ፌደራል ፖሊስ 47 የጤና ባለሙያዎችን በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታወቀ

በቁጥጥር ስር የዋሉ የጤና ባለሙያዎች የደንብ ልብሳቸውን እንደለበሱ በፒክ አፕ መኪና ላይ ተጭነው፤ ጥይት የያዘ የጸጥታ ኃይል አብሯቸው ይታያል

የፎቶው ባለመብት, sm

ፌደራል ፖሊስ፤ በጤና ባለሙያዎች እየተነሳ ያለውን "የመብት ጥያቄ ሽፋን በማድረግ"፤ በአገሪቱ ውስጥ "ትርምስ እንዲፈጠር ከሚሠሩ ኃይሎች ጋር ያበሩ" 47 የጤና ባለሙያዎች በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታወቀ።

የጤና ባለሙያዎች "ሥራ ማቆም" እና ተያያዥ ተግባራት እንዳይፈጽሙ ያስጠነቀቀው ፌደራል ፖሊስ፤ እየወሰደ ያለውን "ሕጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል" ገልጿል።

ፌደራል ፖሊስ፤ የጤና ባለሙያዎችን እስር ለመጀመሪያ ጊዜ ያረጋገጠው ዛሬ አርብ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው።

የደመወዝ ጭማሪ እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን ያቀረቡት የጤና ባለሙያዎች ባለፈው ሳምንት የጀመሩትን ከፊል አድማ በዚህ ሳምንት ወደ ሙሉ አድማ አድርሰዋል።

ከዚህ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘም ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች እስር እና ጫና እየደረሰባቸው መሆኑን ሲገልጹ ቆይተዋል።

የእንቅስቃሴው አስባባሪዎች፤ ባለፈው ሳምንት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች "ከ80 በላይ" የሕክምና ባለሙያዎች መታሰራቸውን አስታውቀው ነበር።

ከዚህ መረጃ በኋላ የጤና ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ዮናታን ዳኛውን ጨምሮ የተወሰኑ የጤና ባለሙያዎች እንደተፈቱ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ "ቢያንስ 20" የጤና ባለሙያዎች እንደታሰሩ አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፌደራል ፖሊስ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ያሉት የጤና ባለሙያዎች ብዛት 47 እንደሆነ ገልጿል።

ግለሰቦቹ የታሰሩት "ሰሞኑን የጤና ባለሙያዎች ያነሱትን የመብት ጥያቄ ሽፋን በማድረግ በአገራችን ትርምስ እንዲፈጠር ከሚሠሩ ኃይሎች ጋር" በማበራቸው እንደሆነ ገልጿል።

የጤና ባለሙያዎቹ "ሕገ ወጥ የሥራ ማቆም አድማ" ማድረጋቸውን የገለጸው ፌደራል ፖሊስ፤ "በጤና ዘርፉ ላይ ሁከት በመፍጠር እና የታካሚዎችን ሕይወት አደጋ ላይ በመጣል" መጠርጠራቸውንም አስታውቋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት የጤና ባለሙያዎች፤ "ሌሎችም ሥራ እንዲያቆሙ ለአድማ በማነሳሳት፣ የታካሚዎች ሕይወት ለሞት እና ለአደጋ እንዲጋለጥ በማድረግ ሁከት እና ብጥብጥ በመፍጠር የተጠረጠሩ ናቸው" ብሏል።

ፌደራል ፖሊስ በጤና ባለሙያዎች እንደተፈጸሙ በመግለጽ በመግለጫው ከዘረዘራቸው ክሶች መካከል፤ "በተለያዩ የጤና ተቋማት የአድማ መረቦችን መዘርጋት" እንዲሁም "የጤና ባለሙያ ያልሆኑ አካላትን ነጭ ጋዋን በማስለበስ የሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ገብተዉ ሁከት እንዲፈጥሩ ማድረግ" የሚሉት ይገኙበታል።

የጤና ባለሙያዎቹ፤ "ሰላማዊ የሕክምና ሂደትን በማደናቀፍ የሕሙማን እና የጤና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ እንዲወድቅ" ማድረጋቸውንም ይዘረዝራል። በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለሙያዎች ከጤና ተቋማት ባሻገር፤ የጤና ትምህርት "በሚሰጥባቸው ተቋማት ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲስተጓጎል" ማድረጋቸውን ያትታል።

በጤና ተቋማት ሥራቸው ላይ የተገኙ ባልደረቦቻቸው ላይ "ዛቻ እና ማስፈራራት" መፈጸማቸውንም አክሏል። ፖሊስ፤ እነዚህን ተግባራት በመፈጸም የተጠረጠሩት 47 የጤና ባለሙያዎችን "በመረጃ እና በማስረጃ በመለየት በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያካሄደ እንደሚገኝ" አስታውቋል።

ፌደራል ፖሊስ በዚህ መግለጫው፤ የጤና ባለሙያዎች ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ተግባራት ከመፈጸም እንዲቆጠቡ አስጠንቅቋል።

ፖሊስ ማስጠንቀቂያ የሰጠባቸው ተግባራት "የሙያው ሥነ-ምግባር እና ሕግ በማይፈቅደው ሁኔታ የዜጎችን ሕይወት ለሞትና ለአደጋ በማጋለጥ ሥራ ማቆም" እንዲሁም "ሌሎችም ሥራ እንዲያቆሙ የማነሳሳት እና ማስፈራራት" የሚሉት ናቸው።

እነዚህ ድርጊቶች "የወንጀል ተግባር" መሆናቸውን የገለጸው ፖሊስ፣ ጤና ባለሙያዎች "ከዚህ ተግባር እንዲቆጠቡ" አሳስቧል።

መግለጫው፤ "ከዚህ ውጭ ሁከት እና ብጥብጥን ለማስፋፋት በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ፖሊስ እየወሰደ ያለውን ሕጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያሳውቃል" ሲልም አስጠንቅቋል።

ፖሊስ፤ "ሕዝባቸውን እና ሕግ አክብረው አገልግሎት እየሰጡ" ላሉ የጤና ባለሙያዎች "አስፈላጊውን ጥበቃ እንደሚያደርግ" አክሏል።

ፌደራል ፖሊስ ባለሙያዎቹ እነዚህ ድርጊቶች በመፈጸም መጠርጠራቸውን ቢገልጽም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ ጤና ባለሞያዎች "መብታቸውን ብቻ በመጠየቃቸው" መታሰራቸውን ገልጿል።

የጤና ባለሙያዎቹ በቁጥጥር ስር ዋሉት "የሚታሰሩበት ምክንያት ሳይነገራቸው" መሆኑን ያስታወቀው አምነስቲ፤ "ያለፍርድ ቤት ማዘዣ ቤታቸው መበርበሩንም" በመግለጫው ጠቅሷል።

አምነስቲ፤ መንግሥት "መብታቸውን በመጠቀማቸው ብቻ ለእስር የተዳረጉ ሁሉንም የጤና ባለሞያዎች በአፋጣኝ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሁሉንም እንዲለቅቅ" ጠይቋል።

የመንግሥት ባለስልጣናት "በሰላማዊ መንገድ እየተቃወሙ ያሉ ግለሰቦች ላይ እያደረሱ ያሉትን ወከባ እንዲያቆሙምም" ጥሪውን አቅርቧል።