በኡጋንዳ እና በኬንያ በደረሱ የመሬት መንሸራተቶች የሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

የ30 ዓመቱ ፍሌክሲ ስድስት የቤተሰቡ አባላትን በመሬት መንሸራተት አደጋ አጥቷል

የፎቶው ባለመብት, Duncan Wanga

የምስሉ መግለጫ, የ30 ዓመቱ ፍሌክሲ ስድስት የቤተሰቡ አባላትን በመሬት መንሸራተት አደጋ አጥቷል

ባለፈው ሳምንት በኬንያ እና በኡጋንዳ ተራራማ የድንበር አካባቢዎች በተደጋጋሚ በደረሱ የመሬት መንሸራተቶች ከ40 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

በኬንያ ድንበር የሚኖረው ፍሌክሲ ኬምቦይ "አያቴን፣ አራስ አክስቴን፣ አጎቴን፣ ሁለት እህቶቼን፣ የቤተሰባችን ጓደኛን እንዲሁም የአጎቴን ልጅ አጣሁ። በካፕቱል መንደር አብረው ነበር የነበሩት" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

የ30 ዓመቱ ፍሌክሲ የደረሰበትን መከራ እና የተሰማውን ሐዘን ለመግለጽ ቃላቶችን በወጉ ለማስቀመጥ ሲቸገር ታይቷል።

በሁለቱም አገራት ድንበሮች አካባቢ አሁንም ድረስ የጠፉ እና ያልተገኙ ሰዎች ያሉ ሲሆን የሕይወት አድን ሠራተኞች ፍለጋቸውን መቀጠላቸው ተገልጿል።

በአካባቢው አሁንም ሌላ የመሬት መንሸራተት አደጋ ይደርሳል በሚል ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥተዋል።

"በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ ሲዘንብ በተለይ ደግሞ በኬሪዮ ቫሊ ክልል የመሬት መንሸራተት አደጋ ይጨምራል" ሲሉ የኬንያ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ኪፕቹምባ ሙርኮሜን ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ማንኛውንም የመሬት ሁኔታ በጥንቃቄ እንዲመለከቱ እና የአካባቢው ባለሥልጣናት ለአደጋ የተጋለጡትን ሰዎች ወደ ተሻለ ስፍራ እንደሚያዘዋውሩ ተናግረዋል።

በግሬት ሪፍት ቫሊ አካባቢ በደረሰ የመሬት መንሸራተት ከሞቱት መካከል 14 ተማሪዎች እንደሚገኙበት የአገሪቱ የትምህርት ሚኒስትር ይፋ አድርጓል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በምሥራቅ ኡጋንዳ በመሬት መንሸራተት አደጋው የተረፉ ሰዎች የደረሰውን ሰቅጣጭ አደጋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ማታ ተኝተን ነበር። በጣም የሚጮህ ደምጽ ሰማን። ጎረቤቶቻችን እየሮጡ መጡ። 'ነቅታችኋል። ተራራው እየተናደ ነው' ሲሉ ቀሰቀሱን። የወንድሜ ልጅ እና ወንድሜ ሞተዋል" ስትል ሄልዳ ናሩንጋ ማሳይ ሁኔታውን ታስታውሳለች።

በክዌን መንደር ያለው ቤቷ በመሬት መንሸራተት ስለወደመ አሁን ተጠግታ የምትኖረው ከጎረቤቶቿ ጋር ነው።

በካፕቾርዋ ከዋናው መንገድ 14 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ መንደር የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሦስት ልጆች እና አንዲት ሴት ሞተዋል።

የኡጋንዳ ቀይ መስቀል ሠራተኞች ቢያንስ 18 ሰዎች በአገሪቱ ምሥራቃዊ አካባቢ መሞታቸውን ይናገራሉ።

የቀይ መስቀል ሠራተኞች እና በጎ ፈቃደኞች አሁንም በካፕቾርዋ፣ ቡክዎ እና ክዌን ዲስትሪክቶች 20 ሰዎች የደረሱበት ባለመታወቁ ፍለጋቸውን ቀጥለዋል።

ማንዴ ዳቪድ ካፕቼሮንጌ ለቢቢሲ እንደተናገረው የሕይወት አድን ሠራተኞች ከጭቃ ውስጥ አስከሬኖቹን ለማውጣት የሚጠቀምበት መሣሪያ ኋላ ቀር ነው።

ባለሙያዎች በኬንያ አና ኡጋንዳ በተደጋጋሚ የመሬት መንሸራተት በሚያጠቃቸው አካባቢዎች መኖሪያ ቤት እንዳይገነባ ሲያስጠነቅቁ ነበር።

እአአ በ2010 በኡጋንዳ ቡዱዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት ቢያንስ 300 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ይህም በአገሪቱ ከደረሱ የተፈጥሮ አደጋዎች ሁሉ የከፋው ሆኖ ተመዝግቧል።

ለዚህ የቅርብ ጊዜ አደጋ ምላሽ የኡጋንዳ መንግሥት ለሟች ቤተሰቦች በአጠቃላይ 5 ሚሊዮን ሽልንግ እና 1ሚሊዮን ሽልንግ ደግሞ በሕይወት ለተረፉ ግለሰቦች ለመክፈል ወስኗል።

የኬንያ መንግሥት እስካሁን ድረስ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ እና ለተረፉ ሰዎች ስለሚሰጠው ካሳ ያለው ነገር የለም።

በኡጋንዳ በመሬት መንሸራተት አደጋው የተነሳ ዋና መንገዶች በመዘጋታቸው ፍለጋውን አስቸጋሪ አድርጎታል።