በቬትናም በተከሰተ የጎርፍ አደጋ 90 ሰዎች ሲሞቱ 12 ሰዎች ደብዛቸው ጠፋ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በቬትናም ለቀናት በጣለ ከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት 90 ሰዎች ሲሞቱ 12 ሰዎች እስካሁን ያሉበት አልታወቀም።
የቬትናም መንግሥት በመላ አገሪቱ 186 ሺህ ቤቶች በጎርፉ መውደማቸውን እና ከ3 ሚሊዮን በላይ ከብቶች መሞታቸውን ገልጿል። ባለሥልጣናት በመቶ ሚሊዮን ፓውንድ የሚያወጣ ውድመት መድረሱን ግምት አስቀምጠዋል።
ኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው ተራራማ የሆነው የዳክ ላክ ግዛት ክፉኛ የተጎዳ ሲሆን ካለፈው ኅዳር 7 ወዲህ 60 በአካካቢው ነዋሪ የነበሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በጥቂት ሳምንታት ልዩነት ካልሜጊ እና ቡዋሎይ የተሰኙ አውሎ ንፋሶች በአገሪቱ ከተከሰቱ በኋላ፤ የጎርፍ አደጋው ባለፉት ወራት ቬትናምን የመታ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው።
እሑድ ጠዋት 258,000 የሚሆኑ ሰዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አጥተው የነበረ ሲሆን፤ ዋና ዋና መንገዶች እና የባቡር ሀዲዶች ክፍሎች ተዘግተዋል ሲሉ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ለመርዳት ወታደራዊ እና የፖሊስ ኃይሎች ተሰማርተዋል።
መንግሥት ኩዋንግ ንጋይ፣ ጂያ ላይ፣ ዳክ ላክ፣ ካንህ ሆአ እና ላም ዶንግ የተሰኙ አምስት ግዛቶች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግሯል።
በዳክ ላክ የሚኖሩ ማች ቫን ሲ የተባሉ ገበሬ "ሰፈራችን ሙሉ በሙሉ ወድሟል። የቀረ ምንም ነገር አልነበረም። ሁሉም ነገር በጭቃ ተሸፍኗል" ሲሉ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺንህ እሑድ ጠዋት የቡድን 20 ጉባኤን እየተከታተሉ ከሚገኙበት ከደቡብ አፍሪካ በበይነ መረብ የአደጋ ጊዜ ስብሰባን መርተዋል።
እስከ አርብ ዕለት ድረስ በበርካታ አካባቢዎች የዝናብ መጠኑ ከ1.5 ሜትር (5 ጫማ) በላይ ሲሆን አንዳንድ አካባቢዎች እአአ ከ1993 ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ 5.2 ሜትር ከፍታ አልፈዋል። ዝናቡ በሚቀጥሉት ቀናት እንደሚቀንስ ይጠበቃል።
ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ቬትናም በሰው ሠራሽ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለከባድ የአየር ሁኔታ ክስተቶች የበለጠ ተጋላጭ ሆናለች፣ ይህም አውሎ ነፋሶችን የበለጠ ጠንካራ እና ተደጋጋሚ አድርጓቸዋል።















