ጠ/ሚ ዐቢይ 4 ሙሉ ጄነራሎችን ጨምሮ ለ66 መኮንኖች ከፍተኛ ማዕረግ እንዲሰጥ አደረጉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዐብይ አሕመድ ያቀረቧቸው ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች በፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የተለያዩ ከፍተኛ የማዕረግ ዕድገት ተሰጣቸው።
ቅዳሜ መስከረም 10/2018 ዓ.ም. ወታደራዊ ሹመት ያገኙ ስድሳ ስድስት ከፍተኛ የወታደራዊ መኮንኖች ሲሆኑ፣ አራቱ የሙሉ ጄነራልነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ከፍተኛው የሙሉ ጄነራልነት ወታደራዊ ማዕረግ የተሰጠው የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም አማካሪ ለሆኑት ሌ/ጄነራል አለምሸት ደግፌ፣ የመከላከያ ምህንድስና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌ/ጄነራል ደስታ አብቼ፣ የመከላከያ ትምህርት እና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌ/ጄነራል ይመር መኮንን እና የመከላከያ ኢንስፔክተር ኃላፊ ሌ/ጄነራል ድሪባ መኮንን ናቸው።
በተጨማሪም ሁለት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ከሜ/ጄነራልነት ወደ ሌ/ጄነራልነት ዕድገት ሲያገኙ፣ 17 ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ደግሞ ከብ/ጄነራልነት ወደ ሜ/ጄነራልነት አድገዋል። በርካታ ቁጥር ያላቸው 43 ወታደራዊ መኮንኖችም ከኮሎኔል ወደ ብ/ጄነራልነት ከፍ ብለዋል።
ይህ በርካታ ቁጥር ያላቸው መኮንኖች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ታጭተው በፕሬዝዳንቱ ለከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች የተሰጠው ኢትዮጵያ በተለይ ባለፈው ዓመት ወታደራዊ አቅሟን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ማከናወኗን በተከታታይ ይፋ ካደረገች በኋላ ነው።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በርካታ የጦር ኃይሏ አባላት የሚሆኑ ወታደሮችን በተከታታይ አሠልጥና ማስመረቋ በተለያዩ ጊዜያት ተዘግቧል።
በተጨማሪም የአየር፣ የምድር እና የባሕር ኃይሏን የሚያጠናክሩ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በራሷ እየሠራች መሆኗ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መገለጹ ይታወሳል።
በተጨማሪም ለአስርታት የባሕር በር እና የባሕር በር አልባ ሆና የቆየችው ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የባሕር ኃይሏን ዳግም መሥርታ ስታጠናክር ቆይታለች። ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይም የባሕር ኃይሉ ዋና ማዘዣ አዲስ አበባ ውስጥ ተገንብቶ ተመርቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ አሁኑ ከሰጡት በተጨማሪ ሁለት ጊዜ ለከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች የማዕረግ ሹመት እንዲሰጥ አድርገዋል።
በጥር 2012 በአጠቃላይ ለ65 ጄነራል መኮንኖች የማዕረግ ሹመቱ የተሰጠ ሲሆን፣ ከመካከላቸው ስድስቱ የሌ/ጄነራል፣ 19 ሜ/ጄነራል እና 40 ደግሞ የብ/ጄነራልነት ማዕረግ ተሰጥቷቸው ነበር።
እንዲሁም ከአራት ዓመታት በፊት በታኅሣሥ 2014 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የፊልድ ማርሻልነት ማዕረግን ጨምሮ ለአንድ መቶ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ማዕረግ ተሰጥቷል።
በዚህም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የሆኑት ጄነራል ብርሃኑ ጁላ የፊልድ ማርሻልነት ማዕረግ ሲሰጣቸው፣ በተጨማሪም ለአራት ጄነራሎች፣ ለ14 ሌ/ጄነራሎች፣ ለ24 ሜ/ጄነራሎች እና ለ58 ብ/ጄነራሎች የማዕረግ ዕድገቱ ተሰጥቷቸው እንደነበር ይታወሳል።















