃ በሚል በከፍተኛ የበታች ሹም ውስጥ በቴክኒክ ዕውቀት በቢሮዎች ውስጥ የሚሠሩ የሠራዊቱን አባላት ይመለከታል።

እነዚህ አባላቱ በተለያዩ የቴክኒክ ሥራዎች ውስጥ እና በሕክምናው ዘርፍ ውስጥም የሚሠሩ ይሆናሉ።

በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ የሃምሳ አለቃ ማዕረግ ላይ የደረሱ ወታደሮች በሚሰጣቸው የአቅም መመዘኛ ፈተና በየትኛው ዘርፍ ቢሰማሩ ሠራዊቱን የበለጠ ያገለግላሉ የሚለው ይለይበታል።

ከዚህ የአቅም ምዘና በኋላ በመስክ ላይ በሚሰጥ ፈተና ችሎታቸው ተፈትሾ ወደ መጋቢ ሃምሳ አለቃ እና ወደ ምክትል መቶ አለቃ ማዕረግ ይሸጋገራሉ።

የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወታደራዊ ትርዒት ሲያቀርቡ

የፎቶው ባለመብት, Office of the PM

የምስሉ መግለጫ, የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወታደራዊ ትርዒት ሲያቀርቡ

ባለ ሌላ ማዕረግ እና የመኮንን ማዕረግ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተቋሙ የማዕረግ ደረጃዎች የመጀመሪያው ክፍል ባለ ሌላ ማዕረግ፣ ሁለተኛው ክፍል መስመራዊ መኮንን፣ የሻለቃ ማዕረግ ሲያገኝ ደግሞ ከፍተኛ መኮንን በመባል ተለይተዋል።

ከዚህ በኋላ ያሉት ደግሞ ከፍተኛ መኮንን፣ ጄነራል መኮንን፣ ከፍተኛ ጄነራል መኮንን በሚል የተከፋፈሉ ናቸው።

ከጄነራል መኮንኖች በላይ ያለው ማዕረግ ማርሻል ሲሆን ይህም ባለ አምስት ኮከብ ነው።

በተቋሙ ውስጥ ከመጋቢ ሃምሳ አለቃ እስከ ሻለቃ ባሻ ድረስ ያሉት ማዕረጎች የባለ ሌላ ማዕረግ (ባማ) በመባል ይጠራሉ።

በመጋቢ ሃምሳ አለቃ ማዕረግ ላይ የሚታዩት ሦስት ቪዎች ላይ ተጨማሪ አንድ ኮከብ የሚቀመጥ ሲሆን፣ ሦስት ዓመት ካገለገለ በኋላ ወደ ሻምበል ባሻ ይሸጋገራል።

ከዚያም ወደ ሻለቃ መጋቢ ባሻ፣ ሻለቃ ባሻ፣ ጁኒየር ዋራንት ኦፊሰር፣ ሲኒየር ዋራንት ኦፊሰር እያለ ያድጋል።

አንድ ሲኒየር ዋራንት ኦፊሰር ላይ የደረሰ የመከላከያ ሠራዊት አባል ከኮሎኔል ማዕረግ ካለው አባል ጋር ተመጣጣኝ ሥልጣን ይኖረዋል።

ኮሎኔል አጠቃላይ የመምራት ዕውቀት ይዞ ሲያድግ ሲኒየር ዋራንት ኦፊሰር ደግሞ አጠቃላይ የቴክኒክ ዕውቀትን ይዞ ያድጋል።

እነዚህ ወታደሮች በአንድ የተለየ ጉዳይ ላይ ጠለቅ ያለ ዕውቀት ስላላቸው የጄነራል ማዕረግ ያላቸውን ከፍተኛ መኮንኖች የማማከር ሚና ይኖራቸዋል።

መጋቢ ሃምሳ አለቃ ለመሆን በተመረጡ ሙያዎች ውስጥ መሠልጠን ሲጠይቅ የምክትል መቶ አለቃ ስልጠና ደግሞ እንደ አጠቃላይ አመራር ሊሆን የሚያስችለውን ሥልጠና ያገኛል።

አንድ የሠራዊቱ አባል የመጋቢ ሃምሳ አለቃ ማዕረግን ካገኘ በኋላ በምንም ዓይነት መንገድ ወደ መኮንንነት መሄድ አይችልም።

በመጋቢ ሃምሳ አለቃነት ቀጥሎ ዋራንት ኦፊሰርነት ደረጃ ላይ ሲደርስ ጡረታ የሚወጣ ይሆናል።

መኮንን ከሆነ በኋላ ግን አቅም እና ችሎታው እስካለው ድረስ ባለ አራት ኮከብ ደረጃ ጄነራልነት ድረስ ማደግ ይችላል።

በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ የአየር ኃይል ማዕረጎች የሚለዩት እስከ መስመራዊ መኮንን ድረስ ያሉት ብቻ ናቸው።

ይህ ባለ ልዩ ማዕረግ በሚባለው መዋቅር ውስጥ ያሉት የማዕረግ ሥያሜዎች በአየር ኃይል ውስጥ ሲሆን፣ ምክትል አስር አለቃ የሚለው በጁኒየር ኤር ክራፍት ማን፣ ከዚያ በኋላም ሲኒየር ኤርክራፍት ማን፣ ሊድ ኤር ክራፍት ማን እየተባሉ ይለያሉ።

የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወታደራዊ ትርዒት ሲያቀርቡ

የፎቶው ባለመብት, Office of the PM

የምስሉ መግለጫ, የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወታደራዊ ትርዒት ሲያቀርቡ

ከምክትል መቶ አለቃ እስከ ባለ አምስት ኮከብ ጄነራል

በኢትዮጵያ እውቅና ያለው ከፍተኛው ወታደራዊ ማዕረግ ባለ አምስት ኮከብ ጄነራል ሲሆን እርሱም ማርሻል ነው።

የምክትል መቶ አለቃ ማዕረግ በሠራዊቱ ውስጥ እያገለገሉ የነበሩ ወይንም ደግሞ ከማኅበረሰቡ ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ እና ፈቃደኛ የሆኑ ዜጎች ተመልምለው የዕጩ መኮንነት ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ የሚሰጥ ነው።

የሠራዊቱ አባላትም በምክትል አስር አለቃ ወይንም በአስር አለቃ ማዕረግ ላይ እያሉ የተለያዩ ትምህርቶችን የተማሩ እና የተመረቁ ከሆነ ተወዳድረው የዕጩ መኮንንነትን ኮርስ በመውሰድ የምክትል መቶ አለቃ ማዕረግን ሊያገኙ ይችላሉ።

በምክትል መቶ አለቃነት ሁለት ዓመት ያገለገለ የሠራዊቱ አባል ወደ መቶ አለቃነት ያድጋል።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ክፍት የመሾሚያ ቦታዎች፣ የወታደሩ ብቃት እና አፈጻጸም ዕድገቱን ለማግኘት የሚያስችሉ ናቸው።

የመቶ አለቃ ማዕረግ ያገኘ አንድ የሠራዊቱ አባል እንዲሁ ያሉት የኃላፊነት ዓይነቶች ለውጥ ይኖረዋል።

ይህ መስመራዊ መኮንን ውስጥ የገባ የመከላከያ አባል መኮንን ተብሎ ይጠራል። መስመራዊ መኮንን ምክትል መቶ አለቃ፣ መቶ አለቃ እና ሻምበል ናቸው።

ሁለተኛው የመኮንንነት ደረጃ ከፍተኛ መኮንን ሲሆን፣ ይህም ሻለቃ፣ ሌተናል ኮሎኔል እና ኮሎኔል ናቸው።

ሦስተኛው የመኮንንነት ደረጃ ጄነራል መኮንን የሚባለው ሲሆን፣ ከዚያ በላይ ያሉትን የብርጋዴር፣ የሜጀር፣ የሌፍተናንት እና የጄነራል ማዕረጎችን ያካተቱ ናቸው።

አንድ የምክትል መቶ አለቃ የነበረ ግለሰብ ከሁለት ዓመት አገልግሎት በኋላ ወደ መስመራዊ መኮንንነት ገብቶ የሙሉ መቶ አለቃ ማዕረግ (ሁለት ኮከብ) ያገኛል።

ከዚህ በኋላ የግድ አራት ዓመት ማገልገል ያለበት ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ወደ ሻምበል (ሦስት ኮከብ) ያድጋል።

ከዚህ ጊዜ ውጪ ደግሞ በልዩ ሁኔታ የሚሰጡ የማዕረግ ዕድገቶችም ይኖራሉ።

ይህ ግን በጣም ውሱን ሲሆን፣ አንድ ወታደር የተሰጠውን ተልዕኮ እየተወጣ እያለ ከሌላው በተለየ ሁኔታ ጀብድ ሲሠራ በልዩ ሁኔታ የቆይታ ጊዜው ሳይጠበቅ የማዕረግ ዕድገት ያገኛል።

በቆይታው ወቅት የሥነ ምግባር ግድፈት ያለበት ሠራዊትም ባለበት ይቆያል።

በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ የመጨረሻው ማዕረግ ባለ አራት ኮከብ ጄኔራል ነው።

ይህ ባለ አራት ኮከብ የጄነራልነት ማዕረግ በፖለቲካዊ ውሳኔ መንግሥት አስፈላጊ ነው ብሎ ባመነ ጊዜ እንደ መኮንኖቹ ብቃት እና ችሎታ በተለያዩ ጊዜያት ይሰጣል።

ከምክትል መቶ አለቃ ማዕረግ በኋላ ግን ሁሉም ማዕረጎች በአየር ኃይል ውስጥ በተመሳሳይነት ይቀጥላሉ።

አንድ ግለሰብ ከምክትል መቶ አለቃነት ተነስቶ ጄነራል ማዕረግ ለመድረስ ቢያንስ 30 ዓመት ሊፈጅበት ይችላል።

ከጄነራል መኮንኖች በላይ ያለው ማዕረግ የማርሻል ማዕረግ ሲሆን ይህም ባለ አምስት ኮከብ ነው።