የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት "የጤና ባለሙያዎችን በማዋከብ የአገሪቱን የጤና ችግር መፍታት አይችሉም" - ሂውማን ራይትስ ዋች

የፎቶው ባለመብት, thiopian Health professionals
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት "የጤና ባለሙያዎች ማኅበርን በማገድ፣ ባለሙያዎችን በማሰር እና በማዋከብ አሳሳቢ የሆነውን የአገሪቱን የጤና ችግር መፍታት እንደማይችሉ" የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪው ሂውማን ራይትስ ዋች ገለጸ።
ሂውማን ራይትስ ዋች የጤና ባለሙያዎቹ ያነሷቸውን "ተገቢ ጥያቄዎች ትርጉም ባለው ውይይት መፈታት አለባቸው" ሲሉ የተቋሙ የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደርን ዋቢ አድርጎ ረቡዕ፣ ሰኔ 18/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
የሕክምና ባለሙያዎቹ ከተመጣጣኝ ደመወዝ፣ ጥቅማጥቅም፣ የሙያ ዕድገት ዕድሎች እንዲሁም ከምቹ የሥራ ቦታ እና የሥራ ቦታ ነጻነት ጋር የተያያዙ ባለ 12 ነጥብ ጥያቄዎችን ለጤና ሚኒስትር ሚያዝያ 3/2017 ዓ.ም. ማቅረባቸው ይታወሳል።
ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ ባለመሰጠቱም ከግንቦት 10/2017 ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ የሥራ ማቆም አድማ አድርገው ነበረ።
አድማውን ተከትሎ መንግሥት በጤና ባለሙያዎቹ ላይ እስር፣ ማዋከብ፣ የሥራ የማባረር ዛቻዎች፣ አዲስ የሥራ ቅጥር ማውጣት እና ሌሎች ጫናዎች መድረሱን ተቋሙ በመግለጫው አስፍሯል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ከሥራ ማቆም አድማ ጋር ተያይዞ አመራሩ ታስረውበት የነበረው የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማኅበር ሰኔ 5/ 2017 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ታግዷል።
የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማኅበር እገዳን በአስቸኳይ እንዲያነሱ ሂውማን ራይትስ ዋች በዚህ መግለጫው ባለሥልጣናቱን የጠየቀ ሲሆን፤ አክሎም "የጤና ባለሙያዎች ቅሬታዎችን በአግባቡ ይፍቱ" ብሏል።
በአገሪቱ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ በመጠየቃቸው ባለሥልጣናቱ ለእስር እንደዳረጓቸውም ጠቅሷል።
የሥራ ማቆም አድማው ከተጀመረበት ከግንቦት 5/2017 ዓ.ም. ጀምሮ 148 የጤና ባለሙያዎች ታስረው እንደነበር በበይነ መረብ ላይ ያለ የጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ መረጃ እንደረሰው ሂውማን ራይትስ ዋች ገልጾ ሆኖም አኃዙን አላጣራሁም ብሏል።
ፌደራል ፖሊስ በበኩሉ 47 የጤና ባለሙያዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቆ ነበር።
"ከግንቦት ወር ጀምሮ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የጤና ባለሙያዎች ከተመጣጣኝ ደመወዝ፣ ጥቅማ ጥቅም እና ከምቹ የሥራ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ከመመለስ ይልቅ አፋኝ ዘዴዎችን ተጠቅመዋል" ሲሉ ላቲሺያ ወቅሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አክለውም "መንግሥት የጤና ባለሙያዎች ማኅበር ላይ የጣለውን እገዳ በአስቸኳይ እንዲያነሳ እንዲሁም በጤና ባለሙያዎች ላይ እያደረሰ ያለውን ወከባ ሊያቆም ይገባል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማኅበር በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የታገደው "ጠቅላላ ጉባኤ አላካሄዳችሁም" እንዲሁም የፋይናንስ ሪፖርት አላቀረባችሁም በሚል እንደሆነ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ዮናታን ዳኜ ከዚህ ቀደም ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ማኅበራቸው "የአገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው እና መመሪያዎችን በመከተል" እንደሚንቀሳቀሱ የገለጹ ሲሆን፣ ይህ እግድ ከጤና ባለሙያዎች እንቅስቃሴ ጋር የተገናኘ ነው" ብለው መናገራቸው ተቋሙ ሚዲያዎችን አጣቅሶ በዚህ መግለጫው አካቷል።
የጤና ባለሙያዎቹን ጥያቄዎች ከፊት ሆኖ ሲያንቀሳቅስ የነበረው ማኅበሩ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አዘጋጅነት ከመንግሥት ጋር በተደረገ ውይይት ተሳትፎ የነበረ ቢሆንም ለችግሮቹ እልባት መስጠት እንዳልተቻለም ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ የሕብረሰብ ጤና አጠባባቅ ወጪ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) አንጻር ሲሰላ 0.7 በመቶ ሲሆን፣ ይህም በዓለም አቀፍ መመዘኛ ከተቀመጠው እጅጉን ያነሰ መሆኑን ከሦስት ዓመታት በፊት የወጣውን የዓለም ጤና ድርጅትን መረጃ ዋቢ አድርጎ ተቋሙ በዚህ መግለጫው አስፍሯል።
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት የጤና አጠባበቅ ወጪያቸው በአማካይ 1.2 በመቶ መሆኑም በዚሁ መግለጫ ተጠቅሷል።
የጤና መድን ሽፋን አለመዘርጋት፣ ከሥራ ጋር በተያያዙ አደጋዎች በቂ ካሳ አለማግኘት፣ የደመወዝ መዘግየት እና ሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች ሲንከባለሉ የቆዩ ነገሮች መሆናቸውን የጤና ባለሙያዎቹ ይጠቅሳሉ።
የጤና ባለሙያዎቹ የሕብረተሰቡን ጤናን በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ቢጫወቱም የጤና ባለሙያዎች በአማካይ የሚያገኙት በወር 80 ዶላር ሲሆን ነርሶች፣ የጤና መኮንኖች እና ሌሎች ባለሙያዎች ከዚህ ያነሰ እንደሚከፈላቸው አምነስቲ ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።
አምነስቲ የኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ለማጠናከር እና በሰላማዊ ተቃውሞ ላይ ያሉ የጤና ባለሙያዎችን መብት ለማስጠበቅ የልማት አጋሮች የሁለትዮሽ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርጓል።
"ባለሥልጣናት ከዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ግዴታዎቻቸው ጎን ለጎን ከፍተኛውን ሃብት እንደ ጤና ላሉ ወሳኝ የሕዝብ አገልግሎቶች መመደባቸውን ለማረጋገጥ አስቸኳይ እርምጃዎችን መውሰድ አላባቸው" ሲል በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አጽንኦት ሰጥቶ ነበር።
ይህንን እልባት ለመስጠት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሳምንት በፊት ከተመረጡ የጤና ባለሙያዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጤና ባለሙያዎቹ ያነሷቸው የደመወዝ ጭማሪ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ተገቢነት ቢኖረውም "የፖለቲካ ኪሳራ በገጠማቸው እና ሐኪም መሳይ ጋወን ለባሽ" ባሏቸው ሰዎች ተጠልፏል ብለዋል።
ከግንቦት መጀመሪያ አንስቶ የሥራ ማቆም አድማ የመቱት የጤና ባለሙያዎች ከሰኞ ሰኔ 9/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ መመለሳቸውን ከሰሞኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
'የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ' በሚል ማዕቀፍ የሚታወቁት ባለሙያዎቹ ሲያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ "የመጀመሪያ ምዕራፍ" እንቅስቃሴያቸው የተሳካ እንደነበር ለቢቢሲ የተናገሩ አንድ የንቅናቄው አስተባባሪ፤ ለጤና ሚኒስቴር ያቀረቧቸው አራት ቅድመ ሁኔታዎች በከፊል በመሟላታቸው እና ለማኅበረሰቡ ሲሉ ወደ ሥራ መመለሳቸውን ገልፀዋል።
አንዳንድ የጤና ተቋማት ግን የጤና ባለሙያዎች ወደ ሥራ "አትመለሱም" በሚል ክልከላ እንደተረገባቸውም አስታውቀዋል።




![ለአንዲት ታዳጊ ክትባት የሚሰጥ ባለሙያ [ፎቶ ከፋይል]](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/660/cpsprodpb/9197/live/8d76d130-4c34-11f0-96bb-172b7e186897.jpg.webp)










