እስራኤል ራፋህን ከወረረች አሜሪካ የተወሰነ መሣሪያ መላክ እንደምታቆም ባይደን አስጠቀቁ

ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እስራኤል በራፋህ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከከፈተች አሜሪካ ከምትሰጣት የጦር መሣሪያ የተወሰነውን መላክ እንደምታቆም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስጠነቀቁ።

ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ራፋህ ውስጥ ከገቡ ከዚህ ቀደም ራፋህ ላይ የተጠቀሙባቸውን መሣሪያዎች አልክም” ብለዋል።

ሆኖም “የእስራኤልን ደኅንነት ማስጠበቅ ግን እቀጥላለሁ” ሲሉ አክለዋል።

አሜሪካ ተቃውሞ ብታሰማም እስራኤል ራፋህን ለመውረር ቆርጣ የተነሳች ይመስላል።

በሰዎች የተጨናነቀው ይህ አካባቢ ሐማስ በብዛት የሚገኝበት ነው።

ከተማ ውስጥ የሚካሄድ ወረራ ከጋዛ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎችን ለአደጋ እንደሚያጋልጥና የንጹኃንን ሞት እንደሚያስከትል አሜሪካ አስጠንቅቃለች።

ባይደን መሣሪያ እንደማይልኩ በገለጹበት ቃለ ምልልስ፣ ራፋህ ውስጥ እግረኛ ጦር ማስገባት ያለውን ጠቀሜታ አሜሪካ እንዳልተቀበለችው አስረድተዋል።

“ለጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁና ለጦርነት ካቢኔው ድጋፋችንን እንደማንሰጣቸው ተናግሬያለሁ” ብለዋል።

የአሜሪካ የጦር መሣሪያ በጋዛ ንጹኃንን ለመግደል መዋሉን አምነዋል።

እስራኤል ቀዩን መስመር አልፋለች? ተብለው ሲጠየቁ “ገና አላለፈችም” ብለው መልሰዋል።

እስራኤል ላይ የሰላ ትችት ሲሰነዝሩና መሣሪያ እንደማይልኩ ሲገልጹ ይህ የመጀመሪያው ነው።

በሺዎች የሚቆጠሩ ፈንጂዎች ወደ እስራኤል የሚላኩበት ጊዜ እንዲዘገይም ተወስኗል።

መከላከያ ሚኒስትሩ ሎይድ ኦስተን በምክር ቤት ቀርበው፣ በምዕራቡ ዓለም ከፍተኛ አውዳሚ የሚባሉ ቦምቦችን ለመላክ እንደሚዘገዩ ተናግረዋል።

እስራኤል ቦምብ እየጣለች ካለችበት ፍጥነት አንጻር የመሣሪያዎቹ መዘግየት መስተጓጎል ሊፈጥርባት ይችላል።

የእስራኤል መከላከያ ከአሜሪካ ጋር ያለውን ልዩነት ከመጋረጃ በስተጀርባ እንደሚፈቱ አስታውቋል።

ዴሞክራቶች ባይደን በጋዛ የሚደርሰውን እልቂት እንዲያስቆሙ ጫና እያደረጉ ነው።

በደቡባዊ ጋዛ ሁለት ዋነኛ ሰብአዊ አቅርቦቶች እንዳልገቡ ተገልጿል።

የእስራኤል መከላከያ ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጊሪ፣ አሜሪካ “ያልተጠበቀ” የፀጥታ ድጋፍ መስጠቷን ገልጸዋል።

የሉኪድ ፓርቲ አባል ቦአዝ ቢስሙት ለቢቢሲ በሰጡት ቃል፣ መሣሪያ የማዘግየት ውሳኔው የአሜሪካ ውስጣዊ ፖለቲካ ውጤት ነው ብለዋል።

ራፋህ ወደ ጋዛ እርዳታ በዋናነት የሚገባባት መተላለፊያ ናት።

ሰዎች መሸሽ የሚችሉትም በራፋህ በኩል ነው።

እስራኤል መተላለፊያውን ዘግታለች።

በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከምሥራቃዊ ራፋህ እንዲወጡ ማስጠንቂያ ሰጥታለች።

በሌላ በኩል የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥረቱ ቀጥሏል።

የተኩስ አቁም ተደርጎ እስራኤላውያን ታጋቾችና ፍልስጤማውያን እስረኞች እንዲለቀቁ እየተሞከረ ነው።

በካይሮ በሚደረገው ውይይት የእስራኤልና ሐማስ ተወካዮች ተገኝተዋል።

ከእስራኤል ጋር የሚደረገው ውይይት እንደቀጠለ የአሜሪካ ተወካይ ተናግረዋል።