ግማሹ የጋዛ የውሃ ጣቢያ መጎዳቱን አሊያም መውደሙን የቢቢሲ ሳተላይት መረጃ አረጋገጠ

እስራኤል በሐማስ ላይ ወታደራዊ እርምጃ ከጀመረች ወዲህ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጋዛ የውሃ እና የንፅህና መጠበቂያ ተቋማት ተጎድተዋል ወይም ወድመዋል ሲል የቢቢሲ የሳተላይት መረጃ አረጋግጧል።
በዋና ዋና የውሃ ማከማቻዎች ላይ የደረሰው ጉዳትም ጥገናውን በእጅጉ አስተጓጉሏል።
የንፁህ ውሃ እጦት እና ያልተጣራ የፍሳሽ ቆሻሻ በጤና ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀናቸውን የእርዳታ ድርጅቶች እየገለጹ ነው።
ሃማስ የሲቪል መሰረተ ልማቶችን ለሽብር ተግባር እየተጠቀመ ነው ሲል የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ለቢቢሲ ገልጿል።
ወሳኝ መሠረተ ልማቶቹ ለወታደራዊ ጥቅም እስካልዋሉ ድረስ በጦርነት ህግ የመጠበቅ ግዴታ እስራኤል እያለባት ጥፋቱ መድረሱን የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የንፁህ ውሃ ውስን በሆነባት በግዛቲቱ የመጠጥ ውሃ በአብዛኛው የሚቀርበው ከጉድጓዶች እና ጨዋማ ውሃን በማጣራት ነው።
መስከረም 26 ሐማስ ጥቃት ካደረሰ በኋላ እስራኤል በጋዛ የአጸፋ ምላሽ መስጠት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከውሃ መሠረተ ልማቶች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተጎድተዋል ወይም ወድመዋል ሲል የቢቢሲ ምርመራ ያሳያል።
በተጨማሪም ከስድስቱ የፍሳሽ ውሃ ማጣሪያዎች አራቱ ተጎድተዋል ወይም ወድመዋል። ሁለቱ ደግሞ በነዳጅ እጥረት ወይም በሌላ አቅርቦት ምክንያት ተዘግተዋል ሲል አንድ የእርዳታ ድርጅት ገልጿል።
ይህ የታወቀው በጋዛ ማዘጋጃ ቤት የውሃ አገልግሎት ከተሰጡ ከ600 በላይ የውሃ እና ፍሳሽ ማጣሪያ ቦታዎች ምርመራ በኋላ ነው።
በአንድ የሳተላይት ምስል በደቡባዊ ጋዛ በሚገኘው ዃን ዩኒስ ሁለት የተበላሹ ትላልቅ የውሃ ማጠራቀሚያዎች ይታያሉ።
“የውሃ እና የንፅህና መጠበቂያ ተቋማት መውደም በህዝቡ ላይ አስከፊ የጤና መዘዝ አስከትሏል” ሲሉ የሜዲሲን ሳን ፍሮንትየር ዩኬ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ናታሊ ሮበርትስ ተናግረዋል።
"የተቅማጥ በሽታዎች መጠን በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል" ብላለች።
በጣም ከባድ በሆኑ ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ በሽታ ህጻናትን እና አቅመ ደካማዎችን ሊገድል ይችላል።
በተበከለ ውሃ ውስጥ የሚገኘው እና በተለይ ለነፍሰ ጡር እናቶች አደገኛ የሆነው የሄፐታይተስ ኤ መጠንም ከፍተኛ መሆኑን የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ገልጿል።
"ይህ ሰዎችን እየገደለ ነው" ብላለች ዶ/ር ሮበርትስ።
በርካታ ጋዛውያን በተሰደዱባት ራፋህ የበሽታ መጨመር አለ ያለችው ዶ/ር ሮበርትስ፤ የኮሌራ ስጋትም ተፈጥሯል ብላለች።
ሐማስ መስከረም 26 እስራኤልን ካጠቃ በኋላ በጋዛ ያሉ ሕንፃዎች ላይ ሰፊ ውድመት ደርሷል
እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሆነ ወደ 69 ሺህ የሚጠጉ ቤቶች ሲወድሙ 290 ሺህ ደግሞ ተጎድተዋል ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የእርዳታ ሠራተኞች እንዳሉት ከሆነ ቤቶች የውሃ የማግኘት ዕድላቸው አነስተኛ ነው።
የቢቢሲ የሳተላይት ትንተና
ይህንን ትንታኔ ለማከናወን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ከሂዩማን ራይትስ ዎች ባለሙያዎች የተሻለውን አካሄድ በተመለከተ ቢቢሲ ምክር ጠይቋል።
ከዚያም በቦታው ያለው ግንባታ ወደ ፍርስራሽ ከተቀየረ፣ በከፊል ከወደቀ ወይም ሌላ የጉዳት ምልክቶች ካሳየ ተቋሙ እንደፈረሰ ወይም እንደተበላሸ ቢቢሲ ይቆጥረዋል።
ቢቢሲ ቬሪፋይ "የወደሙ" እና "የተበላሹ" መሠረተ ልማቶችን አልለየም። የእያንዳንዱ ተቋም ትክክለኛ ዝርዝር መረጃ ሳይታወቅ በከፊል ተጎድቷል ወይም ሙሉ በሙሉ ወድሟል ማለት አይቻልም።
አብዛኛዎቹ የውኃ ጉድጓዶች መቆጣጠሪያ ክፍል እና የኤሌክትሪክ የውሃ መሳብያ ይይዛል።
እነዚህን አነስተኛ ጣብያዎች የማይታይ ወይም በቀላሉ የማይለይ በመሆኑ ጉዳቱን ለመገምገም በአካባቢው ካሉ ሕንፃዎች ላይ በመንተራስ መተንተን አስፈልገዋል።
በምርመራው ምን ተገኘ?
ቢቢሲ ከተመለከታቸው 603 የውሃ ተቋማት ውስጥ ከመስከረም 26 በኋላ 53 በመቶ የሚሆኑት ተበላሽተዋል ወይም ተጎድተዋል።
ተጨማሪ 51 ጣብያዎች መጠነኛ ጉዳት ባስተናገዱ አካባቢዎች የጸሐይ ፓነሎች ተነስተዋል። የውሃ ተቋሙ ተጎድቷል የሚለውን ማወቅ ባለመቻሉ በነዚህ ትንታኔ ውስጥ አልተካተቱም።
አብዛኞቹ የወደሙ ወይም የተበላሹ ቦታዎች በሰሜን ጋዛ ወይም በደቡብ ዃን ዩኒስ ከተማ አካባቢ ይገኛሉ።
በቡሬጅ በሚገኝ አንድ የፈሳሽ ማጣሪያ ተቋም የሚያንቀሳቅሱትን የጸሐይ ፓናሎች ከመጎዳታቸውም በላይ የፍሳሽ ማጣሪያው ማጠራቀሚያዎች ላይ አልጌዎች የበቀሉ ይመስላሉ።
ሁሉም ጉዳቶች ከሳተላይት ምስሎች ስለማይታዩ ትንታኔው አንዳንድ የተጎዱ ጣብያዎችን ሳይዳስስ አምልጦ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጣቢያዎች ደግሞ በነዳጅ እጥረት ምክንያት ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ላይሰጡ ይችላሉ።
ለምሳሌ በዴይር አል-ባላ የሚገኘው የዩኒሴፍ የጨው ውሃ ማጣሪያ በነዳጅ እጥረት ምክንያት በ 30 በመቶ አቅሙ ብቻ እየሠራ መሆኑን ድርጅቱ ለቢቢሲ ተናግሯል።
አብዛኛዎቹ ጋዛውያን ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣብያዎች ውስጥ እየኖሩ በመሆኑ በጎዳናዎች ላይ ያለው የፍሳሽ ማስወገጃ የበለጠ ስጋት ፈጥሯል።
ለፍልስጤም የሰብዓዊ መብቶች ማዕከል የሚሠራው መሐመድ አታላህ "የፍሳሽ ማስወገጃ ፓምፖች ስለማይሠሩ መንገዶቹ በቆሻሻ ፍሳሽ ተጥለቅልቀዋል" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጥገና መጋዘን ላይ የሚደርስ ጉዳት
ግጭቱ የውሃ ተቋማትን ለመጠገን አስቸጋሪ አድርጎታል። ቁልፍ የጥገና ማዕከሎች አለመሥራታቸው ደግሞ ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል።
በአል-ማዋሲ የሚገኘው በጥር ወር በደረሰበት የሚሳኤል ጥቃት ክፉኛ ተጎድቷል። የአካባቢው ውሃ አገልግሎት እንዳለው በጥቃቱ አራት ሰዎች ሲሞቱ 20 ሰዎች ቆስለዋል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሞንዘር ሾብላክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት መጋዘኑ የተቋሙ እና የዩኒሴፍ መጋዘን ሆኖ ከማገልገል ባለፈ ከሁለት ሺህ በላይ ለጥገና የሚያገለግሉ ዕቃዎችን የያዘ ማዕከል ነበር።
ውድመቱ አገልግሎቱን የመጠገን እና የመንከባከብ ሥራ በእጅጉ ገድቦታል ብለዋል።
የእስራኤል ጦር መጋዘኑ ዒላማ እንዳልነበረ እና በአቅራቢያው የሚንቀሳቀሱ የሐማስ አሸባሪዎች መመታታቸውን ገልጿል። "በጥቃቱ ምክንያት የመጋዘኑ ክፍሎች ጉዳት ደርሶባቸዋል" ብሏል።
በትንተናው የተካተቱ አምስት የተበላሹ ወይም የወደሙ የውሃ መሠረተ ልማቶችን መረጃ ለእስራኤል ጦር ተሰጥቷል።
በአንዱ ላይ የአየር ድብደባ እንዳልተፈጸመ ገልጾ፤ በተቀሩት አራቱ የሐማስ ተዋጊዎች ወይም መገኛ በመሆናቸው ዒላማዎች መሆናቸውን አስታውቋል።
"ሐማስ መሳሪያዎቹን በእነዚህ ሲቪል ተቋማት ውስጥ ያከማቻል። ከስር ደግሞ የሽብር መሰረተ ልማቶችን ይገነባል። ከዚህም ጥቃቱን ይጀምራል" ብሏል።
በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ልዩ አማካሪ ሌይላ ሳዳት ለቢቢሲ እንደተናገሩት የተለየ ተጨባጭ ማስረጃ ከሌለ በስተቀር ለሲቪሎች ህልውና ወሳኝ የሆኑ ተቋማት ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል።
የጦርነት ድርጊቶችን ከህጋዊነት አንጻር ለመገምገም የእነዚያን ድርጊቶች "ድግግሞሽ" ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል ብለዋል።
"ጥቃት መድረሱን ብቻ መመልከት አይቻልም… [ጦሩ] የውሃ ቧንቧዎችን፣ ታንኮችን፣ የውሃ ማጠራቀሚያዎችን እና መሠረተ ልማቶችን መትተዋል" ብለዋል።
"ከግማሽ በላይ ውሃን እና የንፅህናን መሠረተ ልማት ሆን ሳይባል መጉዳት በጣም አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ ድግግሞሹ የሲቪል መሠረተ ልማቶች በግዴለሽነት ወይም ሆን ተብለው መጠቃታቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። እነዚህ ሁሉ ስህተቶች ሊሆኑ አይችሉም" ሲሉ አክለዋል።












