በኬንያ ጥቅም ላይ በዋለ የንጽህና መጠበቂያ ምክንያት ሴት ሰራተኞች ራቁታቸውን እንዲወጡ ተደረጉ

የንጽህና መጠበቂያ ፓድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኬንያ ጥቅም ላይ የዋለ የንጽህና መጠበቂያ ተጥሏል በሚል ሴት ሰራተኞች እርቃናቸውን እንዲወጡ ያደረጉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

በአንድ የዓይብ ፋብሪካ ውስጥ የንጽህና መጠበቂያ ትክክለኛ ባልሆነ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ መገኘቱንም ተከትሎ የትኛዋ ሴት የወር አበባዋ ላይ መሆኗን ለመለየት ሴት ሰራተኞቹ ልብሳቸውን አውልቀው እንዲፈተሹ ተደርጓል።

ብራውን ፉድ የተሰኘው የዓይብ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ የንጽህና መጠበቂያ በቆሻሻ መጣያ ውስጥ ማን እንደጣለው ለማወቅም ሴት ሰራተኞችን ሰብስባለች።

ስራ አስኪያጇ ፓዱን ማን እንደጣለው ለማወቅ ጥያቄ ብታቀርብም ምላሽ ባለማግኘቷ ልብሳቸውን እንዲያወልቁ ትዕዛዝ መስጠቷም ተነግሯል።

ኩባንያው በጉዳዩ ላይ ምርመራ እንደጀመረና ይህንን ያደረገችው ስራ አስኪያጅም ማገዱን አስታውቋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ሶስት ግለሰቦች የጥቃት ክስ እንደቀረበባቸው የሊሙሩ ፖሊስ ለኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ገልጿል።

የምክር ቤት አባሏ ግሎሪያ ኦርዎባ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባጋሩት ቪዲዮ ሰኞ ምሽት ስለተፈጠረው ነገር “የሚረብሽ መልዕክት” እንደደረሳቸው ተናግረዋል።

በዚሁም ቪዲዮ ላይ “ስራ አስኪያጇ ጥቅም ላይ የዋለ የንጽህና መጠበቂያ ለሱ ባልተባለ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ መገኘቱንም ሰምቻለሁ” ብለዋል።

ስራ አስኪያጇ መጀመሪያ ሴት ሰራተኞቹን ሰብስባ ማን እንደጣለው ለማወቅ ጥረት ብታደርግም መልስ ስታጣ “የወር አበባዋ ላይ ያለችውን ሴት ለማወቅና ለመቅጣትም በሚል ልብሳቸውን አስወልቃለች” በማለት የወር አበባ ማሸማቀቅን የሚቃወሙት የምክር ቤት አባሏ ግሎሪያ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ለመግባት ቢያደርጉም ኩባንያው ችግሩን ከሰራተኞቻቸው ጋር ለመፍታት አለመቻሉን ተናግረዋል።

ብራውንስ ፉድ ኩባንያ በበኩሉ ጉዳዩ “አሳዝኖናል” እናም ይህ ሁኔታ ‘የኩባንያውን አጠቃላይ አሰራር አያንጸባርቅም” ብሏል በድረገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ።