የሥራ ማቆም አድማ መትተው የነበሩ የጤና ባለሙያዎች ከአንድ ወር በኋላ ወደ ሥራ ተመለሱ
![ለአንዲት ታዳጊ ክትባት የሚሰጥ ባለሙያ [ፎቶ ከፋይል]](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/9197/live/8d76d130-4c34-11f0-96bb-172b7e186897.jpg.webp)
የፎቶው ባለመብት, Ministry of Health/fb
ከግንቦት መጀመሪያ አንስቶ የሥራ ማቆም አድማ የመቱት የጤና ባለሙያዎች ከሰኞ ሰኔ 9/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ መመለሳቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።
ባለሙያዎቹ ባለፉት ወራት የደመወዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎችን ጨምሮ የባለሙያውን ሕይወት እና የጤና ሥርዓቱን ያስተካክላሉ ያሏቸውን 12 ጥያቄዎች አቅርበዋል።
መንግሥት ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ እንዲሰጥ "የማስጠንቀቂያ" ቀነ ገደብ ያስቀመጡት ባለሙያዎቹ ጥቃቄዎቻቸው ትኩረት በማጣታቸው ከግንቦት 10/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ የሥራ ማቆም አድማ መምታታቸውን ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም መንግሥት ፈርጠም ያለ አፃፋዊ እርምጃዎችን የወሰደ ሲሆን፤ እስራትን ጨምሮ ከሥራ ማሰናበት፣ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ አዲስ የሥራ ቅጥር ማውጣት እንዲሁም "ዛቻ እና ጫና" እንዳደረሰባቸው ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።
'የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ' በሚል ማዕቀፍ የሚታወቁት ባለሙያዎቹ ሲያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ "የመጀመሪያ ምዕራፍ" መጠናቀቁን በማስታወቅ ከሰኞ ሰኔ 9/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ መመለሳቸውን ሁለት አስተባባሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የመጀመሪያው ምዕራፍ" እንቅስቃሴያቸው የተሳካ እንደነበር ለቢቢሲ የተናገሩ አንድ የንቅናቄው አስተባባሪ፤ ለጤና ሚኒስቴር ያቀረቧቸው አራት ቅድመ ሁኔታዎች በከፊል በመሟላታቸው እና ለማኅበረሰቡ ሲሉ ወደ ሥራ መመለሳቸውን ገልፀዋል።
"ሕዝቡ እየተበደለ እንደሆነ እያየን ነበር። በጣም ብዙ መጎላላቶች ነበሩ። ከማኅበረሰቡ እንደወጣ ባለሙያ ይህን መቀበል አልቻልንም" የሚሉት አስተባባሪው፤ ወደ ሥራ የተመለሱበትን ዋነኛ ምክንያት ሲያስረዱ "የማኅበረሰቡ ለቅሶ እና ጩኸት ግድ ስላለን ነው" ብለዋል።
ሌላ የንቅናቄው አስተባባሪም "ሁላችንም ወደ ሥራ እና ትምህርት ተመልሰናል" ሲሉ ከሳምንቱ መጀመሪያ አንስቶ ባለሙያዎቹ ከአድማቸው መመለሳቸውን ገልፀዋል።
አንዳንድ የጤና ተቋማት ግን የጤና ባለሙያዎች ወደ ሥራ "አትመለሱም" በሚል ክልከላ እንደተረገባቸውም አስታውቀዋል።
የጤና ባለሙያዎቹ የሥራ ማቆም አድማ ከመቱ በኋላ ታካሚዎች መስተጓጎላቸውን የተናገሩ ሌላ አስተባባሪ፤ ባለሙያዎች ወደ ሥራ ሲመለሱ የጤና ሥርዓቱ "ብዙ መናጋት" እንደገጠመው መረዳታቸውን አመልክተዋል።
በሥራ ማቆም አድማው ታካሚዎች እና የጤና ሥርዓቱ ላይ የደረሰውን ጉዳት በሚመለከት እስካሁን በመንግሥት የተባለ ነገር ባይኖርም፤ ከዚህ ቀደም ጤና ሚኒስቴር የተፈጠረ ክፍተት አለመኖሩን አስታውቆ ነበር።
ከጤና ባለሙያዎች ጥያቄ ጋር በተያያዘ በመላው አገሪቱ ከ100 በላይ ባለሙያዎች በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውለው ነበር።
ፌደራል ፖሊስ ባለፈው ወር የጤና ባለሙያዎችን "የመብት ጥያቄ ሽፋን በማድረግ"፤ "ትርምስ እንዲፈጠር ከሚሠሩ ኃይሎች ጋር ያበሩ" ያላቸውን 47 የጤና ባለሙያዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
ባለሙያዎቹ "ብሔርን ከብሔር ማጋጨት"፣ "ሁከት እና ብጥብጥ ማነሳሳት" በሚሉ እና በሌሎች ከባድ ወንጀሎች ተጠርጥረው ለሳምንታት በእስር ቆይተዋል።
እነዚህ ባለሙያዎች ከእስር እንዲፈቱ ለጤና ሚኒስቴር ቅድመ ሁኔታ ማቅረባቸውን የተናገሩት አስተባባሪዎቹ፤ ሁሉም ባለሙያዎቹ መፈታታቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
"እኛ እስካለን መረጃ ድረስ ሁሉም እንደተፈቱ ነው" ብለዋል።
አብዛኞቹ የጤና ባለሙያዎች የክስ መዝገባቸው ሳይዘጋ በዋስ እንደተፈቱም ተናግረዋል።
"አግባብ" ባልሆነ መልኩ ከሥራ የተሰናበቱ እና የታገዱ የጤና ባለሙያዎችን ጉዳይ በሚመለከት በሕግ እንደሚጠይቁ አስተባባሪው ተናግረዋል።
ባለሙያዎቹ አበክረው ላነሷቸው 12 ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ ካላገኙ በሁለተኛ ምዕራፍ "አዲስ አቅጣጫ ቀይሰው" ጥያቄያቸውን ለማስመለስ እንደሚጥሩ አስታውቀዋል።
መንግሥት "እንደአያያዙ [ጥያቄያችንን] የሚመልስልን አይመስለንም" ያሉ አንድ አስተባባሪ፤ ዳግም የሥራ ማቆም አድማ ማድረግን ጨምሮ ሌሎች እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ጠቁመዋል።
"በደንብ ተደራጅተን እንደመጣለን" ያሉት ባለሙያዎቹ፤ በሚቀጥሉት ወራት በመንግሥት የሚሰጣቸውን ምላሽ ተመልክተው ወደ "ሁለተኛው ምዕራፍ" እንደሚሸጋገሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።




![የሕክምና ባለሙያ [ከጀርባ የሩዋንዳ ባንዲራ]](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/660/cpsprodpb/97b4/live/b2ae03c0-03b4-11ef-bee9-6125e244a4cd.png.webp)










