ተመድ በግሪክ እና ቱርክ ድንበር ላይ እርቃናቸውን በተገኙት ስደተኞች ጉዳይ አዝኛለሁ አለ

የፎቶው ባለመብት, TWITTER
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተቋም በግሪክ እና ቱርክ ድንበር ላይ ወደ 100 የሚጠጉ ስደተኞች እርቃናቸውን መገኘታቸው "በጣም አሳዝኖኛል" ብሏል።
የ92ቱ ስደተኞች መነሻቸው ሶሪያ እና አፍጋኒስታን እንደሆነ የሚታመን ሲሆን፤ ስደተኞቹ እርቃናቸውን ለመገኘታቸው ጎረቤታሞቹ ቱርክ እና ግሪክ እርስ በእርሳቸው እየተወቃቀሱ ይገኛሉ።
ግሪክ ይህንን ያደረገቸው ቱርክ ናት ያለች ሲሆን “ለሰው ልጅ ስልጣኔ አሳፋሪ ተግባር” ስትል ወቅሳለች። ቱርክ በበኩሏ የጎረቤቷን ውንጀላ “የሐሰት ዜና” ብላ ያስተባበለችው ሲሆን “የጭካኔ ተግባር” ስትል ግሪክን ወቅሳለች።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዲደረግ የጠየቀ ሲሆን “በወጡት አስደንጋጭ ዘገባዎች እና ምስሎች በጣም አዝኛለሁ” ሲል ገልጿል።
የግሪክ ፖሊስ አርብ ዕለት ከቱርክ ጋር በሚያዋስነው ሰሜናዊ ድንበር አቅራቢያ እርቃናቸውን ከተገኙት 92 ስደተኞች መካከል የተወሰኑት ሰውነታቸው ላይ ጉዳት አጋጥሟቸው መገኘታቸውን ይፋ አድርጓል።
በግሪክ ፖሊስ እና በአውሮፓ ሕብረት የድንበር ኤጀንሲ ፍሮንቴክስ በተደረገው ምርመራ ስደተኞቹ የኤቭሮስ ወንዝን በፕላስቲክ ጀልባ አቋርጠው ከቱርክ ወደ ግሪክ እንደገቡ የሚያሳይ ማስረጃ መገኘቱን ፖሊስ አክሏል።
የግሪክ ባለስልጣናት እንዳሉት ስደተኞቹ ግሪክ ከገቡ በኋላ ወዲያውኑ ልብስ፣ ምግብ እና የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና እርዳታ አግኝተዋል።
ፍሮንቴክስ ግለሰቦቹ በዋናነት ከአፍጋኒስታን እና ከሶሪያ የመጡ እንደሆኑ እና የመብት ጥሰቶችም ሳያጋጥማቸው እንዳልቀረ ተናግሯል።
የግሪክ የሲቪሎች ጥበቃ ሚኒስትር ታኪስ ቴዎዶሪካኮስ ቱርክ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ቅራኔ ለመወጣት "ሕገ-ወጥ ስደትን መሳሪያ አድርጋ ትጠቀማለች" ሲሉ ከሰዋል።
የግሪክ የስደተኞች ጉዳይ ሚኒስትር ኖቲስ ሚታራቺ በትዊተር ገፃቸው ላይ ቱርክ የስደተኞች አያያዟ "ለስልጣኔ አሳፋሪ ነው" ብለዋል። አንካራ ጉዳዩን እንድታጣራ እና "ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላትን ድንበር ትጠብቃለች" ብለው እንደሚጠብቁ ሚንስትሩ ተናግረዋል።
ቱርክ በበኩሏ በጉዳዩ ላይ ምንም ኃላፊነት እንደማትወስድ እና "በኢሰብዓዊ አያያዝም" ግሪክን ተጠያቂ አድርገዋል።
የፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታይብ ኤርዶጋን ከፍተኛ የፕሬስ ረዳት ፋህረቲን አልቱን በማህበራዊ ድረ-ገጹጻቸው ላይ "የግሪክ የሐሰት ዜናዎች ማሽን ወደ ሥራው ተመልሷል" ብለዋል።
ክሱን "ከንቱ እና አስቂኝ ነው" በማለት ግሪክ የስደተኞቹን ምስል በማሰራጨት ለስደተኞቹ ክብር እንደሌላት አሳይታለች ሲሉ ወቅሰዋል።












