የጤና ባለሙያዎች የሥራ ማቆም አድማ በኢትዮጵያ ሕጎች እንዴት ይታያል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካለፈው ማክሰኞ ግንቦት 5/2017 ጀምሮ በኢትዮጵያ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ከፊት የሥራ ማቆም አድማ ላይ ናቸው። ባለሙያዎቹ የሥራ ማቆም አድማውን የመቱት ከአንድ ወር በፊት ለጤና ሚኒስቴር እና ለሌሎች የመንግሥት ተቋማት ያቀረቡት ቅሬት ምላሽ ባለማግኘቱ ነው።
የጤና ባለሙያዎችን የሥራ መቆም አድማ ተከትሎ ሆስፒታሎች እና የጤና ተቋማት ሠራተኞቻቸው በሥራ ገበታቸው የማይገኙ ከሆነ "አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምጃ" እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል።
ከአድማው መጀመር ሁለት ቀናት በኋላ የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "አስፈላጊ የሆነ ሕጋዊ እርምጃ" እንደሚወስድም አስጠንቅቋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዚሁ መግለጫው "ከሕግ አኳያ የጤና ሙያ የሥራ ማቆም አድማ ከማይደረጉባቸው የሥራ ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑ በግልጽ ተደንግጓል" ብሏል።
ጤና ሚኒስቴር የትኛው የሕግ ድንጋጌ ይህን ክልከላ እንዳስቀመጠ የጠቀሰው ነገር ግን የለም። የጤና ባለሙያዎቹ ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ የጠቀሱት የፌደራል መንግሥት የሠራተኞች አስተዳደር አዋጅ የሥራ ማቆም አድማ መምታትን በተመለከተ ምንም ዓይነት ድንጋጌ የለውም።
የሥራ ማቆም አድማ ከሕግ አንጻር
የሠራተኞችን መብት በሚመለከተው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ድንጋጌ፤ የተወሰኑ የሠራተኛ ክፍሎች "ሥራ ማቆምን ጨማሮ ቅሬታቸውን የማሰማት መብት" እንዳላቸው ያትታል።
ይህ መብት የተሰጣቸው የፋብሪካ እና አገልግሎት ሠራተኞች፣ ገበሬዎች፣ የእርሻ ሠራተኞች ሌሎች የገጠር ሠራተኞች ከተወሰነ ኃላፊነት ደረጃ በታች ያሉ እና የሥራ ጠባያቸው የሚፈቅድላቸው የመንግሥት ሠራተኞች መሆናቸውም ሕገ መንግሥቱ ላይ ሰፍሯል።
ሕገ መንግሥቱ አክሎም "[ይህን] መብት ለመጠቀም የሚችሉት የመንግሥት ሠራተኞች በሕግ ይወሰናሉ" ሲል ይደነግጋል።
ጠበቃ እና የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳንኤል ፍቃዱ ስለ ሕክምና ባለሙያዎች የሥራ ማቆም አድማ፤ "የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ግልጽ ድንጋጌ የለውም" ይላሉ።
ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ የሥራ ማቆም አድማን የተመለከተ ግልጽ ድንጋጌ ባይኖረውም ዓለም አቀፍ ሕጎች ግን ሥራ ማቆም አድማ ማድረግን እንደ ሰብአዊ መብት እንደሚቀጥሩት የሕግ ባለሙያው ያክላሉ።
"ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካል ናቸው" ተብሎ በሕገ መንግሥቱ ላይ ሰፍሯል።
የዓለም አቀፍ ሕጎች እንዴት ይተረጎማሉ?
አቶ ዳንኤል የዓለም አቀፍ አተረጓጎምን በተመለከተ ሁለት ንድፈ ሃሳቦች እንዳሉ ይጠቅሳሉ። እነዚህ ንደፈ ሃሳቦች monist እና dualist እንደሚባሉ የሚያነሱት አቶ ዳንኤል፤ "ኢትዮጵያ የቱ ጋር እንደሆነች በግልጽ ለማወቅ ከባድ ነው" ይላሉ።
"ሆኖም ግን በሰበር ሰሚ ችሎት እና በሌሎችም ፍርድ ቤቶች የሚደረጉ ክርክሮች እነዚሀን ሕጎች ተተርጉመው የኢትዮጵያ ሕግ አካል እስኪሆኑ ሳይጠብቁ ቀጥታ በፍርድ ቤት ክርክር ሲደረግባቸው በተግባር ይስተዋላል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ህግ ወደ Monist ያደላል" ሲሉ ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው እና የሥራ ማቆም አድማ ማድረግን የሚፈቅዱ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች መኖራቸውን የሚጠቅሱት ባለሙያው "እነዚህ [ዓለም አቀፍ] ሕጎች የአገሪቱ ሕግ አካል ናቸው፤ ሕገ መንግሥቱ እና ዓለም አቀፍ ሕጎቹ ደግሞ አቻ ናቸው" ይላሉ።
ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (ILO) በአውሮፓውያኑ 1948 እና 1949 ኮንቬንሽኖች ለመደራጀት ነጻነት የሥራ ማቆም አድማ የማድረግ መብትን አስፈላጊነት አስምሮበታል ይላሉ ባለሙያው።
"ኢትዮጵያ እንደ ደርርጅቱ አባል አገር እነዚህን መርሆች የማክበር ግዴታ አለባት" የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ "የአይኤልኦ ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጻሚነት አላቸው ማለት ነው" ሲሉ በአጽንኦት ይናገራሉ።
ነገር ግን በኢትዮጵያ ሠራተኞችን የተመለከቱ ሁለት ሕጎች አሉ።
አንደኛው አዋጅ ከስድስት ዓመታታ በፊት እንደ አዲስ ተሻሽሎ የወጣው የአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ባለፈው ጥር 2017 ዓ.ም. በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ነው።
የጤና ባለሙያዎቹ ቅሬታቸውን ከአንድ ወር በፊት ለጤና ሚኒስቴር ሲያቀርቡ የጠቀሱት እነሱን ጨምሮ በመንግሥት ሠራተኞች ላይ ተፈጻሚ የሚሆነውን ሁለተኛውን አዋጅ ነው።
ይህ የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ስለ ሥራ ማቆም አድማ ምንም የሚለው ነገር የለም።

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Health professionals
አቶ ዳንኤል "አንዳንድ ባለሙያዎች [አዋጁ ስለ ሥራ ማቆም አድማ] ዝም ካለ እንደተፈቀ ይቆጠራል ብለው የሚከራከሩ አሉ፤ ዝም ካለ አልተፈቀደም የሚሉም ደግሞ አሉ" ሲሉ በአዋጁ ዙሪያ የሚነሳውን ክርክር ያነሳሉ።
በሌላ በኩል የአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጁ ስለ ሥራ ማቆም አድማ ዝርዝር ድንጋጌ አለው። ነገር ግን ይህ አዋጅ ተፈጻሚ የሚሆነው በግል እና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ ነው።
አዋጁ በጤና ባለሙያዎች ላይ የተፈጻሚነት ወሰን ባይኖረውም ስለ ሥራ የማቆም አድማ የያዛቸውን ድንጋጌዎች እንመልከት።
አዋጁ "ሠራተኞች...ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሥራ ማቆም እርምጃ የመውሰድ መብት አላቸው" ይላል። ከዚህ በተጨማሪ አሠሪዎችም "የሥራ መዝጋት እርምጃ የመውሰድ መብት" እንዳላቸው ያትታል።
ነገር ግን እነዚህን "እርምጃዎች" መውሰድ የማይችሉ ድርጅቶች እና ሠራተኞች እንዳሉ አዋጁ ያስቀምጣል። እነሱም በአዋጁ "ለሕዝብ የማያቋርጥ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች" ተብለው የተጠቀሱት ናቸው።
ከእነዚህ ድርጀቶች መካከልም ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮች፣ የመድኃኒት ማከፋፈያ ድርጅቶች እና የመድኃኒት መሸጫ ቤቶች ይገኙበታል።
አዋጁ የሕክምና ተቋማትን "ሥራ ማቆም" እና "ሥራ መዝጋት" የከለከለው "እጅግ አስፈላጊ አገልግሎቶች ናቸው ብሎ ከደነጋጋቸው ውስጥ ሕክምና ስለሚገኝ" መሆኑን አቶ ዳንኤል ይጠቅሳሉ።
ነገር "እጅግ አስፈላጊ" የሚለው ሃሳብ ራሱም ለሁለት መከፈል እንዳለበት ያነሳሉ።
"የሕክምና ባለሙያዎች በሙሉ የሥራ ማቆም አድማ እንዳያደርጉ በሚከለክል መልኩ እና በጠባቡ መተርጎም የለበትም ምክንያቱም ድንጋጌው ዓለም አቀፍ ሕግ መሆኑ ግልጽ ስለሆነ" ይላሉ።
"በእነዚህ አግባብ ታይቶ ጭራሽኑ መብት የላቸውም ብሎ መከልከል አይቻልም፤ በጣም አስፈላጊ የሚባሉት መለየት አለባቸው" የሚሉት አቶ ዳንኤል "እጅግ አስፈላጊ" የሚባለው አገልግሎት ድንገተኛ፣ ማዋለጃ እና የሕጻናት ክፍል የመሳሰሉትን የያዘ ነው ሊሆን የሚችለው ሲሉ ይናገራሉ።
እነዚህ ክፍሎች ደግሞ አሁንም ሥራ እንዳላቆሙ የሚጠቁሙት ባለሙያው፤ "የጤና ባለሙያዎች በእነዚህ ክፍሎች ሥራ እንዲቀጥል አድርገዋል። ስለዚህ ሕጉን መከተል የሚመስል ነገር አለው" ሲሉ ያክላሉ።
ይህ ባይሆን እንኳን "በመሠረቱ [የጤና ባለሙያዎቹ] የግል ሠራተኞች አይደሉም፤ ጥያቄውን እያቀረቡ ያሉት የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው። መንግሥትን ነው ደመወዝ ይጨምርልን እያሉ እየጠየቁ ያሉት፤ ይህን ደግሞ ሕጉ በግልጽ የሚከልክል ነገር የለውም" ሲሉ ያብራራሉ።
የጤና ባለሙያዎቹ ተጠያቂ ይሆናሉ?
የጤና ባለሙያዎቹ የሥራ ማቆም አድማውን ማድረግ ከጀመሩ ወዲህ በርካቶች ለእስር ተዳርገዋል።
የጤና ባለሙያዎችን እስር በተመለከተ በመንግሥት በኩል ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥም የጤና ሚኒስቴር ግን በመግለጫው "በሥራ ገበታቸው ላይ ባልተገኙ" የጤና ባለሙያዎች ላይ "አስፈላጊ የሆነ ሕጋዊ እርምጃ" እንደሚወስድ ዝቷል።
ለመሆኑ የጤና ባለሙያዎች የሥራ ማቆም አድማ በማድረጋቸው በወንጀል ተጠያቂ ይሆናሉ?
የአገሪቱ የወንጀል ሕግ "ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ሕግን ወይም ሙያውን በሚቃረን ሁኔታ በፈቃዱ የሥራ ማቆም አድማ ያደረገ እንደሆነ ወይም የሥራ ማቆም አድማ እንዲደረግ ሌሎችን የገፋፋ እንደሆነ" በስድስት ወር እስራት ወይም የአንድ ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንደሚጣልበት ይደነግጋል።
ይህ ማለት ግን የጤና ባለሙያዎቸ የሥራ መቆም አድማ በመምራት ተጠያቂ ይሆናሉ ማለት አይደለም።
አቶ ዳንኤል ወንጀል በባህሪው ሦስት ነገሮች ማሟላት አለበት ይላሉ። እነሱም ድርጊት፣ በመጣሱ ሊያስቀጣ የሚችል ሕግ እና ሕጉ መጣሱን የሚያስረዱ ማስረጃዎች መኖር አለባቸው።
"አንድ ሕግ ተጣሰ ለመባል መጀመሪያ ያ ነገር በግልጽ የተከለከለ መሆን አለበት" የሚሉት አቶ ዳንኤል በኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች የሥራ ማቆም አድማ እንዳያደርጉ በግልጽ የሚከለክል ሕግ አለመኖሩን ይጠቁማሉ።
በተጨማሪም "ሕግ ኑሮ ያ ነገር በግልጽ ካልተጣሰ በስተቀር ወደ ወንጅል ሕጉ መሄድ አይቻልም። ያንን [የሥራ ማቆም አድማን] የሚከለክል ሕግ በሌለበት ወደ ውንጅላ እና እስር የሚኬድበት አግባብ የለም" ይላሉ።
"ወደ ዓለም አቀፍ ሕጉ ስንሄድ ደግሞ ሕጉ [አድማ ማድረገን] ይፈቅዳል መብት ነው፤ እንደ ሰብዓዊ መብት ነው የሚቆጠረው። ኢትዮጵያ ደግሞ እነዚህን ድንጋጌዎች አጽድቃለች" ሲሉ ያክላሉ።
ሕገ መንግሥቱ ሥራ የማቆም አድማ እና የመደራጀት መብትን "ለመጠቀም የሚችሉት የመንግሥት ሠራተኞች በሕግ ይወሰናሉ" ቢልም የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ስለዚህ ጉዳይ ምንም አላለም።
"አሁን አድማ እያደረጉ ያሉትን የጤና ባለሙያዎች የሚመለከት ከልካይ ድንጋጌ የለም" የሚሉት አቶ ዳንኤል ሕገ መንግሥቱ ይወጣል ያለው ሕግ ወጥቶ ፤"ዝርዝር ድንጋጌ እስከ ሌለ ድረስ ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ነው ተፈጻሚነት ያለው። ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ ከልክሏል ልንል እንችልም" ሲሉ ይናገራሉ።
አክለውም "በሕገ መንግሥቱ መሠረት ነው የታሰራችሁት ሊባሉ አይችሉም ስለዚህ ዝርዝር ድንጋጌ በሌለበት ሁኔታ እስሩ ሕገ ወጥ ነው ማለት ነው" ይላሉ።















