በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ ውዝግብ የፈጠረውን ‘ቲክቶከር’ ጨምሮ 6 ግለሰቦች የሽብር ወንጀል ምርመራ ተከፈተባቸው

ቲክቶከሩን ጨምሮ ለበረራ በተዘጋጀ አውሮፕላን ላይ አምባጓሮ የፈጠሩ 6 ተከሳሾች ምርመራ ተከፈተባቸው

የፎቶው ባለመብት, SM

የምስሉ መግለጫ, ቲክቶከሩን ጨምሮ ለበረራ በተዘጋጀ አውሮፕላን ላይ አምባጓሮ የፈጠሩ 6 ተከሳሾች ምርመራ ተከፈተባቸው

ከቀናት በፊት ከአዲስ አበባ ወደ መቀለ ለመብረር በዝግጅት ላይ በነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ አምባጓሮ በፈጠሩ ስድስት ግለሰቦች ላይ የሽብር ወንጀል ምርመራ ተከፈተ።

በዕለቱ አውሮፕላኑ በአካባቢ በነበረው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ መብረር እንደማይችል ቢገለጽም፤ በዚህ በረራ ላይ ተሳፋሪ የነበሩ ተሳፋሪዎች ከአውሮፕላን “አንወርድም” በማለት ከአየር መንገዱ ሠራተኞች ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ሲገቡ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በተለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ታይተዋል።

አውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩ ተሳፋሪዎች መካከል ቲክቶክ በተሰኘው ማኅበራዊ ሚድያ በርካታ ተከታዮች ያሉት 'ጆን ዳንዔል' በተባለው ግለሰብ በቀጥታ አማካይነት በተላለፈው ቪድዮ ተሳፋሪዎች “አንወርድም” ሲሉ ተደምጠዋል።

በዚህም ሳቢያ ክስተቱ መነጋገሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ የውዝግቡ ተሳታፊዎች በተለይም ዮሐንስ ዳንዔል በተባለው ቲክቶከር ላይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ጠንካራ ውግዘት እና ትችት ሲሰነዘርበት ነበር።

አንዳንዶችም አየር መንገዱ እና የሕግ አስከባሪ አካላት ጠንከር ያለ እርምጃን እንዲወስዱ ሲጠይቁ ነበር።

ይህን ውዝግብ ተከትሎ ቲክቶከሩን ጨምሮ ሌሎች ተሳፋሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተሰማው ከቀናት በፊት ነው።

የፌደራል ፖሊስ እሑድ ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም. ባወጠው መረጃ ጆን ዳንዔል በመባል የሚታወቀው ቲክቶከር እና ሌሎች 5 ግለሰቦች የሽብር ወንጀል ምርመር እንደተከፈተባቸው አመልክቷል።

ዮሐንስ ዳንዔል፣ አማኑኤል መውጫ፣ ናትናኤል ወደንወሰን፣ ኤሊያስ ድሪባ፣ ይዲድያ ነፃነት እና እሌኒ ክንፈ የተባሉት ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ይገኛሉ።

ፖሊስ እንዳለው ስድስቱ ተጠርጣሪዎች “ተፈጥሮ በነበረው የአየር መዛባት ምክንያት አውሮፕላኑ መብረር አይችልም እየተባለ፣ አስገድዶ ለማስኬድ የፈጠሩት አምባጓሮ በወንጀል ሕጉ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል።”

ተሳፋሪዎቹ ከአውሮፕላን “አንወርድም” በማለት ከፈጠሩት ውዝግብ ባለፈ “ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ተልዕኮ ተቀብለው የተንቀሳቀሱ በመሆናቸው በሽብር ወንጀል” መጠርጠራቸውን እና ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑም ተገልጿል።

ስድስቱ ተጠርጣሪዎች “በተላለፉት የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የበረራ አሠራር ጥሰት ብሎም በሽብር ወንጀሎች የምርመራ መዝገብ ነገ ነሐሴ 20/2016 ዓ.ም. ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ” ተሰምቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሐሙስ ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም. በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቹ በለቀቀው መረጃ “በአየር ፀባይ ምክንያት በርካታ አውሮፕላኖች ቦሌ አየር ማረፊያ ማረፍ ባለመቻላቸው ወደሌሎች አማራጭ አየር ማረፊያዎች እየሄዱ” መደረጋቸውን ገልፆ ነበር።

“መቼም ቢሆን የተሳፋሪዎቻችን ደኅንነት ቅድሚያ የምንሰጠው ነው” ያለው አየር መንገዱ በወቅቱ በነበረው የአየር ፀባይ ምክንያት የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ በረራዎች መስተጓጎላቸውንም አሳውቆ ነበር።