በደቡብ እስያ በደረሰ የጎርፍ መጥለቅለቅ እና የመሬት መንሸራተት ከ600 በላይ ሰዎች ሞቱ

በደቡብ እስያ በደረሰ ከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅ 600 ያህል ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በደቡብ ምሥራቅ እስያ ከአስር ዓመታት በኋላ ቀጠናውን ያጋጠመውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ ጎርፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም።

በሞቃታማው አውሎ ንፋስ የተባባሰው የመጣው ዝናብ በዓመታት ውስጥ ከታዩት የጎርፍ አደጋዎች መካከል ከፍተኛውን አስከትሏል።

በዚህም የተነሳ በኢንዶኔዥያ፣ ማሌዢያ እና ታይላንድ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ተጎድተዋል።

በኢንዶኔዢያ ሱማትራ ደሴት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ300 በላይ የተሻገረ ሲሆን በርካቶች አሁንም ያሉነት እንደማይታወቅ ተገልጿል።

በጎርፍ ከተጎዱት አካባቢዎች ነዋሪዎችን የማውጣት ጥረቱ አሁንም የቀጠለ ሲሆን ዋና ዋና መንገዶች በጎርፍ በመወሰዳቸው እና የኢንተርኔት እና የመብራት አገልግሎት በከፊል በመቋረጡ ጥረቱን አስቸጋሪ አድርጎታል።

እስከ ቅዳሜ ድረስ ብቻ በታይላንድ 160 ሰዎች፣ በማሌዥያም እንዲሁ በርካታ ሰዎች መሞታቸውም ተዘግቧል።

በኢንዶኔዢያ ሳይክሎን ሴንያር የተባለ አውሎ ንፋስ የቀለቀለ ዝናብ የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ መጥለቅለቅን አስከትሏል።

በዚህም የተነሳ ቤቶች በጎርፍ ሲወሰዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕንፃዎች ሰጥመዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኢንዶኔዥያ አሲህ ግዛት ነዋሪ የሆነችው አሪኒ አማሊያ "ጎርፉ በጣም ፈጣን ነበር፣ በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ነው ወደ መንገዶቹ የደረሰው፣ ከዚያም ወደ ቤቶቹ እየተንደረደረ ገባ" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

እርሷና ቅድመ አያቷ ከፍ ባለ ቦታ ላይ ወደሚገኝ በፍጥነት ማምራታቸውን ጨምራ ተናግራለች።

በማግሥቱ አንዳንድ ንብረቶችን ለማምጣት ወደ ቤቷ ስትመለስ ጎርፉ ቤቱን ሙሉ በሙሉ መዋጡን ስታስረዳ "ሙሉ በሙሉ ሰምጧል" ብላለች።

በምዐዕራብ ሱማትራ የሚኖረው ሜሪ ኦስማን ደግሞ በአካባቢው በጣለው ከፍተኛ ዝናብ የተነሳ የውሃው መጠን በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መጥቶ "በጎርፍ ተወስጄ ነበር" በማለት የሕይወት አድን ሰራተኞች እንሰኪመጡ ድረስ በጨርቅ ላይ ተንጠላጥሎ መቆየቱን ተናግሯል።

በሱማትራ አሲህ ግዛት የቢሬየን ነዋሪ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት በጎርፉ ወቅት ሁሉም ነገር ወድሟል። "ልብሴን ማዳን ፈልጌ ነበር፤ ነገር ግን ቤቴ ሰመጠ።"

መጥፎው የአየር ሁኔታ የሕይወት አድን ሥራዎችን አስተጓጉሏል።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤታቸው እንዲወጡ ቢደረግም፣ አሁንም በመቶዎች የሚቆጠሩ መውጫ አጥተው እንደሚገኙ የኢንዶኔዥያ የአደጋ ኤጀንሲ አስታውቋል።

የከፋ ጉዳት በደረሰበት በታፓኑሊ ከተማ ነዋሪዎች ምግብ ፍለጋ የግሮሰሪ ሱቆችን ዘርፈዋል።

ፈጣን እና የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት እንዲያስችል በሚል ጃካርታ፣ በሱማትራ ብሔራዊ አደጋ ጊዜ አዋጅ አውጃለች።

በታይላንድ ደቡባዊ ሶንግኽላ ግዛት የውሃው መጠን 3 ሜትር ያህል ከፍ ያለ ሲሆን ቢያንስ 145 ሰዎች ሞተዋል።

እህም በአገሪቱ በአስር ዓመታት ውስጥ ከታዩት አስከፊ ጎርፎች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል።

በጎርፍ በተከሰቱት 10 ግዛቶች ከ160 በላይ ሰዎች መሞታቸውን መንግሥት ቅዳሜ ዕለት ገልጿል። ከ 3.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በማሌዥያ የሟቾች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም የደረሰው ጉዳት ግን አስከፊ ነው።

በሌላ የእስያ ክፍል በስሪላንካ በሳይክሎን ዲትዋህ ተጠቅታ ከ130 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እና 170 ደግሞ ያሉበት አለመታወቁን የአገሪቱ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ስሪላንካ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ካጋጠሟት አስከፊ የአየር ንብረት አደጋዎች አንዱን የተጋፈጠች ሲሆን መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።

ከ15,000 በላይ ቤቶች መውደማቸውን እና 78,000 የሚያህሉ ሰዎች ወደ ጊዜያዊ መጠለያ እንዲገቡ መደረጋቸውን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል። ከአገሪቱ አንድ ሶስተኛው የመብራት እና የውሃ አቅርቦት አልባ እንደሆነም ጨምረው አስታውቀዋል።