ኤምኤስኤፍ በኢትዮጵያ የተቋረጠው የምግብ ዕርዳታ በአስቸኳይ መጀመር አለበት አለ

የፎቶው ባለመብት, Susanne Doettling/MSF
ዓለም አቀፍ የድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በኢትዮጵያ የተቋረጠው የምግብ ዕርዳታ ሥርጭት በአስቸኳይ መጀመር አለበት አለ።
ተቋሙ በአገሪቱ ስደተኞች እና ተፈናቃዮችን ጨምሮ ተጋላጭ የሆኑ 20 ሚሊዮን ሕዝብ በምግብ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ መሆናቸውን አስታውሶ የተቋረጠው የምግብ ዕርዳት መቀጠል አለበት ሲል አሳስቧል።
በድርቅ እና በጦርነት ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ዕርዳታ ጠባቂ በሆነባት ኢትዮጵያ ከፍተኛውን የምግብ እርዳታ የሚያርቡት የአሜሪካ መንግሥት የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) እና የተመድ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የሚያቀርበው የምግብ እርዳታ ከተረጂዎች አፍ እየተነጠቀ ለሌላ ጥቅም ውሏል በሚል እንዲቋረጥ መወሰናቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶቹ የተወሰደውን የእርዳታ አቅርቦትን የማቋረጥ ውሳኔ “ፖለቲካዊ” ነው ሲል ተቃውሟል።
ተቋማቱ የዕርዳታ ምግብ ሥርጭቱን ከማቆማቸው በፊት እንኳ ኤምኤስኤፍ አገልግሎት በሚሰጥባቸው አካባቢዎች የምግብ እጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር ብሏል።
የኤምኤስኤፍ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ካራ ብሩክስ እገዳው ተግባራዊ የሆነው በመላ አገሪቱ ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ ቀድሞውንም አሳሳቢ በሆነበት ወቅት በመሆኑ ሁኔታው የከፋ ያደርገዋል ይላሉ።
ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድኑ በዚህ ዓመት በትግራይ ክልል ሸረ እና ሽራሮ ከተሞች ከጥር እስከ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ባሰባሰው መረጀ መሠረት ከ8ሺህ ነፍሰ ጡር እና አራስ እናቶች መካከል 72.5 በመቶው ለከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መጋለጣቸውን አረጋግጧል።
በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ውስጥ ያሉ እናቶች ከወሊድ ጋር የተያያዘ ችግር ሊገጥማቸው የሚችልበት ዕድል ሰፊ መሆኑን እና አዲስ የሚወለዱትም ለጤና መጓደል የተጋለጡ ናቸው ብሏል ድርጅቱ።
ከነብሰ ጡር እና አራስ ሴቶች በተጨማሪ ኤምኤስኤፍ በእነዚህ ሁለት የትግራይ ከተሞች ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 17 ሺህ 800 ልጆች ምርመራ ያደረገ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 6.5 በመቶው ከፍተኛ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል።
ኤምኤስኤፍ ከትግራይ ክልል በተጨማሪ የጋምቤላ እና የሶማሌ ክልል ከፍተኛ የምግብ እጥረት ከሚስተዋልባቸው ክልሎች መካከል እንደሚገኙበት ገልጿል።
የሶማሌ ክልል በአገሪቱ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ከፍተኛ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው ህጻናት መገኛ ክልል መሆኑን ገልጾ፣ በጋምቤላ ክልል ደግሞ ከአምስት ዓመት በተቻ የሆኑ እና በኤምኤስኤፍ የሚታከሙ ህጻናት ቁጥር ካለፈው ዓመት ወዲህ በእጥፍ መጨመሩን ገልጿል።
ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የምግብ ዕርዳታ መቼ እና የት መድረስ አለበት የሚለውን በመለየት ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደርሳቸው እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪውን አስተላልፏል።
ከሳምንት በፊት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ያቋረጠውን የምግብ ዕርዳታ በሐምሌ ወር ሊጀምር እንደሚችል መግለጹ ይታወቃል።












